Judges (20/21)  

1. የእስራኤልም ልጆች ሁሉ ወጡ፥ ማኅበሩም ከዳን እስከ ቤርሳቤህ ድረስ፥ ከገለዓድም አገር ሰዎች ጋር፥ ወደ እግዚአብሔር ወደ ምጽጳ እንደ አንድ ሰው ሆነው ተሰበሰቡ።
2. ከእስራኤልም ነገድ ሁሉ የሆኑ የሕዝብ ሁሉ አለቆች ሰይፍ በሚመዝዙ በቍጥርም አራት መቶ ሺህ እግረኞች በሆኑ በእግዚአብሔር ሕዝብ ጉባኤ ቆሙ።
3. የብንያምም ልጆች የእስራኤል ልጆች ወደ ምጽጳ እንደ ወጡ ሰሙ። የእስራኤልም ልጆች። ይህ ክፉ ነገር እንደምን እንደ ተደረገ ንገሩን አሉ።
4. የተገደለችውም ሴት ባል ሌዋዊው እንዲህ ብሎ መለሰላቸው። እኔና ቁባቴ በዚያ ለማደር ወደ ብንያም አገር ወደ ጊብዓ መጣን።
5. የጊብዓም ሰዎች ተነሡብኝ፥ ቤቱንም በሌሊት በእኛ ላይ ከበቡት፤ ሊገድሉኝም ወደዱ፥ በቁባቴም አጥብቀው አመነዘሩባት፥ እርስዋም ሞተች።
6. እኔም ቁባቴን ይዤ ቈራረኋጥጥኋት በእስራኤልም ዘንድ እንደዚህ ያለ ኃጢአትና ስንፍና ስለ ተሠራ ወደ እስራኤል ርስት አገር ሁሉ ሰደድሁ።
7. እነሆ፥ የእስራኤል ልጆች ሆይ፥ ሁላችሁ፥ ምክራችሁንና እዝናታችሁን በዚህ ስጡ።
8. ሕዝቡም ሁሉ እንደ አንድ ሰው ተነሥተው አሉ። ከእኛ ዘንድ ማንም ወደ ድንኳኑ አይሄድም፥ ወደ ቤቱም አይመለስም።
9. ነገር ግን በጊብዓ ላይ የምናደርገው ነገር ይህ ነው፤ በዕጣ እንወጣባታለን።
10. ወደ ብንያም ጊብዓ በመጡ ጊዜ እርስዋ በእስራኤል ላይ እንዳደረገችው እንደ ስንፍናዋ እንዲያደርጉ፥ ለሕዝብ ስንቅ የሚይዙ ከእስራኤል ነገድ ሁሉ ከመቶው አሥር ሰው ከሺሁም መቶ ሰው ከአሥሩም ሺህ አንድ ሺህ ሰው እንወስዳለን።
11. የእስራኤልም ሰዎች ሁሉ እንደ አንድ ሰው ሆነው በከተማይቱ ላይ ተሰበሰቡ።
13. የእስራኤልም ነገዶች። በእናንተ መካከል የተደረገ ይህ ክፉ ነገር ምንድር ነው? አሁንም እንድንገድላቸው ከእስራኤልም ክፋትን እንድናርቅ በጊብዓ ውስጥ ያሉትን ምናምንቴዎቹን ሰዎች አውጥታችሁ ስጡን ብለው ወደ ብንያም ነገድ ሁሉ ሰዎችን ላኩ። የብንያም ልጆች ግን የወንድሞቻቸውን የእስራኤልን ልጆች ቃል ሊሰሙ አልወደዱም።
14. የብንያምም ልጆች ከእስራኤል ልጆች ጋር ሊዋጉ ከየከተማው ወደ ጊብዓ ተሰበሰቡ።
15. በዚያም ቀን ከየከተማው የመጡ የብንያም ልጆች ተቈጠሩ፤ ቍጥራቸውም ከጊብዓ ሰዎች ሌላ ሀያ ስድስት ሺህ ሰይፍ የሚመዝዙ ሰዎች ነበሩ፤ ከጊብዓም ሰባት መቶ የተመረጡ ሰዎች ተቈጠሩ።
16. ከእነዚያም ሕዝብ ሁሉ ሰባት መቶ የተመረጡ ግራኝ ሰዎች ነበሩ፤ እነዚህም ሁሉ ድንጋይ ይወነጭፉ ነበር፤ አንዲት ጠጕርስ እንኳ አይስቱም።
