| ← Joshua (21/24) → |
| 1. | የሌዋውያን አባቶች አለቆች ወደ ካህኑ ወደ አልዓዛር፥ ወደ ነዌም ልጅ ወደ ኢያሱ፥ ወደ እስራኤልም ልጆች ነገዶች አለቆች ቀረቡ፤ |
| 2. | በከነዓን ምድር ባለችው በሴሎ። እግዚአብሔር በሙሴ እጅ የምንቀመጥባቸውን ከተሞች፥ ለከብቶቻችንም መሰምርያዎች ትሰጡን ዘንድ አዝዞአል ብለው ተናገሩአቸው። |
| 3. | የእስራኤልም ልጆች እንደ እግዚአብሔር ትእዛዝ ከርስታቸው እነዚህን ከተሞችና መሰምርያቸውን ለሌዋውያን ሰጡ። |
| 4. | ለቀዓትም ወገኖች ዕጣ ወጣ፤ ሌዋውያንም ለነበሩ ለካህኑ ለአሮን ልጆች ከይሁዳ ነገድ፥ ከስምዖንም ነገድ፥ ከብንያምም ነገድ አሥራ ሦስት ከተሞች በዕጣ ሆኑላቸው። |
| 5. | ለቀሩትም ለቀዓት ልጆች ከኤፍሬም ነገድ፥ ከዳንም ነገድ፥ ከምናሴም ነገድ እኩሌታ አሥር ከተሞች በዕጣ ሆኑላቸው። |
| 6. | ለጌድሶንም ልጆች ከይሳኮር ነገድ፥ ከአሴርም ነገድ፥ ከንፍታሌምም ነገድ፥ በባሳንም ካለው ከምናሴ ነገድ እኩሌታ አሥራ ሦስት ከተሞች በዕጣ ሆኑላቸው። |
| 7. | ለሜራሪም ልጆች በየወገኖቻቸው ከሮቤል ነገድ፥ ከጋድም ነገድ፥ ከዛብሎንም ነገድ አሥራ ሁለት ከተሞች ሆኑላቸው። |
| 8. | እግዚአብሔርም በሙሴ እጅ እንዳዘዘ የእስራኤል ልጆች እነዚህን ከተሞችና መሰምርያቸውን ለሌዋውያን በዕጣ ሰጡ። |
| 9. | ከይሁዳም ልጆች ነገድ ከስምዖንም ልጆች ነገድ በስማቸው የተጠሩትን እነዚህን ከተሞች ሰጡ። |
| 10. | የፊተኛው ዕጣ ለእነርሱ ስለ ወጣ የሌዊ ልጆች የቀዓት ወገን ለሆኑ ለአሮን ልጆች ሆኑ። |
| 11. | በይሁዳ ተራራማ አገር ያለችውን ቂርያትአርባቅ የምትባለውን ከተማ በዙሪያዋም ያለውን መሰምርያ ሰጡአቸው፤ እርስዋም ኬብሮን ናት፥ ይህም አርባቅ የዔናቅ አባት ነበረ። |
| 12. | የከተማይቱን እርሻ ግን መንደሮችዋንም ለዮፎኔ ልጅ ለካሌብ ርስት አድርገው ሰጡት። |
| 13. | ለካህኑም ለአሮን ልጆች እነዚህን ሰጡ፤ ለነፍሰ ገዳይ መማፀኛ ከተማ የሆነችውን ኬብሮንንና መሰምርያዋን፥ ልብናንና መሰምርያዋን፥ |
| 14. | የቲርንና መሰምርያዋን፥ ኤሽትሞዓንና መሰምርያዋን፥ |
| 15. | ሖሎንንና መሰምርያዋን፥ ዳቤርንና መሰምርያዋን፥ |
| 16. | ዓይንንና መሰምርያዋን፥ ዮጣንና መሰምርያዋን፥ ቤትሳሚስንና መሰምርያዋን፤ ከእነዚህ ከሁለቱ ነገዶች ዘጠኝ ከተሞችን ሰጡ። |
| 17. | ከብንያምም ነገድ ገባዖንንና መሰምርያዋን፥ ናሲብንና መሰምርያዋን፥ |
| 18. | አናቶትንና መሰምርያዋን፥ አልሞንንና መሰምርያዋን፤ አራት ከተሞችን ሰጡ። |
| 19. | የአሮን ልጆች የካህናት ከተሞች ከመሰምርያቸው ጋር አሥራ ሦስት ናቸው። |
| 20. | ለቀሩትም ለቀዓት ልጆች ወገኖች ሌዋውያን የዕጣቸው ከተሞች ከኤፍሬም ነገድ ደረሱአቸው። |
| 21. | በኤፍሬም ተራራማ አገር ለነፍሰ ገዳይ መማፀኛ ከተማ የሆነችውን ሴኬምንና መሰምርያዋን፥ ጌዝርንና መሰምርያዋን፥ |
| 22. | ቂብጻይምንና መሰምርያዋን፥ ቤትሖሮንንና መሰምርያዋን፤ አራቱን ከተሞች ሰጡአቸው። |
