Judges (18/21)  

1. በዚያም ዘመን በእስራኤል ዘንድ ንጉሥ አልነበረም። እስከዚያም ቀን ድረስ ለዳን ነገድ በእስራኤል ነገዶች መካከል ርስት አልደረሳቸውም ነበርና በዚያ ዘመን የሚቀመጡባት ርስት ይሹ ነበር።
2. የዳንም ልጆች ከወገናቸው አምስት ጽኑዓን ሰዎች ምድሪቱን እንዲሰልሉና እንዲመረምሩ። ሂዱ ምድሪቱንም ሰልሉ ብለው ከጾርዓና ከኤሽታኦል ሰደዱ። እነዚያም ወደ ተራራማው ወደ ኤፍሬም አገር ወደ ሚካ ቤት መጥተው በዚያ አደሩ።
3. በሚካ ቤት አጠገብም በነበሩ ጊዜ የሌዋዊውን የጕልማሳውን ድምፅ አወቁ፤ ወደ እርሱም ቀርበው። ወደዚህ ማን አመጣህ? በዚህስ የምታደርገው ምንድር ነው? በዚህስ ምን አለህ? አሉት።
4. እርሱም። ሚካ እንዲህ እንዲህ አደረገልኝ፥ ቀጠረኝም፥ እኔም ካህን ሆንሁለት አላቸው።
5. እነርሱም። የምንሄድበት መንገድ የቀና መሆኑን እናውቅ ዘንድ፥ እባክህ፥ እግዚአብሔርን ጠይቅልን አሉት።
6. እርሱም። የምትሄዱበት መንገድ በእግዚአብሔር ፊት ነውና በደኅና ሂዱ አላቸው።
7. አምስቱም ሰዎች ሄዱ ወደ ሌሳም መጡ፥ በውስጡም የነበሩትን ሕዝብ ተዘልለው አዩአቸው፥ አንደ ሲዶናውያንም ልማድ ጸጥ ብለው ተዘልለው ተቀምጠው ነበር፤ የሚያስቸግራቸውም የሚገዛቸውም አልነበረም፥ ከሲዶናውያንም ርቀው ከሰውም ሁሉ ተለይተው ለብቻቸው ይኖሩ ነበር።
8. ወደ ወንድሞቻቸውም ወደ ጾርዓና ወደ ኤሽታኦል ተመለሱ፤ ወንድሞቻቸውም። ምን ወሬ ይዛችኋል? አሉአቸው።
9. እነርሱም ምድሪቱን እግጅ መልካም እንደ ሆነች አይተናልና ተነሡ፥ በእነርሱ ላይ እንውጣ፤ እናንተ ዝም ትላላችሁን? ትሄዱ ዘንድ ምድሪቱንም ለመውረስ ትገቡ ዘንድ ቸል አትበሉ።
10. በሄዳችሁ ጊዜ ተዘልለው ወደ ተቀመጡ ሕዝብ ትደርሳላችሁ፥ ምድሪቱም ሰፊ ናት፤ እግዚአብሔርም በምድር ካለው ነገር ሁሉ አንዳች የማይጎድልበትን ስፍራ በእጃችሁ ሰጥቶአል አሉ።
11. ከዳን ወገንም የጦር ዕቃ የታጠቁ ስድስት መቶ ሰዎች ከዚያ ከጾርዓና ከኤሽታኦል ተነሥተው ሄዱ።
12. ወጥተውም በይሁዳ ባለችው በቂርያትይዓሪም ሰፈሩ፤ ስለዚህም የዚያ ስፍራ ስም እስከ ዛሬ ድረስ የዳን ሰፈር ተብሎ ተጠራ፤ እነሆም፥ ከቂርያትይዓሪም በስተ ኋላ ነው።
13. ከዚያም ወደ ተራራማው ወደ ኤፍሬም አገር አለፉ፤ ወደ ሚካም ቤት መጡ።
14. የሌሳን ምድር ሊሰልሉ ሄደው የነበሩት አምስቱ ሰዎችም ወንድሞቻቸውን። በእነዚህ ቤቶች ውስጥ ኤፉድና ተራፊም፥ የተቀረጸ ምስልና ቀልጦ የተሠራ ምስልም እንዳሉ ታውቃላችሁን? አሁንም የምታደርጉትን ምከሩ ብለው ተናገሩአቸው።
15. ከመንገዱም ፈቀቅ ብለው ጕልማሳው ሌዋዊ ወደ ነበረበት ወደ ሚካ ቤት መጡ፥ ደኅንነቱንም ጠየቁት።