17. ከብንያምም ልጆች ሌላ የእስራኤል ሰዎች አራት መቶ ሺህ ሰይፍ የሚመዝዙ ሰዎች ተቈጠሩ፤ እነዚህም ሁሉ ሰልፈኞች ነበሩ።
18. የእስራኤልም ልጆች ተነሥተው ወደ ቤቴል ወጡ፥ እግዚአብሔርንም። የብንያምን ልጆች ለመውጋት አስቀድሞ ማን ይውጣልን? ብለው ጠየቁት፤ እግዚአብሔርም። ይሁዳ ይቅደም አለ።
19. የእስራኤልም ልጆች በማለዳ ተነሥተው በጊብዓ ፊት ሰፈሩ።
20. የእስራኤልም ሰዎች ከብንያም ጋር ሊዋጉ ወጡ፤ የእስራኤልም ሰዎች በጊብዓ አጠገብ በእነርሱ ላይ ተሰልፈው ቆሙ።
21. የብንያምም ልጆች ከጊብዓ ወጡ፥ በዚያም ቀን ከእስራኤላውያን ሀያ ሁለት ሺህ ሰዎች ገደሉ።
22. ሕዝቡም፥ የእስራኤል ሰዎች፥ ተበራቱ፥ በፊተኛውም ቀን በተሰለፉበት ስፍራ ደግመው ተሰለፉ።
23. የእስራኤልም ልጆች ወጥተው በእግዚአብሔር ፊት እስከ ማታ ድረስ አለቀሱ፤ እግዚአብሔርንም። ከወንድሞቻችን ከብንያም ልጆች ጋር ለመዋጋት ዳግመኛ እንቀርባለን? ብለው ጠየቁ። እግዚአብሔርም። በእነርሱ ላይ ውጡ አለ።
24. በሁለተኛውም ቀን የእስራኤል ልጆች ከብንያም ልጆች ጋር ሊዋጉ ቀረቡ።
25. በሁለተኛውም ቀን ብንያም ከጊብዓ በእነርሱ ላይ ወጣ፥ ከእስራኤልም ልጆች ደግሞ አሥራ ስምንት ሺህ ሰዎች ገደሉ፤ እነዚህም ሁሉ ሰይፍ የሚመዝዙ ነበሩ።
26. የእስራኤልም ልጆች ሁሉ ሕዝቡም ሁሉ ወጥተው ወደ ቤቴል መጡ፥ አለቀሱም፥ በዚያም በእግዚአብሔር ፊት ተቀመጡ፥ በዚያም ቀን እስከ ማታ ድረስ ጾሙ፤ በእግዚአብሔር ፊት የሚቃጠልና የደኅንነት መሥዋዕት አቀረቡ።
28. በዚያም ዘመን የእግዚአብሔር የቃል ኪዳኑ ታቦት በዚያ ነበረና፥ በዚያም ዘመን የአሮን ልጅ የአልዓዛር ልጅ ፊንሐስ በፊቱ ይቆም ነበርና የእስራኤል ልጆች እግዚአብሔርን። ከወንድሞቻችን ከብንያም ልጆች ጋር ለመዋጋት ዳግመኛ እንውጣን ወይስ እንቅር? ብለው ጠየቁ። እግዚአብሔርም። ነገ በእጃችሁ አሳልፌ እሰጣቸዋለሁና ውጡ አለ።
29. እስራኤልም በጊብዓ ዙሪያ የተደበቁ ሰዎች አኖሩባት።
30. በሦስተኛውም ቀን የእስራኤል ልጆች ወደ ብንያም ልጆች ወጡ፥ በጊብዓም ፊት እንደ ቀድሞው ጊዜ ተሰለፉ።
31. የብንያምም ልጆች በሕዝቡ ላይ ወጡ፥ ከከተማይቱም ተሳቡ፤ እንደ ቀድሞውም ጊዜ፥ በአውራዎቹ መንገዶች፥ አንደኛው ወደ ቤቴል ሁለተኛውም ወደ ጊብዓ ሜዳ በሚወስዱት መንገዶች ላይ፥ ሕዝቡን ይመቱ ይገድሉም ጀመር፤ ከእስራኤልም ሠላሳ የሚያህሉ ሰዎችን ገደሉ።
32. የብንያምም ልጆች። እንደ ቀድሞው በፊታችን ተመቱ አሉ። የእስራኤል ልጆች ግን። እንሽሽ፥ ከከተማም ወደ መንገድ እንሳባቸው አሉ።
