| ← Joel (3/3) |
| 1. | እነሆም፥ በዚህ ወራትና በዚህ ዘመን፥ የይሁዳንና የኢየሩሳሌምን ምርኮ በምመልስበት ጊዜ፥ |
| 2. | አሕዛብን ሁሉ ሰብስቤ ወደ ኢዮሣፍጥ ሸለቆ አወርዳቸዋለሁ፤ በዚያም ስለ ሕዝቤና ስለ ርስቴ ስለ እስራኤል በአሕዛብ መካከል የበተኑአቸውን ምድሬንም የተካፈሉአትን እፋረድባቸዋለሁ። |
| 3. | በሕዝቤም ላይ ዕጣ ተጣጣሉ፤ ወንድ ልጅን ለጋለሞታ ዋጋ ሰጡ፥ ሴት ልጅን ለወይን ጠጅ ሸጡ፥ ጠጡም። |
| 4. | ጢሮስና ሲዶና የፍልስጥኤምም ግዛት ሁሉ ሆይ፥ ከእናንተ ጋር ለእኔ ምን አለኝ? በውኑ ብድራትን ትመልሱልኛላችሁን? ብድራትን ብትመልሱልኝ ፈጥኜ በችኰላ ብድራታችሁን በራሳችሁ ላይ እመልሳለሁ። |
| 5. | ብሬንና ወርቄን ወስዳችኋልና፥ የተወደደውንም መልካሙን ዕቃዬን ወደ መቅደሳችሁ አግብታችኋልና፥ |
| 6. | ከዳርቻቸውም ታርቁአቸው ዘንድ የይሁዳንና የኢየሩሳሌምን ልጆች ለግሪክ ሰዎች ሸጣችኋልና፥ |
| 7. | እነሆ፥ እነርሱን ከሸጣችሁበት ስፍራ አስነሣቸዋለሁ፥ ብድራታችሁንም በራሳችሁ ላይ እመልሳለሁ። |
| 8. | እግዚአብሔር ተናግሮአልና ወንዶችና ሴቶች ልጆቻችሁን በይሁዳ ልጆች እጅ እሸጣለሁ፥ እነርሱም ለሩቆቹ ሕዝብ ለሳባ ሰዎች ይሸጡአችኋል። |
| 9. | ይህን በአሕዛብ መካከል አውጁ ለሰልፍ ተዘጋጁ ኃያላንን አስነሡ ሰልፈኞች ሁሉ ይቅረቡ ይውጡም። |
| 10. | ማረሻችሁን ሰይፍ፥ ማጭዳችሁንም ጦር ለማድረግ ቀጥቅጡ፤ ደካማውም። እኔ ብርቱ ነኛ ይበል። |
| 11. | እናንተ በዙሪያ ያላችሁ አሕዛብ ሁሉ፥ ቸkWlaችሁ ኑ፥ ተሰብሰቡ፤ አቤቱ፥ ኃያላኖችህን ወደዚያ አውርድ። |
| 12. | አሕዛብ ይነሡ፥ ወደ ኢዮሣፍጥ ሸለቆም ይውጡ፤ በዙሪያ ባሉ አሕዛብ ሁሉ ላይ እፈርድ ዘንድ በዚያ እቀመጣለሁና። |
| 13. | መከሩ ደርሶአልና ማጭድ ስደዱ መጥመቂያውም ሞልቶአልና ኑ እርገጡ፤ ክፉታቸውም በዝቶአልና መጥመቂያ ሁሉ ፈርሶአል። |
| 14. | የእግዚአብሔር ቀን በፍርድ ሸለቆ ቀርቦአልና የብዙ ብዙ ሕዝብ ውካታ በፍርድ ሸለቆ አለ። |
| 15. | ፀሐይና ጨረቃ ጨልመዋል፥ ከዋክብትም ብርሃናቸውን ሰውረዋል። |
| 16. | እግዚአብሔርም በጽዮን ሆኖ ድምፁን ከፍ አድርጎ ይጮኻል፥ በኢየሩሳሌምም ሆኖ ቃሉን ይሰጣል፤ ሰማይና ምድርም ይናወጣሉ፤ እግዚአብሔር ግን ለሕዝቡ መሸሸጊያ፥ ለእስራኤልም ልጆች መጠጊያ ይሆናል። |
| 17. | እኔም በተቀደሰው ተራራዬ በጽዮን የምቀመጥ አምላካችሁ እግዚአብሔር እንደ ሆንሁ ታውቃላችሁ፤ የዚያን ጊዜም ኢየሩሳሌም የተቀደሰች ትሆናለች፥ እንግዶችም ከእንግዲህ ወዲህ አያልፉባትም። |
| 18. | በዚያም ቀን እንዲህ ይሆናል፤ ተራሮች በተሃ ጠጅ ያንጠባጥባሉ፥ ኮረብቶችም ወተትን ያፈስሳሉ፥ በይሁዳም ያሉት ፈፋዎች ሁሉ ውኃን ያጐርፋሉ ከእግዚአብሔርም ቤት ምንጭ ትፈልቃለች፥ የሰጢምንም ሸለቆ ታጠጣለች። |
| 19. | በአገራቸው ንጹሑን ደም አፍስሰዋልና በይሁዳ ልጆች ላይ ስላደረጉት ግፍ ግብጽ ምድረ በዳ፥ ኤዶምያስም በረሃ ይሆናል። |
| 20. | ነገር ግን ይሁዳ ለዘላለም፥ ኢየሩሳሌምም ለልጅ ልጅ መኖሪያ ይሆናል። |
| 21. | እኔም ንጹሕ ያላደረግሁትን ደማቸውን ንጹሕ አደርገዋለሁ፥ እግዚአብሔርም በጽዮን ያድራል። |
| ← Joel (3/3) |