Job (8/42)  

1. ሹሐዊውም በልዳዶስ መለሰ እንዲህም አለ።
2. እስከ መቼ ይህን ትናገራለህ? የአፍህስ ቃል እስከ መቼ እንደ ዐውሎ ነፋስ ይሆናል?
3. በውኑ እግዚአብሔር ፍርድን ያጣምማልን? ሁሉንም የሚችል አምላክ ጽድቅን ያጣምማልን?
4. ልጆችህ በድለውት እንደ ሆነ፥ እርሱ በበደላቸው እጅ ጥሎአቸዋል።
5. እግዚአብሔርን ብትገሠግሥ፥ ሁሉንም የሚችለውን አምላክ ብትለምን፥
6. ንጹሕና ቅን ብትሆን፥ በእውነት አሁን ስለ አንተ ይነቃል፥ የጽድቅህንም መኖሪያ ያከናውንልሃል።
7. ጅማሬህ ታናሽ ቢሆንም እንኳ ፍጻሜህ እጅግ ይበዛል።
9. ዘመናችን በምድር ላይ እንደ ጥላ ነውና እኛ የትናንት ብቻ ነን፤ ምንም አናውቅም፤ ስለዚህ የቀደመውን ትውልድ ጠይቅ፥ አባቶቻቸውም ለመረመሩት ነገር ትጋ፤
10. እነርሱ የሚያስተምሩህና የሚነግሩህ፥ ቃልንም ከልባቸው የሚያወጡ አይደሉምን?
11. በውኑ ደንገል ረግረግ በሌለበት መሬት ይበቅላልን? ወይስ ቄጠማ ውኃ በሌለበት ቦታ ይለመልማልን?
12. ገና ሲለመልም ሳይቈረጥም፥ ከአትክልት ሁሉ በፊት ይደርቃል።
13. እግዚአብሔርን የሚረሱ ሁሉ ፍጻሜአቸው እንዲሁ ነው፤ የዝንጉም ሰው ተስፋ ይጠፋል።
14. ተስፋው ይቈረጣል፥ እምነቱም እንደ ሸረሪት ቤት ይሆናል።
15. ቤቱን ይደግፈዋል፥ አይቆምለትም፤ ይይዘውማል፥ አይጸናለትም።
16. ፀሐይም ሳይተኵስ ይለመልማል፥ ጫፉም በአታክልቱ ቦታ ይወጣል።
17. በድንጋይ ክምር ላይ ሥሩ ይጠመጠማል፤ የድንጋዮቹን ቦታ ይመለከታል።
18. ከቦታው ቢጠፋ። አላየሁህም ብሎ ይክደዋል።
19. እነሆ፥ የመንገዱ ደስታ እንዲህ ነው፤ ሌሎችም ከመሬት ይበቅላሉ።
20. እነሆ፥ እግዚአብሔር ፍጹሙን ሰው አይጥለውም፥ የኃጢአተኞችንም እጅ አያበረታም።
21. አፍህን እንደ ገና ሳቅ ይሞላል፥ ከንፈሮችህንም እልልታ ይሞላል።
22. የሚጠሉህ እፍረት ይለብሳሉ፤ የኃጢአተኞችም ድንኳን አይገኝም።

  Job (8/42)