16. የጦር ዕቃ የታጠቁት፥ ከዳን ልጆችም የሆኑት ስድስቱ መቶ ሰዎች በደጃፉ አጠገብ ቆመው ነበር።
17. ምድሪቱንም ሊሰልሉ ሄደው የነበሩት አምስቱ ሰዎች ወጥተው ወደዚያ ገቡ፤ የተቀረጸውን ምስል ኤፉዱንም ተራፊሙንም ቀልጦ የተሠራውን ምስልም ወሰዱ፤ ካህኑም የጦር ዕቃ ከታጠቁት ከስድስት መቶ ሰዎች ጋር በደጃፉ አጠገብ ቆሞ ነበር።
18. እነዚህም ወደ ሚካ ቤት ገብተው የተቀረጸውን ምስል ኤፉዱንም ተራፊሙንም ቀልጦ የተሠራውን ምስልም በወሰዱ ጊዜ፥ ካህኑ። ምን ታደርጋላችሁ? አላቸው።
19. እነርሱም። ዝም በል፥ እጅህንም በአፍህ ላይ ጫን፥ ከእኛም ጋር መጥተህ አባትና ካህን ሁንልን፤ ለአንድ ሰው ቤት ካህን መሆን ወይስ በእስራኤል ዘንድ ለነገድና ለወገን ካህን መሆን ማናቸው ይሻልሃል? አሉት።
20. ካህኑም በልቡ ደስ አለው፥ ኤፉዱንም ተራፊሙንም የተቀረጸውንም ምስል ወሰደ፥ በሕዝቡም መካከል ሄደ።
21. እነርሱም ዞረው ሄዱ፥ ሕፃናቶችንና ከብቶችን ዕቃዎችንም በፊታቸው አደረጉ።
22. ከሚካም ቤት በራቁ ጊዜ የሚካ ጐረቤቶች ተሰበሰቡ፥ የዳንም ልጆች ተከትለው ደረሱባቸው።
23. ወደ ዳንም ልጆች ጮኹ፥ የዳንም ልጆች ፊታቸውን መልሰው ሚካን። የምትጮኸው ምን ሆነህ ነው? አሉት።
24. እርሱም። የሠራኋቸውን አማልክቴን ካህኑንም ይዛችሁ ሄዳችኋል፤ ሌላ ምን አለኝ? እናንተስ። ምን ሆነሃል እንዴት ትሉኛላችሁ? አለ።
25. የዳንም ልጆች። የተቈጡ ሰዎች እንዳይወድቁብህ ነፍስህም የቤተ ሰቦችህም ነፍስ እንዳይጠፋብህ፥ ድምፅህን በእኛ መካከል አታሰማ አሉት።
26. የዳንም ልጆች መንገዳቸውን ሄዱ፤ ሚካም ከእርሱ እንደ በረቱ ባየ ጊዜ ተመልሶ ወደ ቤቱ ሄደ።
27. እነርሱም ሚካ የሠራውን ጣዖትና ለእርሱ የነበረውን ካህን ይዘው ወደ ሌሳ፥ ጸጥ ብሎ ተዘልሎም ወደ ተቀመጠው ሕዝብ፥ መጡ፤ በሰይፍም ስለት መቱአቸው፥ ከተማይቱንም በእሳት አቃጠሉአት።
28. ከተማይቱ ከሲዶና ራቅ ያለች ነበረችና፥ እነርሱም ከሌሎች ሰዎች ተለይተው ብቻቸውን ይኖሩ ነበርና የሚታደግ አልነበራቸውም። ሌሳም በቤትሮዖብ አጠገብ ባለች ሸለቆ ውስጥ ነበረች። ከተማይቱንም ሠርተው ተቀመጡባት።
29. ከተማይቱንም ከእስራኤል በተወለደው በአባታቸው በዳን ስም ዳን ብለው ጠሩአት፤ የከተማይቱም ስም አስቀድሞ ሌሳ ነበረ።
30. የዳንም ልጆች የተቀረጸውን ምስል ለራሳቸው አቆሙ፤ የሙሴም ልጅ የጌርሳም ልጅ ዮናታን፥ እርሱና ልጆቹ የአገሩ ሰዎች እስከሚማረኩበት ቀን ድረስ የዳን ነገድ ካህናት ነበሩ።
31. ሚካም ያደረገውን የተቀረጸ ምስል የእግዚአብሔር ቤት በሴሎ ባለበት ዘመን ሁሉ አቆሙ። a

  Judges (18/21)