Judges (13/21)  

1. የእስራኤልም ልጆች በእግዚአብሔር ፊት እንደ ገና ክፉ ሥራ ሠሩ፤ እግዚአብሔርም በፍልስጥኤማውያን እጅ አርባ ዓመት አሳልፎ ሰጣቸው።
2. ከዳን ወገን የሆነ ማኑሄ የሚባል አንድ የጾርዓ ሰው ነበረ፤ ሚስቱም መካን ነበረች፥ ልጅም አልወለደችም።
3. የእግዚአብሔርም መልአክ ለሴቲቱ ተገልጦ እንዲህ አላት። እነሆ፥ አንቺ መካን ነሽ፥ ልጅም አልወለድሽም፤ ነገር ግን ትፀንሻለሽ፥ ወንድ ልጅም ትወልጃለሽ።
4. አሁንም ተጠንቀቂ፤ የወይን ጠጅን የሚያሰክርም ነገር አትጠጪ፥ ርኩስም ነገር አትብዪ።
5. እነሆ፥ ትፀንሻለሽ፥ ወንድ ልጅም ትወልጃለሽ፤ ልጁም ከእናቱ ማኅፀን ጀምሮ ለእግዚአብሔር የተለየ ናዝራዊ ይሆናልና በራሱ ላይ ምላጭ አይድረስበት፤ እርሱም እስራኤልን ከፍልስጥኤማውያን እጅ ማዳን ይጀምራል።
6. ሴቲቱም ወደ ባልዋ መጥታ። አንድ የእግዚአብሔር ሰው ወደ እኔ መጣ፥ መልኩም እንደ እግዚአብሔር መልአክ እጅግ የሚያስደነግጥ ነበረ፤ ከወዴትም እንደ መጣ አልጠየቅሁትም፥ እርሱም ስሙን አልነገረኝም።
7. እርሱም። እነሆ፥ ትፀንሻለሽ፥ ወንድ ልጅም ትወልጃለሽ፤ ልጁም ከእናቱ ማኅፀን ጀምሮ እስኪሞት ድረስ ለእግዚአብሔር የተለየ ናዝራዊ ይሆናልና አሁን የወይን ጠጅ የሚያሰክርም ነገር አትጠጪ፥ ርኩስም ነገር አትብዪ አለኝ ብላ ተናገረች።
8. ማኑሄም። ጌታ ሆይ፥ የላክኸው የእግዚአብሔር ሰው፥ እባክህ፥ እንደ ገና ወደ እኛ ይምጣ፤ ለሚወለደውም ልጅ ምን እንድናደርግ ያስገንዝበን ብሎ ወደ እግዚአብሔር ለመነ።
9. እግዚአብሔርም የማኑሄን ድምፅ ሰማ፤ የእግዚአብሔርም መልአክ እንደ ገና ለሴቲቱ በእርሻ ውስጥ ተቀምጣ ሳለች ተገለጠላት፤ ባልዋ ማኑሄ ግን ከእርስዋ ጋር አልነበረም።
10. ሴቲቱም ፈጥና ሮጠች ለባልዋም። እነሆ፥ በቀደም ዕለት ወደ እኔ የመጣው ሰው ደግሞ ተገለጠልኝ ብላ ነገረችው።
11. ማኑሄም ተነሥቶ ሚስቱን ተከተለ፥ ወደ ሰውዮውም መጥቶ። ከዚህች ሴት ጋር የተነጋገርህ አንተ ነህን? አለው። እርሱም። እኔ ነኝ አለ።
12. ማኑሄም። ቃልህ በደረሰ ጊዜ የልጁ ሥርዓት ምንድር ነው? የምናደርግለትስ ምንድር ነው? አለው።
13. የእግዚአብሔርም መልአክ ማኑሄን። ሴቲቱ ከነገርኋፅት ሁሉ ትጠንቀቅ።
14. ከወይንም ከሚወጣው ሁሉ አትብላ፥ የወይን ጠጅንም የሚያሰክርንም ነገር አትጠጣ፥ ርኩስም ነገር ሁሉ አትብላ፤ ያዘዝኋትን ሁሉ ትጠብቅ አለው።
15. ማኑሄም የእግዚአብሔርን መልአክ። የፍየል ጠቦት እስክናዘጋጅልህ ድረስ፥ እባክህ፥ ቆይ አለው።
16. የእግዚአብሔርም መልአክ ማኑሄን። አንተ የግድ ብትለኝ መብልህን አልበላም፤ የሚቃጠለውንም መሥዋዕት ማዘጋጀት ብትወድድ ለእግዚአብሔር አቅርበው አለው። ማኑሄም የእግዚአብሔር መልአክ መሆኑን አላወቀም ነበር።
17. ማኑሄም የእግዚአብሔርን መልአክ። ነገርህ በደረሰ ጊዜ እንድናከብርህ ስምህ ማን ነው? አለው።
18. የእግዚአብሔርም መልአክ። ስሜ ድንቅ ነውና ለምን ትጠይቃለህ? አለው።
19. ማኑሄም የፍየሉን ጠቦትና የእህሉን ቍርባን ወስዶ በድንጋይ ላይ ለእግዚአብሔር አቀረበው። መልአኩም ተአምራት አደረገ፥ ማኑሄና ሚስቱም ይመለከቱ ነበር።
20. ነበልባሉም ከመሠዊያው ላይ ወደ ሰማይ በወጣ ጊዜ የእግዚአብሔርም መልአክ በመሠዊያው ነበልባል ውስጥ ዐረገ፤ ማኑሄና ሚስቱም ተመለከቱ፥ በምድርም በግምባራቸው ተደፉ።
21. የእግዚአብሔርም መልአክ ዳግመኛ ላማኑሄና ለሚስቱ አልተገለጠም፤ ያን ጊዜም ማኑሄ የእግዚአብሔር መልአክ መሆኑን አወቀ።
22. ማኑሄም ሚስቱን። እግዚአብሔርን አይተናልና ሞት እንሞታለን አላት።
23. ሚስቱም። እግዚአብሔርስ ሊገድለን ቢወድድ ኖሮ የሚቃጠለውን መሥዋዕትና የእህሉን ቍርባን ከእጃችን ባልተቀበለን፥ ይህንም ነገር ሁሉ ባላሳየን፥ እንዲህ ያለ ነገርም በዚህ ጊዜ ባላስታወቀን ነበር አለችው።
24. ሴቲቱም ወንድ ልጅ ወለደች፥ ስሙንም ሶምሶን ብላ ጠራችው፤ ልጁም አደገ እግዚአብሔርም ባረከው።
25. የእግዚአብሔርም መንፈስ በጾርዓና በኤሽታኦል መካከል ባለው በዳን ሰፈር ውስጥ ሊያነቃቃው ጀመረ።

  Judges (13/21)