| ← John (8/21) → | 
| 1. | ኢየሱስ ግን ወደ ደብረ ዘይት ሄደ። | 
| 2. | ማለዳም ደግሞ ወደ መቅደስ ደረሰ ሕዝቡም ሁሉ ወደ እርሱ መጡ። ተቀምጦም ያስተምራቸው ነበር። | 
| 3. | ጻፎችና ፈሪሳውያንም በምንዝር የተያዘችን ሴት ወደ እርሱ አመጡ በመካከልም እርሱዋን አቁመው። | 
| 4. | መምህር ሆይ፥ ይህች ሴት ስታመነዝር ተገኝታ ተያዘች። | 
| 5. | ሙሴም እንደነዚህ ያሉት እንዲወገሩ በሕግ አዘዘን፤ አንተስ ስለ እርስዋ ምን ትላለህ? አሉት። | 
| 6. | የሚከሱበትንም እንዲያገኙ ሊፈትኑት ይህን አሉ። ኢየሱስ ግን ጐንበስ ብሎ በጣቱ በምድር ላይ ጻፈ፤ | 
| 7. | መላልሰው በጠየቁት ጊዜ ግን ቀና ብሎ። ከእናንተ ኃጢአት የሌለበት አስቀድሞ በድንጋይ ይውገራት አላቸው። | 
| 8. | ደግሞም ጐንበስ ብሎ በጣቱ በምድር ላይ ጻፈ። | 
| 9. | እነርሱም ይህን ሲሰሙ ሕሊናቸው ወቀሳቸውና ከሽማግሌዎች ጀምረው እስከ ኋለኞች አንድ አንድ እያሉ ወጡ፤ ኢየሱስም ብቻውን ቀረ ሴቲቱም በመካከል ቆማ ነበረች። | 
| 10. | ኢየሱስም ቀና ብሎ ከሴቲቱ በቀር ማንንም ባላየ ጊዜ። አንቺ ሴት፥ እነዚያ ከሳሾችሽ ወዴት አሉ? የፈረደብሽ የለምን? አላት። | 
| 11. | እርስዋም። ጌታ ሆይ፥ አንድ ስንኳ አለች። ኢየሱስም። እኔም አልፈርድብሽም፤ ሂጂ ከአሁንም ጀምሮ ደግመሽ ኃጢአት አትሥሪ አላት። | 
| 12. | ደግሞም ኢየሱስ። እኔ የዓለም ብርሃን ነኝ፤ የሚከተለኝ የሕይወት ብርሃን ይሆንለታል እንጂ በጨለማ አይመላለስም ብሎ ተናገራቸው። | 
| 13. | ፈሪሳውያንም። አንተ ስለ ራስህ ትመሰክራለህ፤ ምስክርነትህ እውነት አይደለም አሉት። | 
| 14. | ኢየሱስ መለሰ አላቸውም። እኔ ስለ ራሴ ምንም እንኳ ብመሰክር ከወዴት እንደመጣሁ ወዴትም እንድሄድ አውቃለሁና ምስክርነቴ እውነት ነው፤ እናንተ ግን ከወዴት እንደ መጣሁ ወዴትም እንድሄድ አታውቁም። | 
| 15. | እናንተ ሥጋዊ ፍርድን ትፈርዳላችሁ፤ እኔ በአንድ ሰው ስንኳ አልፈርድም። | 
| 16. | የላከኝ አብ ከእኔ ጋር ነው እንጂ ብቻዬን አይደለሁምና እኔ ብፈርድ ፍርዴ እውነት ነው። | 
| 17. | የሁለት ሰዎችም ምስክርነት እውነት እንደ ሆነ በሕጋችሁ ተጽፎአል። | 
| 18. | ስለ ራሴ የምመሰክር እኔ ነኝ፥ የላከኝም አብ ስለ እኔ ይመሰክራል። | 
| 19. | እንግዲህ። አባትህ ወዴት ነው? አሉት። ኢየሱስ መልሶ። እኔንም ወይም አባቴንም አታውቁም፤ እኔንስ ብታውቁኝ አባቴን ደግሞ ባወቃችሁ ነበር አላቸው። | 
| 20. | ኢየሱስ በመቅደስ ሲያስተምር በግምጃ ቤት አጠገብ ይህን ነገር ተናገረ፤ ጊዜው ገና አልደረሰምና ማንም አልያዘውም። | 
