| ← John (19/21) → |
| 1. | በዚያን ጊዜም ጲላጦስ ኢየሱስን ይዞ ገረፈው። |
| 2. | ወታደሮችም ከእሾህ አክሊል ጐንጕነው በራሱ ላይ አኖሩ ቀይ ልብስም አለበሱት፤ |
| 3. | እየቀረቡም። የአይሁድ ንጉሥ ሆይ፥ ሰላም ለአንተ ይሁን ይሉት ነበር፤ |
| 4. | በጥፊም ይመቱት ነበር። ጲላጦስም ደግሞ ወደ ውጭ ወጥቶ። እነሆ፥ አንዲት በደል ስንኳ እንዳላገኘሁበት ታውቁ ዘንድ እርሱን ወደ ውጭ አወጣላችኋለሁ አላቸው። |
| 5. | ኢየሱስም የእሾህ አክሊል ደፍቶ ቀይ ልብስም ለብሶ ወደ ውጭ ወጣ። |
| 6. | ጲላጦስም። እነሆ ሰውዬው አላቸው። የካህናት አለቆችና ሎሌዎች ባዩትም ጊዜ። ስቀለው ስቀለው እያሉ ጮኹ። ጲላጦስም። እኔስ አንዲት በደል ስንኳ አላገኘሁበትምና እናንተ ወስዳችሁ ስቀሉት አላቸው። |
| 7. | አይሁድም መልሰው። እኛ ሕግ አለን፥ እንደ ሕጋችንም ሊሞት ይገባዋል፥ ራሱን የእግዚአብሔር ልጅ አድርጎአልና አሉት። |
| 8. | ስለዚህ ጲላጦስ ይህን ነገር በሰማ ጊዜ እግጅ ፈራ፤ |
| 9. | ተመልሶም ወደ ገዡ ግቢ ገባና ኢየሱስን። አንተ ከወዴት ነህ? አለው። ኢየሱስ ግን አንድ እንኳ አልመለሰለትም። |
| 10. | ስለዚህ ጲላጦስ። አትነግረኝምን? ልሰቅልህ ሥልጣን እንዳለኝ ወይም ልፈታህ ሥልጣን እንዳለኝ አታውቅምን? አለው። |
| 11. | ኢየሱስም መልሶ። ከላይ ካልተሰጠህ በቀር በእኔ ላይ ምንም ሥልጣን ባልነበረህም፤ ስለዚህ ለአንተ አሳልፎ የሰጠኝ ኃጢአቱ የባሰ ነው አለው። |
| 12. | ከዚህ በኋላ ጲላጦስ ሊፈታው ፈለገ፤ ነገር ግን አይሁድ። ይህንስ ብትፈታው የቄሣር ወዳጅ አይደለህም፤ ራሱን ንጉሥ የሚያደርግ ሁሉ የቄሣር ተቃዋሚ ነው እያሉ ጮኹ። |
| 13. | ጲላጦስም ይህን ነገር ሰምቶ ኢየሱስን ወደ ውጭ አወጣው፥ በዕብራይስጥም ገበታ በተባለው ጸፍጸፍ በሚሉት ስፍራ በፍርድ ወንበር ተቀመጠ። |
| 14. | ለፋሲካም የማዘጋጀት ቀን ነበረ፤ ስድስት ሰዓትም የሚያህል ነበረ፤ አይሁድንም። እነሆ ንጉሣችሁ አላቸው። |
| 15. | እነርሱ ግን። አስወግደው፥ አስወግደው፥ ስቀለው እያሉ ጮኹ። ጲላጦስም። ንጉሣችሁን ልስቀለውን? አላቸው። የካህናት አለቆችም። ከቄሣር በቀር ሌላ ንጉሥ የለንም ብለው መለሱለት። |
| 16. | ስለዚህ በዚያን ጊዜ እንዲሰቀል አሳልፎ ሰጣቸው። |
| 17. | ኢየሱስንም ይዘው ወሰዱት፤ መስቀሉንም ተሸክሞ በዕብራይስጥ ጎልጎታ ወደ ተባለው የራስ ቅል ስፍራ ወደሚሉት ወጣ። |
| 18. | በዚያም ሰቀሉት፥ ከእርሱም ጋር ሌሎች ሁለት፥ አንዱን በዚህ አንዱን በዚያ ኢየሱስንም በመካከላቸው ሰቀሉ። |
| 19. | ጲላጦስም ደግሞ ጽሕፈት ጽፎ በመስቀሉ ላይ አኖረው፤ ጽሕፈቱም። የአይሁድ ንጉሥ የናዝሬቱ ኢየሱስ የሚል ነበረ። |
| 20. | ኢየሱስም የተሰቀለበት ስፍራ ለከተማ ቅርብ ነበረና ከአይሁድ ብዙዎች ይህን ጽሕፈት አነበቡት፤ በዕብራይስጥና በሮማይስጥ በግሪክም ተጽፎ ነበር። |
| 21. | ስለዚህ የአይሁድ ካህናት አለቆች ጲላጦስን። እርሱ። የአይሁድ ንጉስ ነኝ እንዳለ እንጂ የአይሁድ ንጉሥ ብለህ አትጻፍ አሉት። |
