| ← John (9/21) → |
| 1. | ሲያልፍም ከመወለዱ ጀምሮ ዕውር የሆነውን ሰው አየ። |
| 2. | ደቀ መዛሙርቱም። መምህር ሆይ፥ ይህ ሰው ዕውር ሆኖ እንዲወለድ ኃጢአት የሠራ ማን ነው? እርሱ ወይስ ወላጆቹ? ብለው ጠየቁት። |
| 3. | ኢየሱስም እንዲህ ብሎ መለሰ። የእግዚአብሔር ሥራ በእርሱ እንዲገለጥ ነው እንጂ እርሱ ወይም ወላጆቹ ኃጢአት አልሠሩም። |
| 4. | ቀን ሳለ የላከኝን ሥራ ላደርግ ይገባኛል፤ ማንም ሊሠራ የማይችልባት ሌሊት ትመጣለች። |
| 5. | በዓለም ሳለሁ የዓለም ብርሃን ነኝ። |
| 6. | ይህን ብሎ ወደ መሬት እንትፍ አለ በምራቁም ጭቃ አድርጎ በጭቃው የዕውሩን ዓይኖች ቀባና። |
| 7. | ሂድና በሰሊሆም መጠመቂያ ታጠብ አለው፤ ትርጓሜው የተላከ ነው። ስለዚህ ሄዶ ታጠበ እያየም መጣ። |
| 8. | ጐረቤቶቹም ቀድሞም ሲለምን አይተውት የነበሩ። ይህ ተቀምጦ ይለምን የነበረ አይደለምን? አሉ። |
| 9. | ሌሎች። እርሱ ነው አሉ፤ ሌሎች። አይደለም እርሱን ይመስላል እንጂ አሉ፤ እርሱ። እኔ ነኝ አለ። |
| 10. | ታድያ። ዓይኖችህ እንዴት ተከፈቱ? አሉት። |
| 11. | እርሱ መልሶ። ኢየሱስ የሚባለው ሰው ጭቃ አድርጎ አይኖቼን ቀባና። ወደ ሰሊሆም መጠመቂያ ሄደህ ታጠብ አለኝ፤ ሄጄ ታጥቤም አየሁ አለ። |
| 12. | ያ ሰው ወዴት ነው? አሉት። አላውቅም አለ። |
| 13. | በፊት ዕውር የነበረውን ሰው ወደ ፈሪሳውያን ወሰዱት። |
| 14. | ኢየሱስም ጭቃ አድርጎ ዓይኖቹን የከፈተበት ቀን ሰንበት ነበረ። |
| 15. | ስለዚህ ፈሪሳውያን ደግሞ እንዴት እንዳየ እንደ ገና ጠየቁት። እርሱም። ጭቃ በዓይኖቼ አኖረ ታጠብሁም አያለሁም አላቸው። |
| 16. | ከፈሪሳውያንም አንዳንዶቹ። ይህ ሰው ሰንበትን አያከብርምና ከእግዚአብሔር አይደለም አሉ። ሌሎች ግን። ኃጢአትኛ ሰው እንደነዚህ ያሉ ምልክቶች ሊያደርግ እንዴት ይችላል? አሉ። |
| 17. | በመካከላቸውም መለያየት ሆነ። ከዚህም የተነሣ ዕውሩን። አንተ ዓይኖችህን ስለ ከፈተ ስለ እርሱ ምን ትላለህ? ደግሞ አሉት። እርሱም። ነቢይ ነው አለ። |
| 18. | አይሁድ የዚያን ያየውን ወላጆች እስኪጠሩ ድረስ ዕውር እንደ ነበረ እንዳየም ስለ እርሱ አላመኑም፥ |
| 19. | እነርሱንም። እናንተ ዕውር ሆኖ ተወለደ የምትሉት ልጃችሁ ይህ ነውን? ታድያ አሁን እንዴት ያያል? ብለው ጠየቁአቸው። |
| 20. | ወላጆቹም መልሰው። ይህ ልጃችን እንደ ሆነ ዕውርም ሆኖ እንደ ተወለደ አናውቃለን፤ |
| 21. | ዳሩ ግን አሁን እንዴት እንዳየ አናውቅም፥ ወይም ዓይኖቹን ማን እንደ ከፈተ እኛ አናውቅም፤ ጠይቁት እርሱ ሙሉ ሰው ነው፤ እርሱ ስለ ራሱ ይናገራል አሉ። |
