Job (4/42)  

1. ቴማናዊውም ኤልፋዝ መለሰ እንዲህም አለ።
2. አንድ ሰው ከአንተ ጋር ይናገር ዘንድ ቢሞክር ትቀየማለህን? ቃልንስ ከመናገር ሊቀር የሚችል ማን ነው?
3. እነሆ፥ አንተ ብዙዎችን ታስተምር ነበር፥ የደከሙትንም እጆች ታበረታ ነበር፥
4. ቃልህ የሚሰናከለውን ያስነሣ ነበር፥ አንተም የሚብረከረከውን ጕልበት ታጸና ነበር።
5. አሁን ግን በአንተ ላይ መጥቶአል፥ አንተም ደከምህ፤ ደርሶብሃል፥ አንተም ተቸገርህ።
6. አምላክህን መፍራትህ መጽናናትህ፥ የቅንነትህም መንገድ ተስፋህ አይደለምን?
7. እባክህ አስብ፥ ንጹሕ ሆኖ የጠፋ ማን ነው? ከልበ ቅንስ የተደመሰሰ ማን ነው?
8. እኔ እንዳየሁ፥ ኃጢአትን የሚያርሱ፥ መከራንም የሚዘሩ ይህንኑ ያጭዳሉ።
9. በእግዚአብሔር እስትንፋስ ይጠፋሉ፥ በቍጣውም መንፈስ ያልቃሉ።
10. የአንበሳ ጩኸት፥ የጩዋኺ አንበሳ ድምፅ፥ የአንበሳ ደቦል ጥርስ ተሰባበረ።
11. አሮጌ አንበሳ አደን በማጣት ይሞታል፥ የአንበሳይቱም ግልገሎች ይበተናሉ።
12. ለእኔም በምሥጢር ቃል መጣልኝ፥ ጆሮዬም ሹክሹክታውን ሰማች።
13. በሌሊት ሕልም አሳብ ሲነሣ፥ የከበደም እንቅልፍ በሰው ላይ ሲወድቅ፥
14. አጥንቴን ሁሉ ያናወጡ ድንጋጤና መንቀጥቀጥ ወደቁብኝ።
15. መንፈስም በፊቴ አለፈ፤ የሥጋዬ ጠጕር ቆመ።
16. እርሱም ቆመ፥ መልኩን ግን ለመለየት አልቻልሁም፥ ምሳሌም በዓይኔ ፊት ነበረ፤ የዝምታ ድምፅ ሰማሁ።
17. በውኑ ሰው በእግዚአብሔር ፊት ጻድቅ ሊሆን፥ ወይስ ሰው በፈጣሪው ፊት ሊነጻ ይችላልን?
18. እነሆ፥ በባሪያዎቹ አይታመንም፤ መላእክቱንም ስንፍና ይከስሳቸዋል፤
19. ይልቁንስ በጭቃ ቤት የሚኖሩ፥ መሠረታቸው በትቢያ ውስጥ የሆነ፥ ከብል በፊት የሚጨፈለቁ እንዴት ይሆኑ?
20. በጥዋትና በማታ መካከል ይሰባበራሉ፤ ማንም ሳያስብ ለዘላለም ይጠፋሉ።
21. ገመዳቸው የተነቀለ አይደለምን? አለጥበብም ይሞታሉ።

  Job (4/42)