← Joshua (7/24) → |
1. | የእስራኤል ልጆች ግን እርም በሆነው ነገር በደሉ፤ ከይሁዳ ነገድ የሆነ አካን፥ እርሱም የከርሚ ልጅ፥ የዘንበሪ ልጅ፥ የዛራ ልጅ፥ እርም ከሆነው ነገር ወሰደ፤ የእግዚአብሔርም ቍጣ በእስራኤል ልጆች ላይ ነደደ። |
2. | ኢያሱም ከቤቴል በምሥራቅ በኩል በቤትአዌን አጠገብ ወዳለችው ወደ ጋይ ሰዎችን ከኢያሪኮ ልኮ። ውጡ ምድሪቱንም ሰልሉ ብሎ ተናገራቸው፤ ሰዎቹም ወጡ፥ ጋይንም ሰለሉ። |
3. | ወደ ኢያሱም ተመልሰው። ሁለት ወይም ሦስት ሺህ ያህል ሰው ወጥተው ጋይን ይምቱ እንጂ ሕዝቡ ሁሉ አይውጣ፤ ጥቂቶች ናቸውና ሕዝቡ ሁሉ ወደዚያ ለመሄድ አይድከም አሉት። |
4. | ሦስት ሺህ ያህል ሰዎችም ወደዚያ ወጡ፤ ከጋይም ሰዎች ፊት ሸሹ። |
5. | የጋይም ሰዎች ከእነርሱ ሠላሳ ስድስት ያህል ሰዎችን መቱ፤ ከበሩ እስከ ሸባሪም ድረስ አባረሩአቸው በቍልቍለቱም መቱአቸው፤ የሕዝቡም ልብ ቀለጠ፥ እንደ ውኃም ሆነ። |
6. | ኢያሱም ልብሱን ቀደደ፥ እርሱና የእስራኤልም ሽማግሌዎች በእግዚአብሔር ታቦት ፊት እስከ ማታ ድረስ በግምባራቸው ተደፉ፤ በራሳቸውም ላይ ትቢያ ነሰነሱ። |
7. | ኢያሱም አለ። ዋይ! ጌታ እግዚአብሔር ሆይ፥ በአሞራውያን እጅ አሳልፈህ ትሰጠን ታጠፋንም ዘንድ ይህን ሕዝብ ዮርዳኖስን ለምን አሻገርኸው? በዮርዳኖስ ማዶ መቀመጥን በወደድን ነበር እኮ! |
8. | ጌታ ሆይ፥ እስራኤል በጠላቶቻቸው ፊት ከሸሹ ምን እላለሁ? |
9. | ከነዓናውያንም በምድሪቱ የሚኖሩ ሁሉ ሰምተው ይከብቡናል፥ ስማችንንም ከምድር ያጠፋሉ፤ ለታላቁ ስምህም የምታደርገው ምንድር ነው? |
10. | እግዚአብሔርም ኢያሱን አለው። ለምን በግምባርህ ተደፍተሃል? ቁም፤ |
11. | እስራኤል በድሎአል፤ ያዘዝኋቸውንም ቃል ኪዳኔን አፍርሰዋል፤ እርም የሆነውንም ነገር ወሰዱ፥ ሰረቁም፥ ዋሹም፥ በዕቃቸውም ውስጥ ሸሸጉት። |
12. | ስለዚህም የእስራኤል ልጆች በጠላቶቻቸው ፊት መቆም አይችሉም፤ የተረገሙ ስለ ሆኑ በጠላቶቻቸው ፊት ይሸሻሉ፤ እርም የሆነውንም ነገር ከመካከላችሁ ካላጠፋችሁ ከዚህ በኋላ ከእናንተ ጋር አልሆንም። |
13. | ተነሣና ሕዝቡን ቀድስ፥ እንዲህም በላቸው። እስራኤል ሆይ፥ እርም የሆነ ነገር በመካከልህ አለ፤ እርምም የሆነውን ነገር ከመካከላችሁ እስክታጠፉ ድረስ በጠላቶቻችሁ ፊት መቆም አትችሉም ብሎ የእስራኤል አምላክ እግዚአብሔር ተናግሮአልና እስከ ነገ ተቀደሱ። |
