| ← Joshua (23/24) → |
| 1. | እንዲህም ሆነ፤ ብዙ ዘመን ከሆነ በኋላ፥ እግዚአብሔርም እስራኤልን በዙሪያቸው ካሉት ጠላቶቻቸው ሁሉ ካሳረፈ በኋላ፥ ኢያሱም በሸመገለ በዕድሜውም ባረጀ ጊዜ፥ |
| 2. | ኢያሱ እስራኤልን ሁሉ ሽማግሌዎቻቸውንም አለቆቻቸውንም ፈራጆቻቸውንም ሹማምቶቻቸውንም ጠርቶ እንዲህ አላቸው። እኔ ሸምግያለሁ፥ በዕድሜም አርጅቻለሁ፤ |
| 3. | እናንተም አምላካቸሁ እግዚአብሔር በእነዚህ አሕዛብ ሁሉ ስለ እናንተ ያደረገውን ሁሉ አይታችኋል፤ ስለ እናንተ የተዋጋ እርሱ አምላካችሁ እግዚአብሔር ነው። |
| 4. | እነሆ፥ እኔ ካጠፋኋቸው አሕዛብ ሁሉ ጋር ከዮርዳኖስ ጀምሮ በፀሐይ መግቢያ እስካለው እስከ ታላቁ ባሕር ድረስ ለነገዶቻችሁ ርስት እንዲሆኑ የቀሩትን እነዚህን አሕዛብ በዕጣ ከፈልሁላችሁ። |
| 5. | አምላካችሁም እግዚአብሔር እርሱ ከፊታችሁ በብርቱ ይበትናቸዋል፥ ከፊታችሁም ያሳድዳቸዋል፤ አምላካችሁ እግዚአብሔር እንደ ተናገራችሁም ምድራቸውን ትወርሳላችሁ። |
| 6. | ስለዚህም በሙሴ ሕግ መጽሐፍ የተጻፈውን ሁሉ ለመጠበቅና ለማድረግ በጣም በርቱ፥ ከእርሱም ወደ ቀኝም ወደ ግራም ፈቀቅ አትበሉ። |
| 7. | በእናንተ መካከል ወደ ቀሩት ወደ እነዚህ አሕዛብ አትግቡ፤ የአማልክቶቻቸውንም ስም አትጥሩ፥ አትማሉባቸውም፥ አታምልኩአቸውም፥ አትስገዱላቸውም፤ |
| 8. | እስከ ዛሬ ድረስ እንዳደረጋችሁት ወደ አምላካችሁ ወደ እግዚአብሔር ተጠጉ እንጂ። |
| 9. | እግዚአብሔር ታላላቆችንና ኃይለኞችን አሕዛብ ከፊታችሁ አስወጥቶአል፤ እስከ ዛሬም ድረስ ማንም ሊቋቋማችሁ አልቻለም። |
| 10. | አምላካችሁ እግዚአብሔር እንደ ተናገራችሁ ስለ እናንተ የሚዋጋ እርሱ ነውና ከእናንተ አንዱ ሰው ሺህ ሰውን ያሳድዳል። |
| 11. | አምላካችሁን እግዚአብሔርን ትወድዱት ዘንድ ለራሳችሁ እጅግ ተጠንቀቁ። |
| 12. | እናንተ ግን ተመልሳችሁ በመካከላችሁ ወደ ቀሩት ወደ እነዚህ አሕዛብ ብትጠጉ፥ ከእነርሱም ጋር ብትጋቡ፥ እናንተም ወደ እነርሱ እነርሱም ወደ እናንተ ብትደራረሱ፥ |
| 13. | አምላካችሁ እግዚአብሔር ከሰጣችሁ ከዚህች ከመልካሚቱ ምድር እስክትጠፉ ድረስ መውደቂያና ወጥመድ፥ በጎናችሁም መግረፊያ፥ በዓይናችሁም እሾህ ይሆኑባችኋል እንጂ አምላካችሁ እግዚአብሔር ከእንግዲህ ወዲያ እነዚህን አሕዛብ ከፊታችሁ እንዳያሳድዳቸው ፈጽማችሁ እወቁ። |
| 14. | እነሆም፥ ዛሬ የምድርን ሁሉ መንገድ እሄዳለሁ፤ እናንተም እግዚአብሔር ስለ እናንተ ከተናገረው ከመልካም ነገር ሁሉ አንድ ነገር እንዳልቀረ በልባችሁ ሁሉ በነፍሳችሁም ሁሉ እወቁ፤ ሁሉ ደርሶላችኋል፤ ከእርሱም አንድ ነገር አልቀረም። |
| 15. | አምላካችሁ እግዚአብሔር የተናገረው መልካም ነገር ሁሉ እንደ ደረሰላችሁ፥ አምላካችሁ እግዚአብሔር ከሰጣችሁ ከዚህች ከመልካሚቱ ምድር እናንተን እስኪያጠፋችሁ ድረስ እግዚአብሔር እንዲሁ ክፉን ነገር ሁሉ ያመጣባችኋል። |
| 16. | አምላካችሁ እግዚአብሔር ያዘዛችሁን ቃል ኪዳን ስታፈርሱ፥ ሄዳችሁም ሌሎችን አማልክት ስታመልኩ፥ ስትሰግዱላቸውም፥ በዚያ ጊዜ የእግዚአብሔር ቍጣ ይነድድባችኋል፥ ከሰጣችሁም ከመልካሚቱ ምድር ፈጥናችሁ ትጠፋላችሁ። |
| ← Joshua (23/24) → |