← Joshua (17/24) → |
1. | ለምናሴ ነገድ ዕጣ ይህ ነው፤ የዮሴፍ በኵር እርሱ ነውና። የምናሴም በኵር የገለዓድ አባት ማኪር ብርቱ ሰልፈኛ ስለ ነበረ ገለዓድንና ባሳንን ወረሰ። |
2. | ዕጣውም ለቀሩት ለምናሴ ልጆች በየወገኖቻቸው፥ ለአቢዔዝር ልጆች፥ ለኬሌግ ልጆች፥ ለአሥሪኤል ልጆች፥ ለሴኬም ልጆች፥ ለኦፌር ልጆች፥ ለሸሚዳ ልጆች ሆነ፤ የዮሴፍ ልጅ የምናሴ ወንዶች ልጆች በየወገኖቻቸው እነዚህ ናቸው። |
3. | ለምናሴ ልጅ፥ ለማኪር ልጅ፥ ለገለዓድ ልጅ፥ ለኦፌር ልጅ፥ ለሰለጰዓድ ግን ሴቶች ልጆች እንጂ ወንዶች ልጆች አልነበሩትም የሴቶች ልጆቹም ስም ማህለህ፥ ኑዓ፥ ዔግላ፥ ሚልካ፥ ቲርጻ ነበረ። |
4. | እነርሱም ወደ ካህኑ ወደ አልዓዛርና ወደ ነዌ ልጅ ወደ ኢያሱ ወደ አለቆችም ቀርበው። እግዚአብሔር በወንድሞቻችን መካከል ርስት እንዲሰጠን ሙሴን አዘዘ አሉ፤ እግዚአብሔርም እንዳዘዘ በአባታቸው ወንድሞች መካከል ርስት ሰጣቸው። |
5. | በዮርዳኖስ ማዶ ካለው ከገለዓድና ከባሳን አገር ሌላ ለምናሴ አሥር ዕጣ ሆነ፤ |
6. | የምናሴ ሴቶች ልጆች በወንዶች ልጆች መካከል ርስት ተቀብለዋልና፤ የገለዓድም ምድር ለቀሩት ለምናሴ ልጆች ሆኖአልና። |
7. | የምናሴም ድንበር ከአሴር ጀምሮ በሴኬም ፊት ልፊት እስካለው እስከ ሚክምታት ድረስ ነበረ፤ ድንበሩም በቀኝ በኩል ወደ ዓይንታጱዋ ሰዎች አለፈ። |
8. | የታጱዋ ምድር ለምናሴ ነበረ፤ በምናሴ ዳርቻ ያለው ታጱዋ ግን ለኤፍሬም ልጆች ሆነ። |
9. | ድንበሩም ወደ ቃና ወንዝ ከወንዙ በደቡብ ወገን ወረደ፤ በምናሴም ከተሞች መካከል የነበሩት እነዚህ ከተሞች ለኤፍሬም ሆኑ፤ የምናሴም ድንበር በወንዙ በኩል በሰሜን ወገን ነበረ፥ መውጫውም በባሕሩ አጠገብ ነበረ። |
10. | በደቡብ በኩል ያለው ለኤፍሬም ነበረ፥ በሰሜንም በኩል ያለው ለምናሴ ነበረ፥ ድንበሩም ባሕሩ ነበረ፤ በሰሜን በኩል ወደ አሴር፥ በምሥራቅም በኩል ወደ ይሳኮር ደረሰ። |
11. | በይሳኮርና በአሴር መካከል ቤትሳንና መንደሮችዋ፥ ይብልዓምና መንደሮችዋ፥ ዶርና የመንደሮችዋ ሰዎች፥ ዓይንዶርና የመንደሮችዋ ሰዎች፥ ታዕናክና የመንደሮችዋ ሰዎች፥ መጊዶና የመንደሮችዋ ሰዎች፥ ሦስቱ ኮረብቶች ለምናሴ ነበሩ። |
12. | የምናሴ ልጆች ግን የእነዚህን ከተሞች ሰዎች ሊያሳድዱአቸው አልቻሉም፤ ነገር ግን ከነዓናውያን በዚያ አገር በመቀመጥ ጸኑ። |
13. | የእስራኤልም ልጆች በጸኑ ጊዜ ከነዓናውያንን የጕልበት ግብር አስገበሩአቸው፥ ፈጽመውም አላሳደዱአቸውም። |
14. | የዮሴፍ ልጆች ኢያሱን። እኔ ብዙ ሕዝብ ስለ ሆንሁ እስከ አሁንም እግዚአብሔር ስለ ባረከኝ ለምን አንድ ክፍል አንድም ዕጣ ብቻ ርስት አድርገህ ሰጠኸኝ? አሉት። |
15. | ኢያሱም። ብዙ ሕዝብስ ከሆንህ ተራራማውም የኤፍሬም አገር ጠብቦህ እንደ ሆነ ወደ ዱር ወጥተህ በፌርዛውያንና በራፋይም ምድር ለአንተ ስፍራ መንጥር አላቸው። |
16. | የዮሴፍም ልጆች። ተራራማው አገር አይበቃንም፤ በሸለቆውም ውስጥ ለሚኖሩት፥ በቤትሳንና በመንደሮችዋ በኢይዝራኤልም ሸለቆ ለሚኖሩት ከነዓናውያን የብረት ሰረገሎች አላቸው አሉት። |
17. | ኢያሱም የዮሴፍ ወገን ለሚሆኑ ለኤፍሬምና ለምናሴ። አንተ ብዙ ሕዝብ ነህ፥ ጽኑም ኃይል አለህ አንድ ዕጣ ብቻ አይሆንልህም፤ |
18. | ነገር ግን ተራራማው አገር ለአንተ ይሆናል፥ ዱር እንኳን ቢሆንም ትመነጥረዋለህ፥ ለአንተም ይሆናል፤ ለከነዓናውያንም የብረት ሰረገሎች ቢሆኑላቸው የበረቱም ቢሆኑ ታሳድዳቸዋለህ አላቸው። |
← Joshua (17/24) → |