Job (5/42)  

1. አሁንም ጥራ፤ የሚመልስልህ አለን? ከቅዱሳንስ ወደማናቸው ትዞራለህ?
2. ሰነፉን ሰው ቍጣ ይገድለዋል፥ ሰነፉንም ቅንዓት ያጠፋዋል።
3. ሰነፍ ሰው ሥር ሰድዶ አየሁት፥ ድንገትም መኖሪያውን ረገምሁ።
4. ልጆቹም ከደኅንነት ርቀዋል፥ በበርም ውስጥ ተረግጠዋል፥ የሚታደጋቸውም የለም።
5. የሰበሰበውንም ራብተኛ ይበላዋል፥ ከእሾህም ውስጥ እንኳ ያወጣዋል፤ የተጠማ ሀብታቸውን ዋጠ።
6. ችግር ከትቢያ አይመጣም፥ መከራም ከመሬት አይበቅልም፤
7. የአሞራ ግልገሎች ግን ወደ ላይ እየበረሩ ከፍ እንዲሉ፥ ሰው እንዲሁ ለመከራ ተወልዶአል።
8. እኔ ግን እግዚአብሔርን እለምን ነበር፥ ነገሬንም ወደ እግዚአብሔር አቀርብ ነበር።
9. የማይመረመረውን ታላቅ ነገርና የማይቈጠረውን ተአምራት ያደርጋል።
10. በምድር ላይ ዝናብን ይሰጣል፥ በእርሻም ላይ ውኃ ይልካል።
11. የተዋረዱትን ወደ ላይ ያወጣል፥ ኀዘንተኞችንም ለደኅንነት ከፍ ከፍ ያደርጋቸዋል።
12. እጃቸውም ምክራቸውን እንዳይፈጽም የተንኰለኞችን አሳብ ከንቱ ያደርገዋል።
13. ጠቢባንን በተንኰላቸው ይይዛቸዋል፤ የጠማሞችንም ምክር ይዘረዝራል።
14. በቀን ጨለማን ያገኛሉ፥ በቀትርም ጊዜ በሌሊት እንዳሉ ይርመሰመሳሉ።
15. ድሀውንም ከአፋቸው ሰይፍ ከኃያሉም እጅ ያድነዋል።
16. ለምስኪኑም ተስፋ አለው፤ ክፋት ግን አፍዋን ትዘጋለች።
17. እነሆ፥ እግዚአብሔር የሚገሥጸው ሰው ምስጉን ነው፤ ስለዚህ ሁሉን የሚችለውን የአምላክን ተግሣጽ አትናቅ።
18. እርሱ ይሰብራል፥ ይጠግንማል፤ ያቈስላል፥ እጆቹም ይፈውሳሉ።
19. በስድስት ክፉ ነገር ውስጥ ያድንሃል፥ በሰባትም ውስጥ ክፋት አትነካህም።
20. በራብ ጊዜ ከሞት፥ በሰልፍም ከሰይፍ እጅ ያድንሃል።
21. ከምላስ ጅራፍ ትሰወራለህ፤ ጥፋትም ሲመጣ አትፈራም።
22. በጥፋትና በራብ ላይ ትስቃለህ፤ ከምድረ በዳ አራዊትም አትፈራም፤
23. ቃል ኪዳንህ ከምድረ በዳ ድንጋይ ጋር ይሆናልና፤ የምድረ በዳም አራዊት ከአንተ ጋር ይስማማሉና።
24. ድንኳንህም በሰላም እንዲሆን ታውቃለህ፤ በረትህን ትጐበኛለህ አንዳችም አይጐድልብህም።
25. ዘርህም ታላቅ እንዲሆን፥ ትውልድህም እንደ ምድር ሣር እንዲሆን ታውቃለህ።
26. በወራቱ የእህሉ ነዶ ወደ አውድማ እንዲገባ፥ በረጅም ዕድሜ ወደ መቃብር ትገባለህ።
27. እነሆ፥ ይህችን መረመርን፥ የሰማነውም ይህ ነው፤ አንተ ግን አንዳች ሠርተህ እንደ ሆነ ለራስህ እወቀው።

  Job (5/42)