| Joel (1/3) → |
| 1. | ወደ ባቱኤል ልጅ ወደ ኢዩኤል የመጣው የእግዚአብሔር ቃል ይህ ነው። |
| 2. | እናንተ ሽማግሌዎች፥ ይህን ስሙ፤ በምድርም የምትኖሩ ሁሉ፥ አድምጡ። ይህ በዘመናችሁ ወይስ በአባቶቻችሁ ዘመን ሆኖ ነበርን? |
| 3. | ይህን ለልጆቻችሁ ንገሩ፤ ልጆቻችሁም ለልጆቻቸው፥ ልጆቻቸውም ለኋለኛው ትውልድ ይንገሩ። |
| 4. | ከተሞች የቀረውን አንበጣ በላው፤ ከአንበጣም የቀረውን ደጎብያ በላው፤ ከደጎብያም የቀረውን ኩብኩባ በላው። |
| 5. | በተሃ ወይን ጠጃችሁ ከአፋችሁ ተወግዶአልና እናንተ ሰካራሞች፥ ነቅታችሁ አልቅሱ፤ እናንተም የወይን ጠጅ የምትጠጡ ሁሉ፥ ዋይ በሉ። |
| 6. | ቍጥርም የሌለው ብርቱ ሕዝብ በምድሬ ላይ ወጥቶአልና፤ ጥርሳቸው እንደ አንበሳ ጥርስ፥ መንጋጋቸውም እንደ እንስቲቱ አንበሳ መንጋጋ ነው። |
| 7. | ወይኔን ባዶ ምድር አደረገው፥ በለሴንም ሰበረው፤ ባዶም አደረገው፥ ጣለውም፤ ቅርንጫፎቹም ነጡ። |
| 8. | ለቍንጅናዋ ባል ማቅ ለብሳ እንደምታለቅስ ድንግል አልቅሺ። |
| 9. | የእህሉ ቍርባንና የመጠጡ ቍርባን ከእግዚአብሔር ቤት ተወግዶአል፤ የእግዚአብሔርም አገልጋዮች ካህናቱ አለቀሱ። |
| 10. | እህሉ ጠፍቶአልና፥ ወይኑም ደርቆአልና፥ ዘይቱም ጐድሎአልና እርሻው ምድረ በዳ ሆኖአል፥ ምድሪቱም አልቅሳለች። |
| 11. | መከሩ ከእርሻቸው ጠፍቶአልና ገበሬዎች ስለ ስንዴውና ስለ ገብሱ አፈሩ፤ የወይን አትክልተኞችም አለቀሱ። |
| 12. | ወይኑ ደርቆአል፥ በለሱም ጠውልጎአል፤ ሮማኑና ተምሩ እንኰዩም የምድርም ዛፎች ሁሉ ደርቀዋል፤ ደስታም ከሰው ልጆች ዘንድ ርቆአል። |
| 13. | የእህሉ ቍርባንና የመጠጡ ቍርባን ከአምላካችሁ ቤት ቀርቶአልና እናንተ ካህናት፥ ማቅ ታጥቃችሁ አልቅሱ፤ እናንተም የመሠዊያ አገልጋዮች፥ ዋይ በሉ፤ እናንተ የአምላኬ አገልጋዮች፥ ኑ፥ ሌሊቱን ሁሉ በማቅ ላይ ተኙ። |
| 14. | ጾምን ቀድሱ፥ ጉባኤውንም አውጁ፤ ሽምግሌዎችንና በምድር የሚኖሩትን ሁሉ ወደ አምላካችሁ ወደ እግዚአብሔር ቤት ሰብስቡ፥ ወደ እግዚአብሔርም ጩኹ። |
| 15. | የእግዚአብሔር ቀን ቀርቦአልና ለቀኑ ወዮ! እርሱም ሁሉን ከሚችል ከአምላክ ዘንድ እንደ ጥፋት ይመጣል። |
| 16. | ከዓይናችን ፊት ምግብ፥ ከአምላካችንም ቤት ደስታና እልልታ የጠፋ አይደለምን? |
| 17. | ዘሩ በምድር ውስጥ በሰበሰ፤ እህሉ ደርቆአልና ጎተራዎቹ ባዶ ናቸው፥ ጎታዎቹም ፈርሰዋል። |
| 18. | እንስሶች እጅግ ጮኹ፤ የላምም መንጎች ማሰማርያ የላቸውምና ተጠራጠሩ፤ የበግም መንጎች ጠፍተዋል። |
| 19. | አቤቱ፥ እሳት የምድረ በዳውን ማሰማርያ በልቶአልና፥ ነበልባሉም የዱሩን ዛፍ ሁሉ አቃጥሎአልና ወደ አንተ እጮኻለሁ። |
| 20. | ፈሳሹ ውኃ ደርቆአልና፥ እሳቱም የምድረ በዳውን ማሰማርያ በልቶአልና የምድር አራዊት ወደ አንተ አለኸለኩ። |
| Joel (1/3) → |