← Joshua (10/24) → |
1. | እንዲህም ሆነ፤ የኢየሩሳሌም ንጉሥ አዶኒጼዴቅ ኢያሱ ጋይን እንደ ያዘ ፈጽሞም እንዳጠፋት፥ በኢያሪኮና በንጉሥዋም ያደረገውን እንዲሁ በጋይና በንጉሥዋ እንዳደረገ፥ የገባዖንም ሰዎች ከእስራኤል ጋር ሰላም እንዳደረጉ በመካከላቸውም እንደ ሆኑ በሰማ ጊዜ፥ |
2. | ገባዖን ከመንግሥታት ከተሞች እንደ አንዲቱ ታላቅ ከተማ ስለ ሆነች፥ ከጋይም ስለ በለጠች፥ ሰዎችዋም ሁሉ ኃያላን ስለ ነበሩ፥ እጅግ ፈራ። |
3. | ስለዚህም የኢየሩሳሌም ንጉሥ አዶኒጼዴቅ ወደ ኬብሮን ንጉሥ ወደ ሆሃም፥ ወደ የርሙት ንጉሥም ወደ ጲርአም፥ ወደ ለኪሶ ንጉሥም ወደ ያፊዓ፥ ወደ አዶላም ንጉሥም ወደ ዳቤር ልኮ። ወደ እኔ ውጡ፥ |
4. | ከኢያሱና ከእስራኤልም ልጆች ጋር ሰላም አድርገዋልና ገባዖንን ለመምታት አግዙኝ አለ። |
5. | አምስቱም የአሞራውያን ነገሥታት፥ የኢየሩሳሌም ንጉሥ፥ የኬብሮን ንጉሥ፥ የየርሙት ንጉሥ፥ የለኪሶ ንጉሥ፥ የአዶላም ንጉሥ፥ ከሠራዊቶቻቸው ሁሉ ጋር ተሰብስበው ወጡ፥ ከገባዖንም ጋር ሊጋጠሙ ከበቡአት። |
6. | የገባዖንም ሰዎች ኢያሱ ወደ ሰፈረበት ወደ ጌልገላ ልከው። ባሪያዎችህን ለመርዳት እጅህን አትመልስ፤ በተራራማው አገር የሚኖሩ የአሞራውያን ነገሥታት ሁሉ ተሰብስበውብናልና ፈጥነህ ወደ እኛ ውጣ አድነንም እርዳንም አሉት። |
7. | ኢያሱም ከእርሱም ጋር የነበሩ ሰልፈኞች ሁሉ ጽኑዓን ኃያላኑም ሁሉ ከጌልገላ ወጡ። |
8. | እግዚአብሔርም ኢያሱን። በእጅህ አሳልፌ ሰጥቼአቸዋለሁና አትፍራቸው፤ ከእነርሱም አንድ ሰው የሚቋቋምህ የለም አለው። |
9. | ኢያሱም ከጌልገላ ሌሊቱን ሁሉ ገሥግሦ በድንገት መጣባቸው። |
10. | እግዚአብሔርም በእስራኤል ፊት አስደነገጣቸው፤ በገባዖንም ታላቅ መምታት መታቸው፥ በቤትሖሮንም ዐቀበት በመንገድ አሳደዳቸው፥ እስከ ዓዜቃና እስከ መቄዳ ድረስ መታቸው። |
11. | ከእስራኤልም ልጆች ፊት እየሸሹ በቤትሖሮን ቍልቍለት ሲወርዱ፥ ወደ ዓዜቃ እስኪደርሱ ድረስ እግዚአብሔር ከሰማይ ታላላቅ የበረዶ ድንጋይ አወረደባቸውና ሞቱ፤ የእስራኤል ልጆች በሰይፍ ከገደሉአቸው ይልቅ በበረዶ ድንጋይ የሞቱት በለጡ። |
12. | እግዚአብሔርም በእስራኤል ልጆች እጅ አሞራውያንን አሳልፎ በሰጠ ቀን ኢያሱ እግዚአብሔርን ተናገረ፤ በእስራኤልም ፊት እንዲህ አለ። በገባዖን ላይ ፀሐይ ትቁም፥ በኤሎንም ሸለቆ ጨረቃ፤ |
13. | ሕዝቡም ጠላቶቻቸውን እስኪበቀሉ ድረስ ፀሐይ ቆመ፥ ጨረቃም ዘገየ። ይህስ በያሻር መጽሐፍ የተጻፈ አይደለምን? ፀሐይም በሰማይ መካከል ዘገየ፥ አንድ ቀንም ሙሉ ያህል ለመግባት አልቸኰለም። |
