← Judges (11/21) → |
1. | ገለዓዳዊውም ዮፍታሔ ጽኑዕ ኃያል ሰው የጋለሞታ ሴትም ልጅ ነበረ። ገለዓድም ዮፍታሔን ወለደ። |
2. | የገለዓድም ሚስት ወንዶች ልጆችን ወለደችለት፤ ልጆችዋም ባደጉ ጊዜ ዮፍታሔን። የልዩ ሴት ልጅ ነህና በአባታችን ቤት አትወርስም ብለው አሳደዱት። |
3. | ዮፍታሔም ከወንድሞቹ ፊት ሸሽቶ በጦብ ምድር ተቀመጠ፤ ምናምንቴዎችም ሰዎች ተሰብስበው ዮፍታሔን ተከተሉት። |
4. | ከዚያም ወራት በኋላ የአሞን ልጆች ከእስራኤል ጋር ይዋጉ ነበር። |
5. | የአሞንም ልጆች ከእስራኤል ጋር በተዋጉ ጊዜ የገለዓድ ሽማግሌዎች ዮፍታሔን ከጦብ ምድር ለማምጣት ሄዱ። |
6. | ዮፍታሔንም። ና፥ ከአሞን ልጆች ጋር እንድንዋጋ አለቃችን ሁን አሉት። |
7. | ዮፍታሔም የገለዓድን ሽማግሌዎች። የጠላችሁኝ ከአባቴም ቤት ያሳደዳችሁኝ እናንተ አይደላችሁምን? አሁን በተጨነቃችሁ ጊዜ ለምን ወደ እኔ መጣችሁ? አላቸው። |
8. | የገለዓድም ሽማግሌዎች ዮፍታሔን። ከእኛ ጋር እንድትወጣ፥ ከአሞንም ልጆች ጋር እንድትዋጋ፥ ስለዚህ አሁን ወደ አንተ ተመልሰን መጣን፤ በገለዓድም ሰዎች ሁሉ ላይ አለቃችን ትሆናለህ አሉት። |
9. | ዮፍታሔም የገለዓድን ሽማግሌዎች። ከአሞን ልጆች ጋር ለመዋጋት ወደ አገሬ ብትመልሱኝ፥ እግዚአብሔርም በእጄ አሳልፎ ቢሰጣቸው፥ እኔ አለቃችሁ እሆናለሁን? አላቸው። |
10. | የገለዓድም ሽማግሌዎች ዮፍታሔን። እግዚአብሔር በመካከላችን ምስክር ይሁን፤ በእርግጥ እንደ ቃልህ እናደርጋለን አሉት። |
11. | ዮፍታሔም ከገለዓድ ሽማግሌዎች ጋር ሄደ፥ ሕዝቡም በላያቸው ራስና አለቃ አደረጉት፤ ዮፍታሔም ቃሉን ሁሉ በእግዚአብሔር ፊት በምጽጳ ተናገረ። |
12. | ዮፍታሔም ወደ አሞን ልጆች ንጉሥ። አገሬን ለመውጋት ወደ እኔ የምትመጣ አንተ ከእኔ ጋር ምን አለህ? ብሎ መልክተኞችን ላከ። |
13. | የአሞንም ልጆች ንጉሥ የዮፍታሔን መልክተኞች። እስራኤል ከግብፅ በወጣ ጊዜ ከአርኖን ጀምሮ እስከ ያቦቅና እስከ ዮርዳኖስ ድረስ ምድሬን ስለ ወሰደ ነው፤ አሁንም በሰላም መልሱልኝ ብሎ መለሰላቸው። |
14. | ዮፍታሔም ወደ አሞን ልጆች ንጉሥ መልክተኞችን እንደ ገና ላከ፥ |
15. | እንዲህም አለው። ዮፍታሔ እንዲህ ይላል። እስራኤል የሞዓብን ምድር የአሞንንም ልጆች ምድር አልወሰደም፤ |
16. | ነገር ግን ከግብፅ በወጣ ጊዜ፥ እስራኤልም በምድረ በዳ በኩል ወደ ኤርትራ ባሕር በሄደ ጊዜ፥ ወደ ቃዴስም በደረሰ ጊዜ፥ |
17. | እስራኤል ወደ ኤዶምያስ ንጉሥ። በምድርህ እንዳልፍ፥ እባክህ፥ ፍቀድልኝ ብሎ መልክተኞችን ላከ፤ የኤዶምያስም ንጉሥ አልሰማም። እንዲሁም ወደ ሞዓብ ንጉሥ ላከ፥ እርሱም አልፈቀደም። |
18. | እስራኤልም በቃዴስ ተቀመጠ። በምድረ በዳም በኩል ሄዱ፥ የኤዶምያስንና የሞዓብንም ምድር ዞሩ፤ ከሞዓብ ምድርም በምሥራቅ በኩል መጡ በአርኖንም ማዶ ሰፈሩ፤ አርኖንም የሞዓብ ድንበር ነበረና የሞዓብን ድንበር አላለፉም። |
19. | እስራኤልም ወደ አሞራዊው ወደ ሐሴቦን ንጉሥ ወደ ሴዎን መልክተኞችን ላከ፤ እስራኤልም። በምድርህ በኩል ወደ ስፍራችን፥ እባክህ፥ አሳልፈን አለው። |
20. | ሴዎንም እስራኤል በድንበሩ እንዲያልፍ አላመነውም ነበር፤ ነገር ግን ሴዎን ሕዝቡን ሁሉ ሰበሰበ፥ በያሀጽም ሰፈረ፥ ከእስራኤልም ጋር ተዋጋ። |
