| Judges (1/21) → |
| 1. | እንዲህም ሆነ፤ ኢያሱ ከሞተ በኋላ የእስራኤል ልጆች። ከነዓናውያንን ለመውጋት ማን በፊት ይወጣልናል? ብለው እግዚአብሔርን ጠየቁ። |
| 2. | እግዚአብሔርም። ይሁዳ ይውጣ፤ እነሆ፥ ምድሪቱን በእጁ አሳልፌ ሰጥቻለሁ አለ። |
| 3. | ይሁዳም ወንድሙን ስምዖንን። ከነዓናውያንን እንወጋ ዘንድ ከእኔ ጋር ወደ ዕጣዬ ውጣ፥ እኔም ደግሞ ከአንተ ጋር ወደ ዕጣህ እሄዳለሁ አለው። ስምዖንም ከእርሱ ጋር ሄደ። |
| 4. | ይሁዳም ወጣ፤ እግዚአብሔርም ከነዓናውያንንና ፌርዛውያንን በእጃቸው አሳልፎ ሰጣቸው፥ ከእነርሱም በቤዜቅ ውስጥ አሥር ሺህ ሰዎች ገደሉ። |
| 5. | አዶኒቤዜቅንም በቤዜቅ አገኙትና ተዋጉት፤ ከነዓናውያንንና ፌርዛውያንንም መቱአቸው። |
| 6. | አዶኒቤዜቅም ሸሸ፤ አሳድደውም ያዙት፥ የእጁንና የእግሩንም አውራ ጣት ቈረጡ። |
| 7. | አዶኒቤዜቅም። የእጃቸውና የእግራቸው አውራ ጣት የተቈረጡ ሰባ ነገሥታት ከገበታዬ በታች ፍርፋሪ ይለቅሙ ነበር፤ እኔ እንዳደረግሁ እግዚአብሔር እንዲሁ መለሰልኝ አለ። ወደ ኢየሩሳሌምም አመጡት፥ በዚያም ሞተ። |
| 8. | የይሁዳም ልጆች ኢየሩሳሌምን ተዋግተው ያዙአት፥ በሰይፍ ስለትም መቱአት፥ ከተማይቱንም በእሳት አቃጠሉአት። |
| 9. | ከዚያም በኋላ የይሁዳ ልጆች በተራራማው አገርና በደቡቡ በኩል በቈላውም ውስጥ የሚኖሩትን ከነዓናውያንን ሊወጉ ወረዱ። |
| 10. | ይሁዳም በኬብሮን የሚኖሩትን ከነዓናውያንን ሊወጋ ሄደ። የኬብሮንም ስም አስቀድሞ ቂርያትአርባቅ ነበረ። ሴሲንና አኪመንን ተላሚንም ገደሉ። |
| 11. | ከዚያም የዳቤርን ሰዎች ሊወጋ ሄደ፤ አስቀድሞም የዳቤር ስም ቅርያትሤፍር ነበረ። |
| 12. | ካሌብም። ቅርያትሤፍርን ለሚመታና ለሚይዝ ልጄን ዓክሳን አጋባዋለሁ አለ። |
| 13. | የካሌብም ትንሽ ወንድም የቄኔዝ ልጅ ጎቶንያል ያዛት፤ ልጁንም ዓክሳን አጋባው። |
| 14. | እርስዋም ወደ እርሱ በመጣች ጊዜ ከአባትዋ እርሻ እንዲለምን መከረችው። እርስዋም ከአህያዋ ወረደች፤ ካሌብም። ምን ፈለግሽ? አላት። |
| 15. | እርስዋም። በረከትን ስጠኝ፤ በደቡብ በኩል ያለውን ምድር ሰጥተኸኛልና የውኃ ምንጭ ደግሞ ስጠኝ አለችው። ካሌብም ላይኛውንና ታችኛውን ምንጭ ሰጣት። |
| 16. | የቄናዊው የሙሴ አማት ልጆችም ከይሁዳ ልጆች ጋር ዘንባባ ካለባት ከተማ ተነሥተው ከዓራድ በደቡብ በኩል ወዳለው ወደ ይሁዳ ምድረ በዳ ወጡ፤ ሄደውም ከሕዝቡ ጋር ተቀመጡ። |
| 17. | ይሁዳም ከወንድሙ ከስምዖን ጋር ሄደ፥ በጽፋት የተቀመጡትንም ከነዓናውያንን መቱ፥ ፈጽመውም አጠፉአት። የከተማይቱንም ስም ሔርማ ብለው ጠሩአት። |
| 18. | ይሁዳም ጋዛንና ዳርቻዋን፥ አስቀሎናንና ዳርቻዋን፥ አቃሮንንና ዳርቻዋን ያዘ። |