| 22. | ወላጆቹ አይሁድን ስለ ፈሩ ይህን አሉ፤ እርሱ ክርስቶስ ነው ብሎ የሚመሰክር ቢኖር ከምኵራብ እንዲያወጡት አይሁድ ከዚህ በፊት ተስማምተው ነበርና። |
| 23. | ስለዚህ ወላጆቹ። ሙሉ ሰው ነው፥ ጠይቁት አሉ። |
| 24. | ስለዚህ ዕውር የነበረውን ሰው ሁለተኛ ጠርተው። እግዚአብሔርን አክብር፤ ይህ ሰው ኃጢአተኛ መሆኑን እኛ እናውቃለን አሉት። |
| 25. | እርሱም መልሶ። ኃጢአተኛ መሆኑን አላውቅም፤ ዕውር እንደ ነበርሁ አሁንም እንዳይ ይህን አንድ ነገር አውቃለሁ አለ። |
| 26. | ደግመውም። ምን አደረገልህ? እንዴትስ ዓይኖችህን ከፈተ? አሉት። |
| 27. | እርሱም መልሶ። አስቀድሜ ነገርኋችሁ አልሰማችሁምም፤ ስለ ምን ዳግመኛ ልትሰሙ ትወዳላችሁ? እናንተ ደግሞ ደቀ መዛሙርቱ ልትሆኑ ትወዳላችሁን? አላቸው። |
| 28. | ተሳድበውም። አንተ የእርሱ ደቀ መዝሙር ነህ፥ እኛ ግን የሙሴ ደቀ መዛሙርት ነን፤ |
| 29. | እግዚአብሔር ሙሴን እንደ ተናገረው እኛ እናውቃለን፥ ይህ ሰው ግን ከወዴት እንደ ሆነ አናውቅም አሉት። |
| 30. | ሰውዬው መለሰ እንዲህም አላቸው። ከወዴት እንደ ሆነ እናንተ አለማወቃችሁ ይህ ድንቅ ነገር ነው፥ ዳሩ ግን ዓይኖቼን ከፈተ። |
| 31. | እግዚአብሔርን የሚፈራ ፈቃዱንም የሚያደርግ ቢኖር ያንን እግዚአብሔር ይሰማዋል እንጂ ኃጢአተኞችን እንዳይሰማ እናውቃለን። |
| 32. | ዕውር ሆኖ የተወለደውን ዓይኖች ማንም እንደ ከፈተ ዓለም ከተፈጠረ ጀምሮ አልተሰማም፤ |
| 33. | ይህ ሰው ከእግዚአብሔር ባይሆን ምንም ሊያደርግ ባልቻለም ነበር። |
| 34. | መልሰው። አንተ ሁለንተናህ በኃጢአት ተወለድህ፥ አንተም እኛን ታስተምረናለህን? አሉት። ወደ ውጭም አወጡት። |
| 35. | ኢየሱስም ወደ ውጭ እንዳወጡት ሰማ ሲያገኘውም። አንተ በእግዚአብሔር ልጅ ታምናለህን? አለው። |
| 36. | እርሱም መልሶ። ጌታ ሆይ፥ በእርሱ አምን ዘንድ ማን ነው? አለ። |
| 37. | ኢየሱስም። አይተኸዋልም ከአንተ ጋርም የሚናገረው እርሱ ነው አለው። |
| 38. | እርሱም። ጌታ ሆይ፥ አምናለሁ አለ፤ ሰገደለትም። |
| 39. | ኢየሱስም። የማያዩ እንዲያዩ የሚያዩም እንዲታወሩ እኔ ወደዚህ ዓለም ለፍርድ መጣሁ አለ። |
| 40. | ከፈሪሳውያንም ከእርሱ ጋር የነበሩት ይህን ሰምተው። እኛ ደግሞ ዕውሮች ነንን? አሉት። |
| 41. | ኢየሱስም አላቸው። ዕውሮችስ ብትሆኑ ኃጢአት ባልሆነባችሁም ነበር፤ አሁን ግን። እናያለን ትላላችሁ፤ ኃጢአታችሁ ይኖራል። |
| ← John (9/21) → |