| ← Job (6/42) → |
| 1. | ኢዮብም መለሰ እንዲህም አለ። |
| 2. | ትካዜዬ ምነው በተመዘነ ኖሮ! መከራዬም ሁሉ ምነው በሚዛን ላይ በተደረገ ኖሮ! |
| 3. | ከባሕር አሸዋ ይልቅ ይከብድ ነበርና፤ ስለዚህ ቃሌ ደፋር ሆኖአል። |
| 4. | ሁሉን የሚችል የአምላክ ፍላጻ በሥጋዬ ውስጥ ነው፥ መርዙንም ነፍሴ ትጠጣለች፤ የእግዚአብሔር ድንጋጤ በላዬ ተሰልፎአል። |
| 5. | በውኑ የሜዳ አህያ ሣር ሳለው ይጮኻልን? ወይስ በሬ ገለባ ሳለው ይጮኻልን? |
| 6. | የማይጣፍጥስ ነገር ያለ ጨው ይበላልን? ወይስ የእንቁላል ውኃ ይጥማልን? |
| 7. | ሰውነቴ ትነካው ዘንድ እንቢ አለችው፤ እንደሚያስጸይፍ መብል ሆነብኝ። |
| 8. | ልመናዬ ምነው በደረሰልኝ! እግዚአብሔርም ምኞቴን ምነው በሰጠኝ! |
| 9. | እግዚአብሔርም ያደቀኝ ዘንድ እጁንም ለቅቆ ያጠፋኝ ዘንድ ወድዶ ቢሆን ኖሮ! |
| 10. | መጽናናት በሆነልኝ ነበር፤ በማይራራ ሕመም ሐሤት ባደረግሁ ነበር፥ የቅዱሱን ቃል አልካድሁምና። |
| 11. | እጠብቅ ዘንድ ጕልበቴ ምንድር ነው? እታገሥም ዘንድ ፍጻሜዬ ምንድር ነው? |
| 12. | ጕልበቴ የድንጋይ ጕልበት ነውን? ሥጋዬስ እንደ ናስ ነውን? |
| 13. | በውኑ ረድኤት በእኔ እንደሌለ ጥበብም ሁሉ ከእኔ ዘንድ እንደ ተባረረ አይደለምን? |
| 14. | ሁሉን የሚችለውን የአምላክን መፍራት ለሚተው፥ ለመዛል ለቀረበው ስንኳ ወዳጁ ቸርነትን ሊያሳይ ይገባል። |
| 15. | ወንድሞቼ እንደ ፈፋ፥ እንደሚያልፍ ፈፋ ሐሰተኞች ሆኑብኝ። |
| 16. | ከበረዶ የተነሣ ደፈረሱ፥ አመዳይም ተሰወረባቸው፤ |
| 17. | ፀሐይ በተኰሰች ጊዜ ይደርቃሉ፤ በሙቀትም ጊዜ ከስፍራቸው ይጠፋሉ። |
| 18. | በየዳርቻቸውም የሚሄዱ ነጋዴዎች ፈቀቅ ይላሉ፤ ወደ በረሃ ወጥተው ይጠፋሉ። |
| 19. | የቴማን ነጋዴዎች ተመለከቱ፥ የሳባ መንገደኞችም ተጠባበቁአቸው። |
| 20. | ተስፋ አድርገዋቸው ነበርና አፈሩ፤ ወደዚያ ደረሱ፥ እፍረትም ያዛቸው። |
| 21. | አሁንም እናንተ እንደዚሁ ሆናችኋል፤ መከራዬን አይታችሁ ፈራችሁ። |
| 22. | በውኑ። አንዳች ነገር አምጡልኝ፤ ወይስ። ከብልጥግናችሁ ስጦታ አቅርቡልኝ፤ |
| 23. | ወይስ። ከጠላቴ እጅ አስጥሉኝ፤ ወይስ። ከአስጨናቂው እጅ አድኑኝ አልኋችሁን? |
| 24. | አስተምሩኝ፥ እኔም ዝም እላለሁ፤ የተሳሳትሁትንም ንገሩኝ። |
| 25. | የቅንነት ቃል እንዴት ኃይለኛ ነው! የእናንተ ሙግት ግን ምን ይገሥጻል? |
| 26. | ተስፋ የሌለው ሰው ንግግር እንደ ነፋስ ነውና ቃሌን ትገሥጹ ዘንድ ታስባላችሁን? |
| 27. | በድሀ አደጉ ላይ ዕጣ ትጣጣላላችሁ፤ ለወዳጆቻችሁም ጕድጓድ ትቈፍራላችሁ። |
| 28. | አሁንም፥ እባካችሁ፥ ወደ እኔ ተመልከቱ፤ በፊታችሁም ሐሰት አልናገርም። |
| 29. | እባካችሁ፥ ተመለሱ፤ በደል አይሁን፤ ጽድቄ በዚህ ነገር ነውና አንድ ጊዜ ተመለሱ። |
| 30. | በውኑ በአንደበቴ በደል ይገኛልን? አፌስ ተንኰልን ይለይ ዘንድ አይችልምን? |
| ← Job (6/42) → |