| 21. | ኢየሱስም ደግሞ። እኔ እሄዳለሁ ትፈልጉኛላችሁም በኃጢአታችሁም ትሞታላችሁ እኔ ወደምሄድበት እናንተ ልትመጡ አትችሉም አላቸው። | 
| 22. | አይሁድም። እኔ ወደ ምሄድበት እናንተ ልትመጡ አትችሉም ማለቱ ራሱን ይገድላልን? እንጃ አሉ። | 
| 23. | እናንተ ከታች ናችሁ፥ እኔ ከላይ ነኝ፤ እናንተ ከዚህ ዓለም ናችሁ፥ እኔ ከዚህ ዓለም አይደለሁም። | 
| 24. | እንግዲህ። በኃጢአታችሁ ትሞታላችሁ አልኋችሁ፤ እኔ እንደሆንሁ ባታምኑ በኃጢአታችሁ ትሞታላችሁና አላቸው። | 
| 25. | እንግዲህ። አንተ ማን ነህ? አሉት። ኢየሱስም። ከመጀመሪያ ለእናንተ የተናገርሁት ነኝ። | 
| 26. | ስለ እናንተ የምናገረው የምፈርደውም ብዙ ነገር አለኝ፤ ዳሩ ግን የላከኝ እውነተኛ ነው እኔም ከእርሱ የሰማሁትን ይህን ለዓለም እናገራለሁ አላቸው። | 
| 27. | ስለ አብ እንደ ነገራቸው አላስተዋሉም። | 
| 28. | ስለዚህም ኢየሱስ። የሰውን ልጅ ከፍ ከፍ ባደረጋችሁት ጊዜ እኔ እሆን ዘንድ አባቴም እንዳስተማረኝ እነዚህን እናገር ዘንድ እንጂ ከራሴ አንዳች እንዳላደርግ በዚያን ጊዜ ታውቃላችሁ። | 
| 29. | የላከኝም ከእኔ ጋር ነው፤ እኔ ደስ የሚያሰኘውን ዘወትር አደርጋለሁና አብ ብቻዬን አይተወኝም አላቸው። | 
| 30. | ይህን ሲናገር ብዙዎች በእርሱ አመኑ። | 
| 31. | ኢየሱስም ያመኑትን አይሁድ። እናንተ በቃሌ ብትኖሩ በእውነት ደቀ መዛሙርቴ ናችሁ፤ | 
| 32. | እውነትንም ታውቃላችሁ እውነትም አርነት ያወጣችኋል አላቸው። | 
| 33. | እነርሱም መልሰው። የአብርሃም ዘር ነን ለአንድም ስንኳ ከቶ ባሪያዎች አልሆንም፤ አንተ። አርነት ትወጣላችሁ እንዴት ትላለህ? አሉት። | 
| 34. | ኢየሱስ መለሰ፥ እንዲህ ሲል። እውነት እውነት እላችኋለሁ፥ ኃጢአት የሚያደርግ ሁሉ የኃጢአት ባርያ ነው። | 
| 35. | ባርያም ለዘላለም በቤት አይኖርም፤ ልጁ ለዘላለም ይኖራል። | 
| 36. | እንግዲህ ልጁ አርነት ቢያወጣችሁ በእውነት አርነት ትወጣላችሁ። | 
| 37. | የአብርሃም ዘር መሆናችሁንስ አውቃለሁ ነገር ግን ቃሌ በእናንተ አይኖርምና ልትገድሉኝ ትፈልጋላችሁ። | 
| 38. | እኔ በአባቴ ዘንድ ያየሁትን እናገራለሁ፤ እናንተም ደግሞ በአባታችሁ ዘንድ ያያችሁትን ታደርጋላችሁ። | 
| 39. | መልሰውም። አባታችንስ አብርሃም ነው አሉት። ኢየሱስም። የአብሃም ልጆች ብትሆኑ የአብርሃምን ሥራ ባደረጋችሁ ነበር። | 
| 40. | ነገር ግን አሁን ከእግዚእብሔር የሰማሁትን እውነት የነገርኋችሁን ሰው ልትገድሉኝ ትፈልጋላችሁ፤ አብርሃም እንዲህ አላደረገም። | 