| 19. | እግዚአብሔርም ከይሁዳ ጋር ነበረ፤ ይሁዳም ተራራማውን አገር ወረሰ፤ በሸለቆው የሚኖሩት ግን የብረት ሰረገሎች ነበሩአቸውና ሊያወጣቸው አልቻለም። |
| 20. | ሙሴም እንደ ተናገረ ለካሌብ ኬብሮንን ሰጡት፤ ከዚያም ሦስቱን የዔናቅ ልጆች አወጣ። |
| 21. | ነገር ግን በኢየሩሳሌም የሚኖሩትን ኢያቡሳውያንን የብንያም ልጆች አላወጡአቸውም፤ ኢያቡሳውያንም ከብንያም ልጆች ጋር እስከ ዛሬ ድረስ በኢየሩሳሌም ተቀምጠዋል። |
| 22. | የዮሴፍም ወገን ደግሞ በቤቴል ላይ ወጡ፥ እግዚአብሔርም ከእነርሱ ጋር ነበረ። |
| 23. | የዮሴፍም ወገን ቤቴልን የሚሰልሉ ላኩ። አስቀድሞም የከተማይቱ ስም ሎዛ ይባል ነበር። |
| 24. | ጠባቂዎቹም አንድ ሰው ከከተማ ሲወጣ አይተው። የከተማይቱን መግቢያ አሳየን፥ እኛም ቸርነት እናደርግልሃለን አሉት። |
| 25. | የከተማይቱንም መግቢያ አሳያቸው፥ ከተማይቱንም በሰይፍ ስለት መቱ፤ ያንን ሰውና ወገኖቹን ግን ለቀቁአቸው። |
| 26. | ሰውየውም ወደ ኬጢያውያን ምድር ሄደ፥ በዚያም ከተማን ሠራ፥ ስምዋንም ሎዛ ብሎ ጠራት። እስከ ዛሬም ድረስ ስምዋ ይህ ነው። |
| 27. | ምናሴም የቤትሳንንና የመንደሮችዋን፥ የታዕናክንና የመንደሮችዋን፥ የዶርንና የመንደሮችዋን፥ የይብለዓምንና የመንደሮችዋን፥ የመጊዶንና የመንደሮችዋን ሰዎች አላወጣቸውም፤ ነገር ግን ከነዓናውያን በዚያ አገር በመቀመጥ ጸኑ። |
| 28. | እስራኤልም በበረቱ ጊዜ ከነዓናውያንን አስገበሩአቸው፥ ፈጽመውም አላወጡአቸውም። |
| 29. | ኤፍሬምም በጌዝር የተቀመጡትን ከነዓናውያንን አላወጣቸውም፤ ነገር ግን ከነዓናውያን በመካከላቸው በጌዝር ተቀመጡ። |
| 30. | ዛብሎንም የቂድሮንንና የነህሎልን ሰዎች አላወጣቸውም፤ ነገር ግን ከነዓናውያን በመካከላቸው ተቀመጡ፥ ግብርም የሚገብሩለት ሆኑ። |
| 31. | አሴርም የዓኮንና የሲዶንን የአሕላብንም የአክዚብንም የሒልባንም የአፌቅንም የረአብንም ሰዎች አላወጣቸውም። |
| 32. | በዚያችም ምድር የተቀመጡትን ከነዓናውያን አላወጡአቸውምና በመካከላቸው የአሴር ልጆች ተቀመጡ። |
| 33. | ንፍታሌምም የቤትሳሚስንና የቤትዓናትን ሰዎች አላወጣቸውም፥ በምድሩም በተቀመጡት በከነዓናውያን መካከል ተቀመጡ፤ ነገር ግን የቤትሳሚስና የቤትዓናት ሰዎች ግብር የሚገብሩለት ሆኑ። |
| 34. | አሞራውያንም የዳንን ልጆች ወደ ተራራማው አገር እንዲያፈገፍጉ አስገደዱአቸው፥ ወደ ሸለቆውም እንዳይወርዱ ከለከሉአቸው። |
| 35. | አሞራውያን በሔሬስ ተራራና በኤሎን በሸዓልቢምም በመቀመጥ ጸኑ፤ ነገር ግን የዮሴፍ ቤት እጅ ከበደች፥ አስገበረቻቸውም። |
| 36. | የአሞራውያንም ድንበር ከአቅረቢም ዐቀበት ከጭንጫው ጀምሮ እስከ ላይ ድረስ ነበረ። |
| Judges (1/21) → |