| ← Judges (12/21) → |
| 1. | የኤፍሬም ሰዎች ተሰበሰቡ፥ ወደ ጻፎንም ተሻግረው ዮፍታሔን። ከአሞን ልጆች ጋር ለመዋጋት ስታልፍ ከአንተ ጋር እንድንሄድ ስለ ምን አልጠራኸንም? ቤትህን በአንተ ላይ በእሳት እናቃጥለዋለን አሉት። |
| 2. | ዮፍታሔም። ከአሞን ልጆች ጋር ለእኔና ለሕዝቤ ጽኑ ጠብ ነበረን፤ በጠራኋችሁም ጊዜ ከእጃቸው አላዳናችሁኝም። |
| 3. | እንዳላዳናችሁኝም ባየሁ ጊዜ ነፍሴን በእጄ አድርጌ በአሞን ልጆች ላይ አለፍሁ፥ እግዚአብሔርም በእጄ አሳልፎ ሰጣቸው፤ ለምንስ ዛሬ ልትወጉኝ ወደ እኔ መጣችሁ? አላቸው። |
| 4. | ዮፍታሔም የገለዓድን ሰዎች ሁሉ ሰበሰበ፥ ከኤፍሬምም ጋር ተዋጋ፤ ኤፍሬምም። ገለዓዳውያን ሆይ፥ እናንተ በኤፍሬምና በምናሴ መካከል የተቀመጣችሁት ከኤፍሬም ሸሽታችሁ ነው ስላሉ የገለዓድ ሰዎች ኤፍሬምን መቱ። |
| 5. | ገለዓዳውያንም ኤፍሬም የሚያልፍበትን የዮርዳኖስን መሻገሪያ ያዙባቸው፤ የሸሸም የኤፍሬም ሰው። ልለፍ ባለ ጊዜ፥ የገለዓድ ሰዎች። አንተ ኤፍሬማዊ ነህን? አሉት፤ እርሱም። አይደለሁም ቢል፥ |
| 6. | እነርሱ። አሁን ሺቦሌት በል አሉት፤ እርሱም አጥርቶ መናገር አልቻለምና። ሲቦሌት አለ፤ ይዘውም በዮርዳኖስ መሻገሪያ አረዱት፤ በዚያም ጊዜ ከኤፍሬም አርባ ሁለት ሺህ ሰዎች ወደቁ። |
| 7. | ዮፍታሔም በእስራኤል ላይ ስድስት ዓመት ፈረደ። ገለዓዳዊውም ዮፍታሔ ሞተ፥ ከገለዓድም ከተሞች በአንዲቱ ተቀበረ። |
| 8. | ከእርሱም በኋላ የቤተ ልሔሙ ኢብጻን በእስራኤል ላይ ፈራጅ ሆነ። |
| 9. | ሠላሳም ወንዶች ልጆችና ሠላሳ ሴቶች ልጆች ነበሩት፤ ሠላሳ ሴቶች ልጆቹንም ወደ ውጭ አገር ዳረ፤ ለወንዶች ልጆቹም ከውጭ አገር ሴቶች ልጆችን አመጣ። በእስራኤልም ላይ ሰባት ዓመት ፈረደ። |
| 10. | ኢብጻንም ሞተ፥ በቤተ ልሔምም ተቀበረ። |
| 11. | ከእርሱም በኋላ ዛብሎናዊው ኤሎም በእስራኤል ላይ ፈራጅ ሆነ፤ እርሱም በእስራኤል ላይ አሥር ዓመት ፈረደ። |
| 12. | ዛብሎናዊውም ኤሎም ሞተ፥ በዛብሎንም ምድር ባለችው በኤሎም ተቀበረ። |
| 13. | ከእርሱም በኋላ የጲርዓቶናዊው የሂሌል ልጅ ዓብዶን በእስራኤል ላይ ፈራጅ ሆነ። |
| 14. | አርባም ልጆች ሠላሳም የልጅ ልጆች ነበሩት፤ በሰባም አህያ ግልገሎች ላይ ይቀመጡ ነበር። በእስራኤልም ላይ ስምንት ዓመት ፈረደ። |
| 15. | የጲርዓቶናዊውም የሂሌል ልጅ ዓብዶን ሞተ፥ በተራራማውም በአማሌቃውያን ምድር በኤፍሬም ባለችው በጲርዓቶን ተቀበረ። a |
| ← Judges (12/21) → |