| ← Job (41/42) → |
| 1. | እነሆ፥ ተስፋው ከንቱ ነው፤ ያየው ሁሉ ስንኳ በፊቱ ይዋረዳል። |
| 2. | ያንቀሳቅሰውም ዘንድ የሚደፍር የለም፤ እንግዲህ በፊቴ መቆም የሚችል ማን ነው? |
| 3. | እመልስለትስ ዘንድ መጀመሪያ የሰጠኝ ማን ነው? ከሰማይ ሁሉ በታች ያለው ገንዘቤ ነው። |
| 4. | ስለ አካላቱና ስለ ብርቱ ኃይሉ፥ ስለ መልካም ሰውነቱ ዝም አልልም። |
| 5. | የውጪ ልብሱን ማን ይገፋል? በጥንድ መንጋጋውስ ውስጥ ማን ይገባል? |
| 6. | የፊቱንስ ደጆች የሚከፍት ማን ነው? በጥርሶቹ ዙሪያ ግርማ አለ። |
| 7. | ቅርፊቶቹ ጠንካራ ስለ ሆኑ እርሱ ትዕቢተኛ ነው፤ በጠባብ ማተሚያ እንደ ታተሙ ናቸው። |
| 8. | እርስ በርሳቸው የተቀራረቡ ናቸውና ነፋስ በመካከላቸው መግባት አይችልም። |
| 9. | እርስ በርሳቸው የተገጣጠሙ ናቸው፤ እስከማይለያዩም ድረስ ተያይዘዋል። |
| 10. | እንጥሽታው ብልጭታ ያወጣል፥ ዓይኖቹም እንደ ወገግታ ናቸው። |
| 11. | ከአፉ ፋናዎች ይወጣሉ፥ የእሳትም ፍንጣሪ ይረጫል። |
| 12. | እንደ ፈላ ድስትና እንደሚቃጠል ሸምበቆ ከአንፍንጫው ጢስ ይወጣል። |
| 13. | እስትንፋሱ ከሰልን ታቃጥላለች፥ ነበልባልም ከአፉ ይወጣል። |
| 14. | በአንገቱ ኃይል ታድራለች፤ ግርማ በፊቱ ይዘፍናል። |
| 15. | የሥጋውም ቅርፊት የተጣበቀ ነው፤ እስከማይንቀሳቀሱም ድረስ በእርሱ ላይ ጸንተዋል። |
| 16. | ልቡ እንደ ድንጋይ የደነደነ ነው፤ እንደ ወፍጮ ድንጋይ የጸና ነው። |
| 17. | በተነሣ ጊዜ ኃያላን ይፈራሉ፤ ከድንጋጤም የተነሣ ያብዳሉ። |
| 18. | ሰይፍና ጦር፥ ፍላጻና መውጊያም ቢያገኙት አያሸንፉትም። |
| 19. | ብረትን እንደ ገለባ፥ ናስንም እንደ ነቀዘ እንጨት ይቈጥራቸዋል። |
| 20. | ፍላጻ ሊያባርረው አይችልም፤ የወንጭፍም ድንጋዮች እንደ ገለባ ይሆኑለታል። |
| 21. | በሎታውን እንደ ገለባ ይቈጥረዋል፤ ሰላጢኑም ሲሰበቅ ይስቃል። |
| 22. | ታቹ እንደ ስለታም ገል ነው፤ እንደ መዳመጫም በጭቃ ላይ ያልፋል። |
| 23. | ቀላዩን እንደ ድስት ያፈላዋል፤ ባሕሩንም እንደ ሽቱ ምንቸት ያደርገዋል። |
| 24. | በስተ ኋላው ብሩህ መንገድን ያበራል፤ ቀላዩም ሽበት ይመስላል። |
| 25. | ያለ ፍርሃት የተፈጠረ፥ እንደ እርሱ ያለ በምድር ላይ የለም። |
| 26. | ከፍ ያለውን ሁሉ ይመለከታል፤ በትዕቢተኞችም ሁሉ ላይ ንጉሥ ነው። |
| ← Job (41/42) → |