← Judges (17/21) → |
1. | በተራራማውም በኤፍሬም አገር ሚካ የተባለ አንድ ሰው ነበረ። |
2. | እናቱንም። ከአንቺ ዘንድ የተወሰደው፥ የረገምሽበትም፥ በጆሮዬም የተናገርሽበት አንድ ሺህ አንድ መቶ ብር፥ እነሆ፥ በእኔ ዘንድ አለ፤ እኔም ወስጄዋለሁ አላት። እናቱም። ልጄ ሆይ፥ እግዚአብሔር ይባርክህ አለችው። |
3. | አንዱን ሺህ አንዱን መቶ ብርም መለሰላት፤ እናቱም። ይህን ብር የተቀረጸ ምስልና ቀልጦ የተሠራ ምስል አድርጌ ከእጄ ስለ ልጄ ለእግዚአብሔር እቀድሰዋለሁ፤ አሁንም ለአንተ እመልሰዋለሁ አለች። |
4. | ለእናቱም ገንዘቡን በመለሰላት ጊዜ እናቱ ሁለቱን መቶ ብር ወስዳ ለአንጥረኛ ሰጠችው፥ እርሱም የተቀረጸ ምስልና ቀልጦ የተሠራ ምስል አደረገው። ያም በሚካ ቤት ነበረ። |
5. | ሰውዮውም ሚካ የአምላክ ቤት ነበረው፤ ኤፉድና ተራፊም አደረገ፥ ከልጆቹም አንዱን ቀደሰው፥ ካህንም ሆነለት። |
6. | በዚያም ዘመን በእስራኤል ዘንድ ንጉሥ አልነበረም፤ ሰውም ሁሉ በፊቱ መልካም መስሎ የታየውን ያደርግ ነበር። |
7. | በቤተ ልሔም ይሁዳም ከይሁዳ ወገን የሆነ አንድ ጕልማሳ ነበረ፥ እርሱም ሌዋዊ ነበረ፥ በዚያም ይቀመጥ ነበር። |
8. | ይህም ሰው የሚቀመጥበትን ስፍራ ለመሻት ከከተማው ከቤተ ልሔም ይሁዳ ወጣ፤ ሲሔድም ወደ ተራራማው ወደ ኤፍሬም አገር ወደ ሚካ ቤት መጣ። |
9. | ሚካም። ከወዴት መጣህ? አለው። እርሱም። ከቤተ ልሔም ይሁዳ የሆንሁ ሌዋዊ ነኝ፤ የምቀመጥበትንም ስፍራ ለመሻት እሄዳለሁ አለው። |
10. | ሚካም። ከእኔ ዘንድ ተቀመጥ፥ አባትና ካህንም ሁነኝ፤ እኔም ልብሶችንና ምግብህን፥ በእየዓመቱም አሥር ብር እሰጥሃለሁ አለው። ሌዋዊውም ገባ። |
11. | ሌዋዊውም ከሰውዮው ጋር መቀመጥን ፈቀደ፤ ጕልማሳውም ከልጆቹ እንደ አንዱ ሆነለት። |
12. | ሚካም ሌዋዊውን ቀደሰ፥ ጕልማሳውም ካህኑ ሆነለት፥ በሚካም ቤት ነበረ። |
13. | ሚካም። ሌዋዊ ካህን ስለ ሆነልኝ እግዚአብሔር መልካም እንዲሠራልኝ አሁን አውቃለሁ አለ። |
← Judges (17/21) → |