← Joshua (11/24) → |
1. | እንዲህም ሆነ፤ የአሶር ንጉሥ ኢያቢስ ይህን በሰማ ጊዜ ወደ ማዶን ንጉሥ ወደ ዮባብ፥ ወደ ሺምሮንም ንጉሥ፥ ወደ አዚፍም ንጉሥ፥ |
2. | በሰሜንም በተራራማው አገር፥ በኪኔሬትም ደቡብ በዓረባ፥ በቈላውም፥ በምዕራብም በኩል ባለ በዶር ኮረብታ ወደ ነበሩ ነገሥታት፥ |
3. | በምሥራቅና በምዕራብም ወዳለው ወደ ከነዓናዊው፥ ወደ አሞራዊውም፥ ወደ ኬጢያዊውም፥ ወደ ፌርዛዊውም፥ በተራራማውም አገር ወዳለው ወደ ኢያቡሳዊው፥ ከአርሞንዔምም በታች በምጽጳ ወዳለው ወደ ኤዊያዊው ላከ። |
4. | እነዚህም ከሠራዊቶቻቸው ሁሉ ከእጅግም ብዙ ፈረሰኞችና ሠረገሎች ጋር ወጡ፤ በባሕር ዳርም እንዳለ አሸዋ ብዙ ሕዝብ ነበረ። |
5. | እነዚህም ነገሥታት ሁሉ ተሰብስበው እስራኤልን ለመውጋት መጥተው በማሮን ውኃ አጠገብ አንድ ሆነው ሰፈሩ። |
6. | እግዚአብሔርም ኢያሱን። ነገ በዚህ ጊዜ ሁሉን እንደ ሞቱ አድርጌ በእስራኤል እጅ አሳልፌ እሰጣቸዋለሁና አትፍራቸው፤ የፈረሶቻቸውንም ቋንጃ ትቈርጣለህ፥ ሰረገሎቻቸውንም በእሳት ታቃጥላለህ አለው። |
7. | ኢያሱም ከሰልፈኞቹ ሁሉ ጋር በድንገት ወደ ማሮን ውኃ መጣባቸው፥ ወደቀባቸውም። |
8. | እግዚአብሔርም በእስራኤል እጅ አሳልፎ ሰጣቸው፤ መቱአቸውም፥ ወደ ታላቂቱም ሲዶና፥ ወደ ማሴሮንም፥ በምሥራቅም በኩል ወዳለው ወደ ምጽጳ ሸለቆ አሳደዱአቸው፤ ማንንም ሳያስቀሩ መቱአቸው። |
9. | ኢያሱም እግዚአብሔር እንዳዘዘው አደረገባቸው፤ የፈረሶቻቸውንም ቋንጃ ቈረጠ፥ ሰረገሎቻቸውንም በእሳት አቃጠለ። |
10. | በዚያን ጊዜም ኢያሱ ተመልሶ አሶርን ያዘ፥ ንጉሥዋንም በሰይፍ ገደለ፤ አሶርም አስቀድሞ የእነዚህ መንግሥታት ዋና ከተማ ነበረች። |
11. | በእርስዋም ያሉትን ነፍሳት ሁሉ በሰይፍ ስለት ገደሉ፥ ፈጽመውም አጠፉአቸው፤ እስትንፋስ ያለውንም አላስቀሩም፤ አሶርንም በእሳት አቃጠላት። |
12. | የእግዚአብሔርም ባሪያ ሙሴ እንዳዘዘው፥ ኢያሱ የእነዚህን ነገሥታት ከተሞች ሁሉ፥ ነገሥታቶቻቸውንም ሁሉ ያዘ፥ በሰይፍም ስለት መታቸው፥ ፈጽሞም አጠፋቸው። |
13. | እስራኤልም በኮረብቶቹ ላይ የነበሩትን ከተሞች ሁሉ አላቃጠሉም፤ ነገር ግን እስራኤል አሶርን ብቻ አቃጠሉአት። |
14. | የእስራኤልም ልጆች የእነዚህን ከተሞች ምርኮ ሁሉ ከብቶቹንም ለራሳቸው ዘረፉ፤ ሰዎቹን ሁሉ ግን እስኪጠፉ ድረስ በሰይፍ ስለት መቱአቸው፥ እስትንፋስ ያለውንም ሁሉ አላስቀሩም። |
15. | እግዚአብሔርም ባሪያውን ሙሴን እንዳዘዘው እንዲሁ ሙሴ ኢያሱን አዝዞት ነበር፥ ኢያሱም እንዲሁ አደረገ፤ እግዚአብሔር ሙሴን ካዘዘው ሁሉ ምንም አላስቀረም። |
16. | ኢያሱም ያን ምድር ሁሉ፥ ተራራማውን፥ ደቡቡንም ሁሉ፥ የጎሶምንም ምድር ሁሉ፥ ቈላውንም፥ ዓረባንም፥ የእስራኤልንም ተራራማውንና ቈላውን ያዘ፥ |
17. | እስከ ሴይርም ከሚያወጣው ወና ከሆነው ተራራ ጀምሮ ከአርሞንዔም ተራራ በታች በሊባኖስም ሸለቆ ውስጥ እስካለው እስከ በኣልጋድ ድረስ፤ ነገሥታቶቻቸውንም ሁሉ ይዞ መታቸው፥ ገደላቸውም። |
18. | ኢያሱም ብዙ ዘመን ከእነዚህ ነገሥታት ሁሉ ጋር ይዋጋ ነበር። |
19. | በገባዖን ከሚኖሩ ከኤዊያውያን በቀር ከእስራኤል ልጆች ጋር ዕርቅ ያደረገች አንዲት ከተማ አልነበረችም፤ ሁሉን በሰልፍ ያዙ። |
20. | እግዚአብሔር ሙሴን እንዳዘዘ፥ ያጠፉአቸው ዘንድ ሞገስንም እንዳያገኙ ፈጽመውም እንዲያጠፉአቸው፥ ከእስራኤል ጋር ይጋጠሙ ዘንድ ልባቸውን እንዲያደነድኑ ከእግዚአብሔር ዘንድ ሆነ። |
21. | በዚያን ጊዜም ኢያሱ መጣ፥ ከተራራማውም አገር ከኬብሮንም ከዳቤርም ከአናብም ከእስራኤልም ተራራማ ሁሉ ከይሁዳም ተራራማ ሁሉ የዔናቅን ልጆች ገደለ፤ ኢያሱም ከከተሞቻቸው ጋር ፈጽሞ አጠፋቸው። |
22. | በጋዛ በጌትም በአዛጦንም ጥቂቶች ቀሩ እንጂ በእስራኤል ልጆች ምድር ከዔናቅ ልጆች ማንም አልቀረም። |
23. | እግዚአብሔርም ለሙሴ እንደ ነገረው ሁሉ ኢያሱ ምድሪቱን ሁሉ ያዘ፤ ኢያሱም ለእስራኤል እንደ ክፍላቸውና እንደ ነገዳቸው ርስት አድርጎ ምድሪቱን ሰጣቸው፤ ምድሪቱም ከሰልፍ ዐረፈች። |
← Joshua (11/24) → |