33. የእስራኤልም ሰዎች ሁሉ ከስፍራቸው ተነሥተው በበኣልታማር ተሰለፉ። ከእስራኤልም ተደብቀው የነበሩት ከስፍራቸው ከጊብዓ ሜዳ ወጡ።
34. ከእስራኤልም ሁሉ የተመረጡ አሥር ሺህ ሰዎች ወደ ጊብዓ አንጻር መጡ፤ ሰልፍም በርትቶ ነበር፤ መከራም እንዲያገኛቸው አላወቁም ነበር።
35. እግዚአብሔርም ብንያምን በእስራኤል ፊት መታ፤ በዚያም ቀን የእስራኤል ልጆች ከብንያም ሀያ አምስት ሺህ አንድ መቶ ሰዎች ገደሉ፤ እነዚህ ሁሉ ሰይፍ የሚመዝዙ ነበሩ።
36. የብንያም ልጆች እንደ ተመቱ አዩ፤ የእስራኤል ልጆች ግን በጊብዓ ላይ ባኖሩት ድብቅ ጦር ታምነዋልና ለብንያም ስፍራ ለቀቁላቸው።
37. ተደብቀውም የነበሩት ፈጥነው ወደ ጊብዓ ሮጡ፤ ተደብቀውም የነበሩት መጥተው ከተማውን ሁሉ በሰይፍ ስለት መቱ።
38. የተደበቁትም ሰዎች ከከተማው ብዙ ጢስ እንደ ደመና እንዲያስነሡ በእስራኤል ልጆችና በተደበቁት ሰዎች መካከል ምልክት ተደርጎ ነበር።
39. የእስራኤልም ሰዎች ከሰልፉ አፈገፈጉ፤ ብንያማውያንም። እንደ ቀድሞው ሰልፍ በፊታችን ተመትተዋል እያሉ ከእስራኤል ሰዎች ሠላሳ የሚያህሉ ሰዎች መምታትና መግደል ጀመሩ።
40. ምልክቱ በጢሱ ዓምድ ከከተማው ሊወጣ በጀመረ ጊዜ ብንያማውያን ወደ ኋላቸው ተመለከቱ፥ እነሆም፥ የሞላ ከተማው ጥፋት ወደ ሰማይ ወጣ።
41. የእስራኤልም ሰዎች ተመለሱ፥ የብንያምም ሰዎች ክፉ ነገር እንደ ደረሰባቸው አይተዋልና ደነገጡ።
42. ከእስራኤልም ሰዎች ፊት ጀርባቸውን መልሰው ወደ ምድረ በዳ መንገድ ሸሹ፤ ሰልፉም ተከታትሎ ደረሰባቸው፤ ከየከተማውም የወጡት በመካከላቸው ገደሉአቸው።
43. ብንያማውያንንም ከበቡ፥ በምሥራቅም በኩል እስካለው እስከ ጊብዓ አንጻር ድረስ አሳደዱአቸው፥ በመኑሔም አጠፉአቸው።
44. ከብንያምም አሥራ ስምንት ሺህ ሰው ሞተ፤ እነዚህ ሁሉ ጽኑዓን ነበሩ።
45. ከእነርሱም የተረፉት ተመልሰው ወደ ምድረ በዳ ወደ ሬሞን ዓለት ሸሹ፥ ከእነርሱም በየመንገዱ ላይ አምስት ሺህ ሰው ለቀሙ፤ ወደ ጊድአምም አሳደዱአቸው፥ ከእነርሱም ሁለት ሺህ ሰዎችን ገደሉ።
46. እንዲሁም በዚያ ቀን ከብንያም የሞቱት ሀያ አምስት ሺህ ሰይፍ የሚመዝዙ ሰዎች ነበሩ፤ እነዚህ ሁሉ ጽኑዓን ነበሩ።
47. ስድስቱም መቶ ሰዎች ተመልሰው ወደ ምድረ በዳ ወደ ሬሞን ዓለት ሸሹ፥ በሬሞን ዓለት አራት ወር ተቀመጡ።
48. የእስራኤልም ሰዎች በብንያም ልጆች ላይ ዳግመኛ ተመለሱ፤ ሞላውን ከተማ ከብቱንም ያገኙትንም ሁሉ በሰይፍ ስለት መቱ፤ ያገኙትንም ከተማ ሁሉ በእሳት አቃጠሉ።

  Judges (20/21)