14. | እግዚአብሔር ለእስራኤል ይዋጋ ነበርና እግዚአብሔር የሰውን ቃል የሰማበት እንደዚያ ያለ ቀን ከዚያም በፊት ከዚያም በኋላ አልነበረም። |
15. | ኢያሱም ከእርሱም ጋር እስራኤል ሁሉ ወደ ሰፈራቸው ወደ ጌልገላ ተመለሱ። |
16. | እነዚህም አምስት ነገሥታት ሸሽተው በመቄዳ ዋሻ ተሸሸጉ። |
17. | ለኢያሱም። አምስቱ ነገሥታት በመቄዳ ዋሻ ተሸሽገው ተገኙ ብለው ነገሩት። |
18. | ኢያሱም እንዲህ አለ። ወደ ዋሻው አፍ ታላላቅ ድንጋይ አንከባልላችሁ፥ ይጠብቁአቸው ዘንድ ሰዎችን በዚያ አኑሩ፤ |
19. | እናንተ ግን አትዘግዩ፥ ጠላቶቻችሁንም አባርሩአቸው፥ በኋላም ያሉትን ግደሉ፤ አምላካችሁም እግዚአብሔር በእጃችሁ አሳልፎ ሰጥቶአቸዋልና ወደ ከተሞቻቸው እንዳይገቡ ከልክሉአቸው አለ። |
20. | እስኪጠፉም ድረስ ኢያሱና የእስራኤል ልጆች በታላቅ መምታት መምታታቸውን በፈጸሙ ጊዜ፥ ከእነርሱም ያመለጡት ወደ ተመሸገ ከተማ በገቡ ጊዜ፥ |
21. | ሕዝብ ሁሉ ኢያሱ ወደ ሰፈረበት ወደ መቄዳ በደኅና ተመለሱ፤ በእስራኤል ልጆች ላይ ምላሱን ማንቀሳቀስ የደፈረ ማንም ሰው የለም። |
22. | ኢያሱም። የዋሻውን አፍ ክፈቱ፥ እነዚያንም አምስት ነገሥታት ከዋሻው ወደ እኔ አውጡአቸው አለ። |
23. | እንዲህም አደረጉ፤ አምስቱንም ነገሥታት፥ የኢየሩሳሌምን ንጉሥ የኬብሮንንም ንጉሥ የየርሙትንም ንጉሥ የለኪሶንም ንጉሥ የኦዶላምንም ንጉሥ፥ ከዋሻው ወደ እርሱ አወጡአቸው። |
24. | እነዚያንም ነገሥታት ወደ ኢያሱ ባወጡአቸው ጊዜ ኢያሱ የእስራኤልን ሰዎች ሁሉ ጠራ፥ ከእርሱም ጋር የሄዱትን የሰልፈኞች አለቆች። ቅረቡ፥ በእነዚህም ነገሥታት አንገት ላይ እግራችሁን አኑሩ አላቸው። ቀረቡም በአንገታቸውም ላይ እግራቸውን አኖሩ። |
25. | ኢያሱም። እግዚአብሔር በምትወጉአቸው በጠላቶቻችሁ ሁሉ ላይ እንዲሁ ያደርጋልና አትፍሩ፥ አትደንግጡ፤ ጽኑ፥ አይዞአችሁ አላቸው። |
26. | ከዚህም በኋላ መትተው ገደሉአቸው፥ በአምስቱም ዛፎች ላይ ሰቀሉአቸው፤ እስከ ማታም ድረስ በዛፎቹ ተሰቅለው ቈዩ። |
27. | ፀሐይም ልትገባ በቀረበች ጊዜ ኢያሱ አዘዘ፥ ከዛፎችም አወረዱአቸው፥ ተሸሽገውም በነበሩበት ዋሻ ጣሉአቸው፥ እስከ ዛሬም ድረስ በዋሻው አፍ ታላላቅ ድንጋይ ተደርጎአል። |
28. | በዚያም ቀን ኢያሱ መቄዳን ያዛት፥ እርስዋንና ንጉሥዋንም በሰይፍ ስለት መታ፤ በእርስዋም ያሉትን ነፍሳት ሁሉ ፈጽሞ አጠፋቸው፥ ከእነርሱም አንዱን ስንኳ አላስቀረም፤ በኢያሪኮም ንጉሥ እንዳደረገ በመቄዳ ንጉሥ አደረገ። |