21. | የእስራኤልም አምላክ እግዚአብሔር ሴዎንና ሕዝቡን ሁሉ በእስራኤል እጅ አሳልፎ ሰጠ፥ መቱአቸውም፤ እስራኤልም በዚያ ምድር ተቀምጠው የነበሩትን የአሞራውያንን ምድር ሁሉ ወረሰ። |
22. | ከአርኖንም እስከ ያቦቅ ድረስ ከምድረ በዳውም እስከ ዮርዳኖስ ድረስ የአሞራውያንን ምድር ሁሉ ወረሱ። |
23. | የእስራኤልም አምላክ እግዚአብሔር ከሕዝቡ ከእስራኤል ፊት አሞራውያንን አስወገደ፤ አንተም ምድሩን ትወርሳለህን? |
24. | አምላክህ ካሞሽ የሚሰጥህን አትወርስምን? እኛም አምላካችን እግዚአብሔር ከፊታችን ያስወጣቸውን የእነርሱን ምድር እንወርሳለን። |
25. | ወይስ ከሞዓብ ንጉሥ ከሴፎር ልጅ ከባላቅ አንተ ትሻላለህን? በውኑ እርሱ እስራኤልን ከቶ ተጣላውን? ወይስ ተዋጋውን? |
26. | እስራኤልም በሐሴቦንና በመንደሮችዋ፥ በአሮዔርና በመንደሮችዋ፥ በአርኖንም አቅራቢያ ባሉት ከተሞች ሁሉ ሦስት መቶ ዓመት ተቀምጦ በነበረ ጊዜ፥ በዚያ ዘመን ስለ ምን አልወሰዳችኋቸውም ነበር? |
27. | እኔ አልበደልሁህም፥ አንተ ግን ከእኔ ጋር እየተዋጋህ በድለኸኛል፤ ፈራጁ እግዚአብሔር በእስራኤል ልጆችና በአሞን ልጆች መካከል ዛሬ ይፍረድ። |
28. | ነገር ግን ዮፍታሔ የላከበትን ቃል የአሞን ልጆች ንጉሥ አልሰማም። |
29. | የእግዚአብሔርም መንፈስ በዮፍታሔ ላይ መጣ፤ እርሱም ገለዓድንና ምናሴን አለፈ፥ በገለዓድም ያለውን ምጽጳን አለፈ፥ ከምጽጳም ወደ አሞን ልጆች አለፈ። |
30. | ዮፍታሔም። በእውነት የአሞንን ልጆች በእጄ አሳልፈህ ብትሰጠኝ፥ |
31. | ከአሞን ልጆች ዘንድ በደኅና በተመለስሁ ጊዜ፥ ሊገናኘኝ ከቤቴ ደጅ የሚወጣው ማንኛውም ለእግዚአብሔር ይሆናል፤ ለሚቃጠልም መሥዋዕት አቀርበዋለሁ ብሎ ለእግዚአብሔር ስእለት ተሳለ። |
32. | ዮፍታሔም ሊዋጋቸው ወደ አሞን ልጆች አለፈ፥ እግዚአብሔርም በእጁ አሳልፎ ሰጣቸው። |
33. | ከአሮዔርም እስከ ሚኒትና እስከ አቤልክራሚም ድረስ ሀያ ከተሞችን በታላቅ አገዳደል መታቸው። የአሞንም ልጆች በእስራኤል ልጆች ፊት ተዋረዱ። |
34. | ዮፍታሄም ወደ ቤቱ ወደ ምጽጳ መጣ፥ እነሆም ልጁ ከበሮ ይዛ እየዘፈነች ልትገናኘው ወጣች፤ ለእርሱም አንዲት ብቻ ነበረች፤ ከእርስዋም በቀር ወንድ ወይም ሴት ሌላ ልጅ አልነበረውም። |
35. | እርስዋንም ባየ ጊዜ ልብሱን ቀድዶ። አወይ ልጄ ሆይ! ወደ እግዚአብሔር አፌን ከፍቻለሁና፥ ከዚያውም እመለስ ዘንድ አልችልምና በጣም አዋረድሽኝ አስጨነቅሽኝም አላት። |
36. | እርስዋም። አባቴ ሆይ፥ አፍህን ለእግዚአብሔር ከከፈትህ፥ እግዚአብሔር በጠላቶችህ በአሞን ልጆች ላይ ተበቅሎልሃልና በአፍህ እንደ ተናገርህ አድርግብኝ አለችው። |
37. | አባትዋንም። ይህ ነገር ይደረግልኝ፤ ከዚህ ሄጄ በተራሮች ላይ እንድወጣና እንድወርድ፥ ከባልንጀሮቼም ጋር ለድንግልናዬ እንዳለቅስ ሁለት ወር አሰናብተኝ አለችው። |
38. | እርሱም። ሂጂ አለ። ሁለት ወርም አሰናበታት፤ ከባልንጀሮችዋም ጋር ሄደች፥ በተራሮችም ላይ ለድንግልናዋ አለቀሰች። |
39. | ሁለትም ወር ከተፈጸመ በኋላ ወደ አባትዋ ተመለሰች፥ እንደ ተሳለውም ስእለት አደረገባት፤ እርስዋም ወንድ አላወቀችም ነበር። |
40. | የእስራኤልም ሴቶች ልጆች በዓመት በዓመቱ እየሄዱ የገለዓዳዊውን የዮፍታሔን ልጅ በዓመት አራት ቀን ሙሾ እንዲያወጡ በእስራኤል ዘንድ ልማድ ሆነ። |
← Judges (11/21) → |