| ← Joshua (14/24) → |
| 1. | የእስራኤልም ልጆች በከነዓን ምድር የወረሱት፥ ካህኑ አልዓዛርና የነዌ ልጅ ኢያሱ የእስራኤልም ልጆች ነገድ የአባቶቻቸው አለቆች ያካፈሉአቸው ርስት ይህ ነው፤ |
| 2. | እግዚአብሔር በሙሴ እጅ እንዳዘዘ ለዘጠኙ ነገድና ለእኩሌታው በየርስታቸው በዕጣ አካፈሉአቸው። |
| 3. | ለሁለቱ ነገድና ለእኩሌታው ነገድ በዮርዳኖስ ማዶ ሙሴ ርስት ሰጥቶ ነበረ፤ ነገር ግን በመካከላቸው ለሌዋውያን ርስት አልሰጣቸውም። |
| 4. | የዮሴፍ ልጆች ምናሴና ኤፍሬም ሁለት ነገዶች ነበሩ፤ ለሌዋውያንም ከሚቀመጡባቸው ከተሞች ለእንስሶቻቸውና ለከብቶቻቸውም ከሚሆን መሰምርያቸው በቀር በምድሩ ውስጥ ድርሻ አልሰጡአቸውም። |
| 5. | እግዚአብሔር ሙሴን እንዳዘዘ እንዲሁ የእስራኤል ልጆች አደረጉ፥ ምድሪቱንም ተካፈሉ። |
| 6. | የይሁዳም ልጆች በጌልገላ ወደ ኢያሱ ቀረቡ፤ ቄኔዛዊውም የዮፎኒ ልጅ ካሌብ አለው። ለአምላክህ ሰው ለሙሴ ስለ እኔና ስለ አንተ እግዚአብሔር በቃዴስ በርኔ የተናገረውን ነገር ታውቃለህ። |
| 7. | የእግዚአብሔር ባሪያ ሙሴ ምድርን እሰልል ዘንድ ከቃዴስ በርኔ በላከኝ ጊዜ እኔ የአርባ ዓመት ሰው ነበርሁ እኔም በልቤ የነበረውን ቃል መለስሁለት። |
| 8. | ከእኔ ጋር የወጡ ወንድሞቼ ግን የሕዝቡን ልብ አቀለጡ፤ እኔ ግን አምላኬን እግዚአብሔርን ፈጽሜ ተከተልሁ። |
| 9. | ሙሴም በዚያ ቀን። አምላኬን እግዚአብሔርን ፈጽመህ ተከትለሃልና እግርህ የረገጠው ምድር ለአንተና ለልጆችህ ለዘላለም በእርግጥ ርስት ይሆናል ብሎ ማለ። |
| 10. | አሁንም፥ እነሆ፥ እግዚአብሔር ለሙሴ ይህን ቃል ከተናገረ በኋላ፥ እስራኤል በምድረ በዳ ሲዞሩ፥ እርሱ እንደ ተናገረኝ እግዚአብሔር እነዚህን አርባ አምስት ዓመት በሕይወት አኖረኝ፤ አሁንም፥ እነሆ፥ ለእኔ ዛሬ ሰማንያ አምስት ዓመት ሆነኝ። |
| 11. | ሙሴም በላከኝ ጊዜ እንደ ነበርሁ፥ ዛሬ ጕልበታም ነኝ፤ ጕልበቴም በዚያን ጊዜ እንደ ነበረ፥ እንዲሁ ዛሬ ለመዋጋት ለመውጣትም ለመግባትም ጉልበቴ ያው ነው። |
| 12. | አሁን እንግዲህ በዚያን ቀን እግዚአብሔር የተናገረውን ይህን ተራራማ አገር ስጠኝ፤ አንተ በዚያ ቀን ዔናቃውያን ታላላቆችና የተመሸጉ ከተሞችም በዚያ እንዳሉ ሰምተህ ነበር፤ ምናልባት እግዚአብሔር ከእኔ ጋር ይሆናል፥ እግዚአብሔርም እንደ ተናገረኝ አሳድዳቸዋለሁ። |
| 13. | ኢያሱም ባረከው፤ ለዮፎኒም ልጅ ለካሌብ ኬብሮንን ርስት አድርጎ ሰጠው። |
| 14. | ስለዚህም የእስራኤልን አምላክ እግዚአብሔርን ፈጽሞ ስለ ተከተለ ኬብሮን እስከ ዛሬ ለቄኔዛዊው ለዮፎኒ ልጅ ለካሌብ ርስት ሆነች። |
| 15. | የኬብሮንም ስም አስቀድሞ ቂርያትአርባቅ ትባል ነበር፤ ይህም አርባቅ በዔናቅ ሰዎች መካከል ከሁሉ ከፍ ያለ ነበረ። ምድሪቱም ከውጊያ ዐረፈች። a |
| ← Joshua (14/24) → |