29. | ኢያሱም ከእርሱም ጋር እስራኤል ሁሉ ከመቄዳ ወደ ልብና አለፉ፥ ልብናንም ወጉ። |
30. | እግዚአብሔርም እርስዋንና ንጉሥዋን በእስራኤል እጅ አሳልፎ ሰጠ፤ እርስዋንም በእርስዋም ያሉትን ነፍሳት ሁሉ በሰይፍ ስለት መታ፥ በእርስዋም አንዱን ስንኳ አላስቀረም፤ በኢያሪኮም ንጉሥ እንዳደረገው በልብና ንጉሥ አደረገ። |
31. | ኢያሱም ከእርሱም ጋር እስራኤል ሁሉ ከልብና ወደ ለኪሶ አለፉ፥ ከበቡአትም፥ ወጉአትም። |
32. | እግዚአብሔርም ለኪሶን በእስራኤል እጅ አሳልፎ ሰጣት፥ በሁለተኛውም ቀን ያዙአት፤ በልብናም እንዳደረጉት ሁሉ፥ እርስዋን በእርስዋም ያሉትን ነፍሳት ሁሉ በሰይፍ ስለት መቱአቸው። |
33. | በዚያን ጊዜም የጌዝር ንጉሥ ሆራም ለኪሶን ለመርዳት ወጣ፤ ኢያሱም አንድ ስንኳ ሳይቀር እርሱንና ሕዝቡን መታ። |
34. | ኢያሱም ከእርሱም ጋር እስራኤል ሁሉ ከለኪሶ ወደ ኦዶላም አለፉ፥ ከበቡአትም፥ ወጉአትም፤ |
35. | በዚያም ቀን ያዙአት፥ በሰይፍም ስለት መቱአት፤ በለኪሶም እንዳደረገው ሁሉ፥ በእርስዋ ያሉትን ነፍሳት ሁሉ በዚያ ቀን ፈጽሞ አጠፋ። |
36. | ኢያሱም ከእርሱም ጋር እስራኤል ሁሉ ከኦዶላም ወደ ኬብሮን ወጡ፥ ወጉአትም፥ ያዙአትም፤ |
37. | እርስዋንም ንጉሥዋንም ከተሞችዋንም ሁሉ በእርስዋም ያሉትን ነፍሳት ሁሉ በሰይፍ ስለት መቱ፤ በኦዶላም እንዳደረገው ሁሉ ማንንም አላስቀረም፤ እርስዋንም በእርስዋም ያሉትን ነፍሳት ሁሉ ፈጽሞ አጠፋ። |
38. | ኢያሱም ከእርሱም ጋር እስራኤል ሁሉ ወደ ዳቤር ተመለሱ፥ ወጉአትም፥ |
39. | እርስዋንም ንጉሥዋንም ከተሞችዋንም ያዙ፤ በሰይፍም ስለት መቱአቸው፥ በእነርሱም ውስጥ ያሉትን ነፍሳት ሁሉ ፈጽመው አጠፉ፤ ማንንም አላስቀረም፤ በኬብሮን፥ ደግሞ በልብናና በንጉሥዋ እንዳደረገው እንዲሁ በዳቤርና በንጉሥዋ አደረገ። |
40. | እንዲሁም ኢያሱ ምድሪቱን ሁሉ ተራራማውን አገር ደቡቡንም ቈላውንም ቍልቍለቱንም ነገሥታቶቻቸውንም ሁሉ መታ፤ ማንንም አላስቀረም፤ የእስራኤል አምላክ እግዚአብሔር እንዳዘዘውም ነፍስ ያለበትን ሁሉ ፈጽሞ አጠፋ። |
41. | ኢያሱም ከቃዴስ በርኔ እስከ ጋዛ ድረስ የጎሶምንም ምድር ሁሉ እስከ ገባዖን ድረስ መታ። |
42. | የእስራኤልም አምላክ እግዚአብሔር ለእስራኤል ስለ ተዋጋላቸው ኢያሱ እነዚህን ነገሥታት ሁሉ ምድራቸውንም በአንድ ጊዜ ያዘ። |
43. | ኢያሱም ከእርሱም ጋር እስራኤል ሁሉ ወደ ሰፈሩ ወደ ጌልገላ ተመለሱ። a |
← Joshua (10/24) → |