| 41. | እናንተ የአባታችሁን ሥራ ታደርጋላችሁ አላቸው። እኛስ ከዝሙት አልተወለድንም አንድ አባት አለን እርሱም እግዚአብሔር ነው አሉት። | 
| 42. | ኢየሱስም አላቸው። እግዚአብሔርስ አባታችሁ ከሆነ በወደዳችሁኝ ነበር፤ እኔ ከእግዚአብሔር ወጥቼ መጥቻለሁና፤ እርሱ ላከኝ እንጂ ከራሴ አልመጣሁምና። | 
| 43. | ንግግሬን የማታስተውሉ ስለ ምንድር ነው? ቃሌን ልትሰሙ ስለማትችሉ ነው። | 
| 44. | እናንተ ከአባታችሁ ከዲያብሎስ ናችሁ የአባታችሁንም ምኞት ልታደርጉ ትወዳላችሁ። እርሱ ከመጀመሪያ ነፍሰ ገዳይ ነበረ፤ እውነትም በእርሱ ስለ ሌለ በእውነት አልቆመም። ሐሰትን ሲናገር ከራሱ ይናገራል፥ ሐሰተኛ የሐሰትም አባት ነውና። | 
| 45. | እኔ ግን እውነትን የምናገር ስለ ሆንሁ አታምኑኝም። | 
| 46. | ከእናንተ ስለ ኃጢአት የሚወቅሰኝ ማን ነው? እውነት የምናገር ከሆንሁ እናንተ ስለ ምን አታምኑኝም? | 
| 47. | ከእግዚአብሔር የሆነ የእግዚአብሔርን ቃል ይሰማል፤ እናንተ ከእግዚአብሔር አይደላችሁምና ስለዚህ አትሰሙም። | 
| 48. | አይሁድ መልሰው። ሳምራዊ እንደ ሆንህ ጋኔንም እንዳለብህ በማለታችን እኛ መልካም እንል የለምን? አሉት። | 
| 49. | ኢየሱስም መለሰ፥ እንዲህ ሲል። እኔስ ጋኔን የለብኝም ነገር ግን አባቴን አከብራለሁ እናንተም ታዋርዱኛላችሁ። | 
| 50. | እኔ ግን የራሴን ክብር አልፈልግም፤ የሚፈልግ የሚፈርድም አለ። | 
| 51. | እውነት እውነት እላችኋለሁ፥ ቃሌን የሚጠብቅ ቢኖር ለዘላለም ሞትን አያይም። | 
| 52. | አይሁድ። ጋኔን እንዳለብህ አሁን አወቅን። አብርሃም ስንኳ ሞተ ነቢያትም፤ አንተም። ቃሌን የሚጠብቅ ቢኖር ለዘላለም ሞትን አይቀምስም ትላለህ። | 
| 53. | በእውኑ አንተ ከሞተው ከአባታችን ከአብርሃም ትበልጣለህን? ነቢያትም ሞቱ፤ ራስህን ማንን ታደርጋለህ? አሉት። | 
| 54. | ኢየሱስም መለሰ አለም። እኔ ራሴን ባከብር ክብሬ ከንቱ ነው፤ የሚያከብረኝ እናንተ አምላካችን የምትሉት አባቴ ነው፤ | 
| 55. | አላወቃችሁትምም፥ እኔ ግን አውቀዋለሁ። አላውቀውም ብል እንደ እናንተ ሐሰተኛ በሆንሁ፤ ዳሩ ግን አውቀዋለሁ ቃሉንም እጠብቃለሁ። | 
| 56. | አባታችሁ አብርሃም ቀኔን ያይ ዘንድ ሐሤት አደረገ፥ አየም ደስም አለው። | 
| 57. | አይሁድም። ገና አምሳ ዓመት ያልሆነህ አብርሃምን አይተሃልን? አሉት። | 
| 58. | ኢየሱስም። እውነት እውነት እላችኋለሁ፥ አብርሃም ሳይወለድ እኔ አለሁ አላቸው። | 
| 59. | ስለዚህ ሊወግሩት ድንጋይ አነሡ፤ ኢየሱስ ግን ተሰወራቸው ከመቅደስም ወጥቶ በመካከላቸው አልፎ ሄደ። | 
| ← John (8/21) → |