| ← Job (40/42) → |
| 1. | እግዚአብሔርም መለሰ ኢዮብንም እንዲህ አለው። |
| 2. | በውኑ የሚከራከር ሰው ሁሉን ከሚችል አምላክ ጋር ይከራከራልን? ከእግዚአብሔር ጋር የሚዋቀስ እርሱ ይመልስለት። |
| 3. | ኢዮብም መለሰ እግዚአብሔርንም እንዲህ አለው። |
| 4. | እነሆ፥ እኔ ወራዳ ሰው ነኝ፤ የምመልስልህ ምንድር ነው? እጄን በአፌ ላይ እጭናለሁ። |
| 5. | አንድ ጊዜ ተናገርሁ፥ አልመልስምም፤ ሁለተኛ ጊዜም፥ ከእንግዲህ ወዲህ አልናገርም። |
| 6. | እግዚአብሔርም በዐውሎ ነፋስ ውስጥ ሆኖ ለኢዮብ መለሰ እንዲህም አለ። |
| 7. | እንግዲህ እንደ ወንድ ወገብህን ታጠቅ፤ እጠይቅሃለሁ፥ አንተም ተናገረኝ። |
| 8. | በውኑ ፍርዴን ታፈርሳለህን? አንተስ ጻድቅ ትሆን ዘንድ በእኔ ትፈርዳለህን? |
| 9. | እንደ እግዚአብሔር ክንድ ያለ ክንድ አለህን? ወይስ እንደ እርሱ ባለ ድምፅ ታንጐደጕዳለህን? |
| 10. | በታላቅነትና በልዕልና ተላበስ፤ በክብርና በግርማም ተጐናጸፍ። |
| 11. | የቍጣህን ፈሳሽ አፍስስ፤ ትዕቢተኛውንም ሁሉ ተመልክተህ አዋርደው። |
| 12. | ትዕቢተኛውንም ሁሉ ተመልከት፥ ዝቅ ዝቅም አድርገው፤ በደለኞችንም ወዲያውኑ እርገጣቸው። |
| 13. | በአፈር ውስጥ በአንድነት ሰውራቸው፤ በተሸሸገም ስፍራ ፊታቸውን ሸፍን። |
| 14. | በዚያን ጊዜም ቀኝ እጅህ ታድንህ ዘንድ እንድትችል እኔ ደግሞ እመሰክርልሃለሁ። |
| 15. | ከአንተ ጋር የሠራሁትን ጉማሬ፥ እስኪ፥ ተመልከት፤ እንደ በሬ ሣር ይበላል። |
| 16. | እነሆ፥ ብርታቱ በወገቡ ውስጥ ነው፤ ኃይሉም በሆዱ ጅማት ውስጥ ነው። |
| 17. | ጅራቱን እንደ ጥድ ዛፍ ያወዛውዛል፤ የወርቹ ጅማት የተጐነጐነ ነው። |
| 18. | አጥንቱ እንደ ናስ አገዳ ነው፤ አካላቱ እንደ ብረት ዘንጎች ናቸው። |
| 19. | እርሱ የእግዚአብሔር ፍጥረት አውራ ነው፤ ሠሪውም ሰይፉን ሰጠው። |
| 20. | የሜዳ እንስሶች ሁሉ የሚጫወቱበት ተራራ ምግብን ያበቅልለታል። |
| 21. | ጥላ ካለው ዛፍ በታች፥ በደንገልና በረግረግ ውስጥ ይተኛል። |
| 22. | ጥላ ያለው ዛፍ በጥላው ይሰውረዋል፤ የወንዝ አኻያ ዛፎች ይከብቡታል። |
| 23. | እነሆ፥ ወንዙ ቢጐርፍ አይደነግጥም፤ ዮርዳኖስም እስከ አፉ ድረስ ቢፈስስ እርሱ ይተማመናል። |
| 24. | ዓይኖቹ እያዩ ይያዛልን? አፍንጫውስ በወጥመድ ይበሳልን? |
| ← Job (40/42) → |