14. | ነገም በየነገዳችሁ ትቀርባላችሁ፤ እግዚአብሔርም የሚለየው ነገድ በየወገኖቹ ይቀርባል፤ እግዚአብሔርም የሚለየው ወገን በየቤተ ሰቦቹ ይቀርባል፤ እግዚአብሔርም የሚለየው ቤተ ሰብ በየሰዉ ይቀርባል። |
15. | እርም የሆነውም ነገር የተገኘበት ሰው የእግዚአብሔርን ቃል ኪዳን አፍርሶአልና፥ በእስራኤልም ዘንድ በደል አድርጎአልና እርሱና ያለው ሁሉ በእሳት ይቃጠላሉ። |
16. | ኢያሱም ማልዶ ተነሣ፥ እስራኤልንም በየነገዶቻቸው አቀረበ፤ የይሁዳም ነገድ ተለየ፤ |
17. | የይሁዳንም ወገን አቀረበ የዛራንም ወገን ለየ፤ የዛራንም ወገን ሰዎች አቀረበ፤ |
18. | ዘንበሪም ተለየ፤ የቤቱንም ሰዎች አቀረበ፤ ከይሁዳም ነገድ የሆነ የከርሚ ልጅ የዘንበሪ ልጅ የዛራ ልጅ አካን ተለየ። |
19. | ኢያሱም አካንን። ልጄ ሆይ፥ ለእስራኤል አምላክ ለእግዚአብሔር ክብር ስጥ፥ ለእርሱም ተናዘዝ፤ ያደረግኸውንም ንገረኝ፤ አትሸሽገኝ አለው። |
20. | አካንም መልሶ ኢያሱን። በእውነት የእስራኤልን አምላክ እግዚአብሔርን በድያለሁ እንዲህና እንዲህም አድርጌአለሁ። |
21. | በዘረፋ መካከል አንድ ያማረ የሰናዖር ካባ፥ ሁለት መቶም ሰቅል ብር፥ ሚዛኑም አምሳ ሰቅል የሆነ ወርቅ አይቼ ተመኘኋቸው፥ ወሰድኋቸውም፤ እነሆም፥ በድንኳኔ ውስጥ በመሬት ተሸሽገዋል፥ ብሩም ከሁሉ በታች ነው አለው። |
22. | ኢያሱም መልክተኞች ሰደደ ወደ ድንኳኑም ሮጡ፤ እነሆም፥ በድንኳኑ ውስጥ ተሸሽጎ ነበር፥ ብሩም በበታቹ ነበረ። |
23. | ከድንኳኑም ውስጥ ወስደው ወደ ኢያሱና ወደ እስራኤል ልጆች ሁሉ አመጡት፤ በእግዚአብሔርም ፊት አኖሩት። |
24. | ኢያሱና እስራኤል ሁሉ የዛራን ልጅ አካንን፥ ብሩንም፥ ካባውንም፥ ወርቁንም፥ ወንዶችና ሴቶች ልጆቹንም፥ በሬዎቹንም፥ አህያዎቹንም፥ በጎቹንም፥ ድንኳኑንም፥ ያለውንም ሁሉ ወስደው ወደ አኮር ሸለቆ አመጡአቸው። |
25. | ኢያሱም። ለምን አስጨነቅኸን? እግዚአብሔር ዛሬ ያስጨንቅሃል አለው፤ እስራኤልም ሁሉ በድንጋይ ወገሩት፤ በእሳትም አቃጠሉአቸው፥ በድንጋይም ወገሩአቸው። |
26. | በላዩም እስከ ዛሬ ድረስ ያለ ታላቅ የድንጋይ ክምር ከመሩ፤ እግዚአብሔርም ከቍጣው ትኵሳት ተመለሰ። ስለዚህም የዚያ ስፍራ ስም እስከ ዛሬ ድረስ የአኮር ሸለቆ ተብሎ ተጠራ። |
← Joshua (7/24) → |