| 22. | ጲላጦስም። የጻፍሁትን ጽፌአለሁ ብሎ መለሰ። |
| 23. | ጭፍሮችም ኢየሱስን በሰቀሉት ጊዜ ልብሶቹን ወስደው ለእያንዳንዱ ጭፍራ አንድ ክፍል ሆኖ በአራት ከፋፈሉት፤ እጀጠባቡን ደግሞ ወሰዱ። እጀ ጠባቡም ከላይ ጀምሮ ወጥ ሆኖ የተሠራ ነበረ እንጂ የተሰፋ አልነበረም። |
| 24. | ስለዚህ እርስ በርሳቸው። ለማን እንዲሆን በእርሱ ዕጣ እንጣጣልበት እንጂ አንቅደደው ተባባሉ። ይህም። ልብሴን እርስ በርሳቸው ተከፋፈሉ በእጀ ጠባቤም ዕጣ ተጣጣሉበት የሚለው የመጽሐፍ ቃል ይፈጸም ዘንድ ነው። |
| 25. | ጭፍሮችም እንዲህ አደረጉ። ነገር ግን በኢየሱስ መስቀል አጠገብ እናቱ፥ የእናቱም እኅት፥ የቀለዮጳም ሚስት ማርያም፥ መግደላዊትም ማርያም ቆመው ነበር። |
| 26. | ኢየሱስም እናቱን ይወደው የነበረውንም ደቀ መዝሙር በአጠገቡ ቆሞ ባየ ጊዜ እናቱን። አንቺ ሴት፥ እነሆ ልጅሽ አላት። |
| 27. | ከዚህ በኋላ ደቀ መዝሙሩን። እናትህ እነኋት አለው። ከዚህም ሰዓት ጀምሮ ደቀ መዝሙሩ ወደ ቤቱ ወሰዳት። |
| 28. | ከዚህ በኋላ ኢየሱስ አሁን ሁሉ እንደተፈጸመ አውቆ የመጽሐፉ ቃል ይፈጸም ዘንድ። ተጠማሁ አለ። |
| 29. | በዚያም ሆምጣጤ የሞላበት ዕቃ ተቀምጦ ነበር፤ እነርሱም ሆምጣጤውን በሰፍነግ ሞልተው በሁሶፕም አድርገው ወደ አፉ አቀረቡለት። |
| 30. | ኢየሱስም ሆምጣጤውን ከተቀበለ በኋላ። ተፈጸመ አለ፥ ራሱንም አዘንብሎ ነፍሱን አሳልፎ ሰጠ። |
| 31. | አይሁድም የማዘጋጀት ቀን ስለ ሆነ ያ ሰንበት ትልቅ ነበረና ሥጋቸው በሰንበት በመስቀል ላይ እንዳይኖር፥ ጭናቸውን ሰብረው እንዲያወርዱአቸው ጲላጦስን ለመኑት። |
| 32. | ጭፍሮችም መጥተው የፊተኛውን ጭን ከእርሱም ጋር የተሰቀለውን የሌላውን ጭን ሰበሩ፤ |
| 33. | ወደ ኢየሱስ በመጡ ጊዜ ግን እርሱ ፈጽሞ እንደ ሞተ አይተው ጭኑን አልሰበሩም፤ |
| 34. | ነገር ግን ከጭፍሮች አንዱ ጎኑን በጦር ወጋው፤ ወዲያውም ደምና ውኃ ወጣ። |
| 35. | ያየውም መስክሮአል፤ ምስክሩም እውነት ነው፤ እናንተም ደግሞ ታምኑ ዘንድ እርሱ እውነት እንዲናገር ያውቃል። |
| 36. | ይህ የሆነ። ከእርሱ አጥንት አይሰበርም የሚል የመጽሐፉ ቃል እንዲፈጸም ነው። |
| 37. | ደግሞም ሌላው መጽሐፍ። የወጉትን ያዩታል ይላል። |
| 38. | ከዚህም በኋላ አይሁድን ስለ ፈራ በስውር የኢየሱስ ደቀ መዝሙር የነበረ የአርማትያስ ዮሴፍ የኢየሱስን ሥጋ ሊወስድ ጲላጦስን ለመነ፤ ጲላጦስም ፈቀደለት። ስለዚህም መጥቶ የኢየሱስን ሥጋ ወሰደ። |
| 39. | ደግሞም አስቀድሞ በሌሊት ወደ ኢየሱስ መጥቶ የነበረ ኒቆዲሞስ መቶ ንጥር የሚያህል የከርቤና የእሬት ቅልቅል ይዞ መጣ። |
| 40. | የኢየሱስንም ሥጋ ወስደው እንደ አይሁድ አገናነዝ ልማድ ከሽቱ ጋር በተልባ እግር ልብስ ከፈኑት። |
| 41. | በተሰቀለበትም ስፍራ አትክልት ነበረ፥ በአትክልቱም ማንም ገና ያልተቀበረበት አዲስ መቃብር ነበረ። |
| 42. | ስለዚህ መቃብሩ ቅርብ ነበረና ስለ አይሁድ ማዘጋጀት ቀን ኢየሱስን በዚያ አኖሩት። |
| ← John (19/21) → |