| ← Judges (10/21) → |
| 1. | ከአቤሜሌክም በኋላ ከይሳኮር ነገድ የሆነ የዱዲ ልጅ የፎሖ ልጅ ቶላ እስራኤልን ለማዳን ተነሣ፤ በተራራማውም በኤፍሬም አገር ባለችው በሳምር ተቀምጦ ነበር። |
| 2. | በእስራኤልም ላይ ሀያ ሦስት ዓመት ፈረደ፤ ሞተም፥ በሳምርም ተቀበረ። |
| 3. | ከእርሱም በኋላ ገለዓዳዊው ኢያዕር ተነሣ፥ በእስራኤልም ላይ ሀያ ሁለት ዓመት ፈረደ። |
| 4. | በሠላሳ የአህያ ግልገሎች ይቀመጡ የነበሩ ሠላሳ ልጆችም ነበሩት፤ ለእነርሱም እስከ ዛሬ ድረስ የኢያዕር መንደሮች የተባሉ በገለዓድ ምድር ያሉ ሠላሳ ከተሞች ነበሩአቸው። |
| 5. | ኢያዕርም ሞተ፥ በቃሞንም ተቀበረ። |
| 6. | የእስራኤልም ልጆች በእግዚአብሔር ፊት እንደ ገና ክፉ ሥራ ሠሩ በኣሊምንና አስታሮትን የሶርያንም አማልክት፥ የሲዶናንም አማልክት፥ የሞዓብንም አማልክት፥ የአሞንንም ልጆች አማልክት፥ የፍልስጥኤማውያንንም አማልክት አመለኩ፤ እግዚአብሔርንም ተዉ፥ አላመለኩትምም። |
| 7. | የእግዚአብሔርም ቍጣ በእስራኤል ላይ ነደደ፥ በፍልስጥኤማውያንና በአሞን ልጆች እጅ አሳልፎ ሰጣቸው። |
| 8. | በዚያም ዓመት የእስራኤልን ልጆች ሥቃይ አበዙባቸው፤ በዮርዳኖስ ማዶ በአሞራውያን አገር በገለዓድ ውስጥ ያሉትን የእስራኤልን ልጆች ሁሉ አሥራ ስምንት ዓመት ተጋፉአቸው። |
| 9. | የአሞንም ልጆች ከይሁዳ ከብንያምና ከኤፍሬም ቤት ጋር ደግሞ ሊዋጋ ዮርዳኖስን ተሻገሩ፤ እስራኤልም እጅግ ተጨነቁ። |
| 10. | የእስራኤልም ልጆች። አምላካችንን ትተን በኣሊምን አምልከናልና አንተን በድለናል ብለው ወደ እግዚአብሔር ጮኹ። |
| 11. | እግዚአብሔርም የእስራኤልን ልጆች አላቸው። ግብፃውያን፥ አሞራውያንም፥ የአሞንም ልጆች፥ |
| 12. | ፍልስጥኤማውያንም፥ ሲዶናውያንም፥ አማሌቃውያንም፥ ማዖናውያንም አላስጨነቋችሁምን? ወደ እኔም ጮኻችሁ፥ እኔም ከእጃቸው አዳንኋችሁ። |
| 13. | እናንተ ግን ተዋችሁኝ ሌሎችንም አማልክት አመለካችሁ፤ ስለዚህም ደግሞ አላድናችሁም። |
| 14. | ሄዳችሁም የመረጣችኋቸውን አማልክት ጥሩ፤ እነርሱም በመከራችሁ ጊዜ ያድኑአችሁ። |
| 15. | የእስራኤልም ልጆች እግዚአብሔርን። እኛ ኃጢአትን ሠርተናል፤ አንተ ደስ የሚያሰኝህን አድርግብን ዛሬ ግን፥ እባክህ፥ አድነን አሉት። |
| 16. | ሌሎችንም አማልክት ከመካከላቸው አስወገዱ፥ እግዚአብሔርንም አመለኩ፤ ነፍሱም ስለ እስራኤል ጕስቍልና አዘነች። |
| 17. | የአሞንም ልጆች ተሰብስበው በገለዓድ ሰፈሩ። የእስራኤልም ልጆች ተሰብስበው በምጽጳ ሰፈሩ። |
| 18. | ሕዝቡም፥ የገለዓድ አለቆች፥ እርስ በእርሳቸው። ከአሞን ልጆች ጋር መዋጋት የሚጀምር ማን ነው? እርሱ በገለዓድ ሰዎች ሁሉ ላይ አለቃ ይሆናል አሉ። a |
| ← Judges (10/21) → |