| 23. | ከዳንም ነገድ ኤልተቄንና መሰምርያዋን፥ ገባቶንንና መሰምርያዋን፥ ኤሎንንና መሰምርያዋን፥ |
| 24. | ጋትሪሞንንና መሰምርያዋን፤ አራቱን ከተሞች ሰጡአቸው። |
| 25. | ከምናሴም ነገድ እኩሌታ ታዕናክንና መሰምርያዋን፥ ጋትሪሞንንና መሰምርያዋን፤ ሁለቱን ከተሞች ሰጡአቸው። |
| 26. | የቀሩት የቀዓት ልጆች ወገኖች ከተሞች ሁሉ ከመሰምርያቸው ጋር አሥር ናቸው። |
| 27. | ለሌዋውያንም ወገኖች ለጌድሶን ልጆች ከምናሴ ነገድ እኩሌታ ለነፍሰ ገዳይ መማፀኛ ከተማ በባሳን ውስጥ የሆነችውን ጎላንንና መሰምርያዋን፥ በኤሽትራንና መሰምርያዋን፤ ሁለቱን ከተሞች ሰጡአቸው። |
| 28. | ከይሳኮርም ነገድ ቂሶንንና መሰምርያዋን፥ ዳብራትንና መሰምርያዋን፥ |
| 29. | የርሙትንና መሰምርያዋን፥ ዓይንጋኒምንና መሰምርያዋን፤ አራቱን ከተሞች ሰጡአቸው። |
| 30. | ከአሴርም ነገድ ሚሽአልንና መሰምርያዋን፥ ዓብዶንንና መሰምርያዋን፥ |
| 31. | ሔልቃትንና መሰምርያዋን፥ ረአብንና መሰምርያዋን፤ አራቱን ከተሞች ሰጡአቸው። |
| 32. | ከንፍታሌምም ነገድ ለነፍሰ ገዳይ መማፀኛ ከተማ የሆነችውን በገሊላ ውስጥ ቃዴስንና መሰምርያዋን፥ ሐሞትዶርንና መሰምርያዋን፥ ቀርታንንና መሰምርያዋን፤ ሦስቱን ከተሞች ሰጡአቸው። |
| 33. | የጌድሶን ልጆች ከተሞች ሁሉ በየወገኖቻቸው አሥራ ሦስት ከተሞች ከመሰምርያቸው ጋር ናቸው። |
| 34. | ከሌዋውያንም ለቀሩት ለሜራሪ ልጆች ወገን ከዛብሎን ነገድ ዮቅንዓምንና መሰምርያዋን፥ |
| 35. | ቀርታንና መሰምርያዋን፥ ዲሞናንና መሰምርያዋን፥ ነህላልንና መሰምርያዋን፤ አራቱን ከተሞች ሰጡ። |
| 36. | ከሮቤልም ነገድ ቦሶርንና መሰምርያዋን፥ ያሀጽንና መሰምርያዋን፥ |
| 37. | ቅዴሞትንና መሰምርያዋን፥ ሜፍዓትንና መሰምርያዋን፤ አራቱን ከተሞች ሰጡ። |
| 38. | ከጋድም ነገድ ለነፍሰ ገዳይ መማፀኛ ከተማ የሆነችውን በገለዓድ ውስጥ ራሞትንና መሰምርያዋን፥ መሃናይምንና መሰምርያዋን፥ |
| 39. | ሐሴቦንንና መሰምርያዋን፥ ኢያዜርንና መሰምርያዋን፤ አራቱን ከተሞች ሰጡ። |
| 40. | ከሌዋውያን ወገኖች የቀሩት የሜራሪ ልጆች ከተሞች ሁሉ በየወገኖቻቸው እነዚህ ነበሩ፤ ዕጣቸውም አሥራ ሁለት ከተማ ነበረ። |
| 41. | በእስራኤል ልጆች ርስት መካከል የነበሩት የሌዋውያን ከተሞች ሁሉ አርባ ስምንት ከተሞችና መሰምርያቸው ነበሩ። |
| 42. | እነዚህም ከተሞች እያንዳንዳቸው ከመሰምርያቸው ጋር ነበሩ፤ እነዚህም ከተሞች ሁሉ እንዲሁ ነበሩ። |
| 43. | እግዚአብሔርም ይሰጣቸው ዘንድ ለአባቶቻቸው የማለላቸውን ምድር ሁሉ ለእስራኤል ሰጠ፤ ወረሱአትም፥ ተቀመጡባትም። |
| 44. | እግዚአብሔርም ለአባቶቻቸው እንደ ማለላቸው በዙሪያቸው ካሉት አሳረፋቸው፤ ከጠላቶቻቸውም ሁሉ ይቋቋማቸው ዘንድ ማንም ሰው አልቻለም፤ እግዚአብሔርም ጠላቶቻቸውን ሁሉ በእጃቸው አሳልፎ ሰጣቸው። |
| 45. | እግዚአብሔር ለእስራኤል ቤት ከተናገረው መልካም ነገር ሁሉ ተፈጸመ እንጂ ምንም አልቀረም። |
| ← Joshua (21/24) → |