Judges (15/21)  

1. ከዚህም በኋላ በስንዴ መከር ጊዜ ሶምሶን የፍየል ጠቦት ይዞ ሚስቱን ሊጠይቅ ሄደና። ወደ ጫጉላ ቤት ወደ ሚስቴ ልግባ አለ፤ አባትዋ ግን እንዳይገባ ከለከለው።
2. አባትዋም። ፈጽመህ የጠላሃት መስሎኝ ለሚዜህ አጋባኋፅት፤ ታናሽ እኅትዋ ከርስዋ ይልቅ የተዋበች አይደለችምን? እባክህ፥ በእርስዋ ፋንታ አግባት አለው።
3. ሶምሶንም። ከእንግዲህ ወዲህ በፍልስጥኤማውያን ላይ ክፉ ባደርግ እኔ ንጹሕ ነኝ አላቸው።
4. ሶምሶንም ሄዶ ሦስት መቶ ቀበሮች ያዘ፤ ችቦም ወስዶ ሁለት ሁለቱንም ቀበሮዎች በጅራታቸው አሰረ፥ በሁለቱም ጅራቶች ማካከል አንድ ችቦ አደረገ።
5. ችቦውንም አንድዶ በቆመው በፍልስጥኤማውያን እህል መካከል ሰደዳቸው፤ ነዶውንም የቆመውንም እህል ወይኑንም ወይራውንም አቃጠለ።
6. ፍልስጥኤማውያንም። ይህን ያደረገው ማን ነው? አሉ። እነርሱም። ሚስቱን ወስዶ ለሚዜው አጋብቶበታልና የተምናዊው አማች ሶምሶን ነው አሉ። ፍልስጥኤማያንም ወጥተው ሴቲቱንና አባትዋን በእሳት አቃጠሉ።
7. ሶምሶንም። እናንተ እንዲሁ ብታደርጉ እኔ እበቀላችኋለሁ፥ ከዚያም በኋላ ዐርፋለሁ አላቸው።
8. እርሱም ጭን ጭናቸውን ብሎ በታላቅ አገዳደል መታቸው፤ ወርዶም በኤጣም ዓለት ባለው ዋሻ ውስጥ ተቀመጠ።
9. ፍልስጥኤማውያንም ወጡ፥ በይሁዳም ሰፈሩ፥ በሌሒ ላይም ተበታትነው ተቀመጡ።
10. የይሁዳም ሰዎች። በእኛ ላይ የወጣችሁት ለምንድር ነው? አሉ። እነርሱም። ሶምሶንን ልናስር፥ እንዳደረገብንም ልናደርግበት መጥተናል አሉ።
11. ከይሁዳም ሰዎች ሦስት ሺህ የሚያህሉ በኤጣም ዓለት ወዳለው ዋሻ ወርደው ሶምሶንን። ገዦቻችን ፍልስጥኤማውያን እንደ ሆኑ አታውቅምን? ያደረግህብን ይህ ምንድር ነው? አሉት። እርሱም። እንዳደረጉብኝ እንዲሁ አደረግሁባቸው አላቸው።
12. እነርሱም። አስረን በፍልስጥኤማውያን እጅ አሳልፈን ልንሰጥህ መጥተናል አሉት። ሶምሶንም። እናንተ እንዳትገድሉኝ ማሉልኝ አላቸው።
13. እነርሱም። አስረን በእጃቸው አሳልፈን እንሰጥሃለን እንጂ አንገድልህም ብለው ተናገሩት። በሁለትም አዲስ ገመድ አስረው ከዓለቱ ውስጥ አወጡት።
14. ወደ ሌሒ በመጣ ጊዜም ፍልስጥኤማውያን እልል እያሉ ተገናኙት። የእግዚአብሔርም መንፈስ በኃይል ወረደበት፤ ክንዱም የታሰረበት ገመድ በእሳት እንደ ተበላ እንደ ተልባ እግር ፈትል ሆነ፥ ማሰሪያዎቹም ከእጁ ወደቁ።
15. አዲስም የአህያ መንጋጋ አገኘ፥ እጁንም ዘርግቶ ወሰደው፥ በእርሱም አንድ ሺህ ሰው ገደለ።
16. ሶምሶንም። በአህያ መንጋጋ ክምር በክምር ላይ አድርጌአቸዋለሁ፤ በአህያ መንጋጋ አንድ ሺህ ሰው ገድያለሁ አለ።
17. መናገሩንም በፈጸመ ጊዜ መንጋጋውን ከእጁ ጣለ፤ የዚያንም ስፍራ ስም ራማትሌሒ ብሎ ጠራው።
18. እርሱም እጅግ ተጠምቶ ነበርና። አንተ ይህችን ታላቅ ማዳን በባሪያህ እጅ ሰጥተሃል፤ አሁንም በጥም እሞታለሁ፥ ባልተገረዙትም እጅ እወድቃለሁ ብሎ ወደ እግዚአብሔር ጮኸ።
19. እግዚአብሔርም በሌሒ ያለውን አዘቅት ሰነጠቀ፥ ከእርሱም ውኃ ወጣ፤ እርሱም ጠጣ፥ ነፍሱም ተመለሰች፥ ተጠናከረም። ስለዚህም የዚያን ቦታ ስም ዓይንሀቆሬ ብሎ ጠራው፤ ይህም እስከ ዛሬ ድረስ በሌሒ አለ።
20. በፍልስጥኤማውያንም ዘመን በእስራኤል ላይ ሀያ ዓመት ፈረደ።

  Judges (15/21)