← Job (38/42) → |
1. | እግዚአብሔርም በዐውሎ ነፋስ ውስጥ ሆኖ ለኢዮብ መለሰ እንዲህም አለ። |
2. | ያለ እውቀት በሚነገር ቃል ምክርን የሚያጨልም ይህ ማነው? |
3. | እንግዲህ እንደ ሰው ወገብህን ታጠቅ፤ እጠይቅሃለሁ፥ አንተም ተናገረኝ። |
4. | ምድርን በመሠረትሁ ጊዜ አንተ ወዴት ነበርህ? ታስተውል እንደ ሆንህ ተናገር። |
5. | ብታውቅስ መሠፈሪያዋን የወሰነ፥ በላይዋስ የመለኪያ ገመድ የዘረጋ ማን ነው? |
7. | አጥቢያ ኮከቦች በአንድነት ሲዘምሩ፥ የእግዚአብሔርም ልጆች ሁሉ እልል ሲሉ፥ መሠረቶችዋ በምን ላይ ተተክለው ነበር? የማዕዘንዋንስ ድንጋይ ያቆመ ማን ነው? |
8. | ከማኅፀን እንደሚወጣ በወጣ ጊዜ ባሕርን በመዝጊያዎች የዘጋ ማን ነው? |
9. | ደመናውን ለልብሱ፥ ጨለማንም ለመጠቅለያው አደረግሁ፤ |
10. | ድንበሩን በዙሪያው አድርጌ፥ መወርወሪያዎቹንና መዝጊያዎቹን አኑሬ። |
11. | እስከዚህ ድረስ ድረሺ፥ አትለፊ፤ በዚህም ለትዕቢተኛው ማዕበልሽ ገደብ ይሁን አልሁ። |
13. | የምድርን ዳርቻ ይይዝ ዘንድ፥ ከእርስዋም በደለኞች ይናወጡ ዘንድ፥ በውኑ ከተወለድህ ጀምሮ ማለዳን አዝዘሃልን? ለወገግታም ስፍራውን አስታወቀኸዋልን? |
14. | ጭቃ ከማኅተም በታች እንደሚለወጥ እንዲሁ እርስዋ ትለወጣለች፤ ነገርም ሁሉ እንደ ልብስ ተቀልሞአል። |
15. | ከበደለኞች ብርሃናቸው ተከልክሎአል፥ ከፍ ያለውም ክንድ ተሰብሮአል። |
16. | ወደ ባሕር ምንጭስ ውስጥ ገብተሃልን? በቀላዩስ መሠረት ውስጥ ተመላልሰሃልን? |
17. | የሞት በሮች ተገልጠውልሃልን? የሞትንስ ጥላ ደጆች አይተሃልን? |
18. | ምድርንስ በስፋትዋ አስተውለሃታልን? ሁሉን አውቀህ እንደ ሆነ ተናገር። |
20. | ወደ ዳርቻው ትነዳው ዘንድ፥ ወደ ቤቱም የሚያደርሰውን ጐዳና ታውቅ ዘንድ፥ የብርሃን መኖሪያ መንገድ የት ነው? የጨለማውስ ቦታ ወዴት አለ? |
21. | በዚያን ጊዜ ተወልደህ ነበርና፥ የዕድሜህም ቍጥር ብዙ ነውና፤ በእውነት አንተ ሳታውቅ አትቀርም። |
22. | በውኑ ወደ በረዶው ቤተ መዛግብት ገብተሃልን? የበረዶውንስ ቅንጣት ቤተ መዛግብት አይተሃልን? |
23. | ይኸውም ለመከራ ጊዜ ለሰልፍና ለጦርነት ቀን የጠበቅሁት ነው። |
24. | ብርሃንስ በምን መንገድ ይከፈላል? የምሥራቅስ ነፋስ በምድር ላይ እንዴት ይበተናል? |
26. | ባድማውንና ውድማውን እንዲያጠግብ፥ |
27. | ሣሩንም እንዲያበቅል፥ ማንም በሌለባት ምድር ላይ፥ ሰውም በሌለባት ምድረ በዳ ላይ ዝናብን ያዘንብ ዘንድ፥ ለፈሳሹ ውኃ መንዶልዶያውን፥ ወይስ ለሚያንጐደጕድ መብረቅ መንገድን ያበጀ ማን ነው? |
28. | በውኑ ለዝናብ አባት አለውን? ወይስ የጠልን ነጠብጣብ የወለደ ማን ነው? |
29. | በረዶስ ከማን ማኅፀን ወጣ? የሰማዩንስ አመዳይ ማን ወለደው? |
30. | ውኆች እንደ ድንጋይ ጠነከሩ፥ የቀላዩም ፊት ረግቶአል። |
31. | በውኑ የሰባቱን ከዋክብት ዘለላ ታስር ዘንድ፥ ወይስ ኦሪዮን የሚባለውን ኮከብ ትፈታ ዘንድ ትችላለህን? |
32. | ወይስ ማዛሮት የሚባሉትን ከዋክብት በጊዜያቸው ታወጣ ዘንድ፥ ወይስ ድብ የሚባለውን ኮከብ ከልጆቹ ጋር ትመራ ዘንድ ትችላለህን? |
33. | የሰማይን ሥርዓት ታውቃለህን? በምድርስ ለይ እንዲሠለጥን ልታደርግ ትችላለህን? |
34. | የውኆች ብዛት ይሸፍንህ ዘንድ ቃልህን ወደ ደመናት ታነሣ ዘንድ ትችላለህን? |
35. | መብረቆች ሄደው። እነሆ፥ እዚህ አለን ይሉህ ዘንድ ልትልካቸው ትችላለህን? |
36. | በውስጡስ ጥበብን ያኖረ፥ ለሰውስ ልብ ማስተዋልን የሰጠ ማን ነው? |
38. | የሰማይን ደመና በጥበቡ ሊቈጥር የሚችል ማን ነው? ትቢያ በተበጠበጠ ጊዜ፥ ጓሎቹም በተጣበቁ ጊዜ፥ የሰማይን ረዋት ሊያዘነብል የሚችል ማን ነው? |
40. | በዋሾቻቸው ውስጥ ተጋድመው፥ በጫካም ውስጥ አድብተው ሳሉ፥ ለአንበሳይቱ አደን ታድናለህን? የልጆችዋንስ ነፍስ ታጠግብ ዘንድ ትችላለህን? |
41. | ልጆቹ ወደ እግዚአብሔር ሲጮኹ፥ የሚበሉትም አጥተው ሲቅበዘበዙ፥ ለቍራ መብልን የሚሰጠው ማን ነው? |
← Job (38/42) → |