| ← Job (33/42) → | 
| 1. | ነገር ግን፥ ኢዮብ ሆይ፥ ንግግሬን እንድትሰማ፥ ቃሌንም ሁሉ እንድታደምጥ እለምንሃለሁ። | 
| 2. | እነሆ፥ አፌን ከፍቻለሁ፥ አንደበቴም በትናጋዬ ተናግሮአል። | 
| 3. | ቃሌ የልቤን ቅንነት ያወጣል፤ ከንፈሮቼም የሚያውቁትን በቅንነት ይናገራሉ። | 
| 4. | የእግዚአብሔር መንፈስ ፈጠረኝ፥ ሁሉንም የሚችል የአምላክ እስትንፋስ ሕይወት ሰጠኝ። | 
| 5. | ይቻልህ እንደ ሆነ መልስልኝ፤ ቃልህንም አዘጋጅተህ በፊቴ ቁም። | 
| 6. | እነሆ፥ በእግዚአብሔር ፊት እኔ እንደ አንተ ነኝ፤ እኔ ደግሞ ከጭቃ የተፈጠርሁ ነኝ። | 
| 7. | እነሆ፥ ግርማዬ አታስፈራህም እጄም አትከብድብህም። | 
| 8. | በጆሮዬ ተናግረሃል፥ የቃልህንም ድምፅ ሰምቻለሁ፥ እንዲህም ብለሃል። | 
| 9. | እኔ ያለ መተላለፍ ንጹሕ ነኝ፤ ያለ ነውር ነኝ፥ ኃጢአትም የለብኝም፤ | 
| 10. | እነሆ፥ ምክንያት አግኝቶብኛል፥ እንደ ጠላቱም ቈጥሮኛል፤ | 
| 11. | እግሬን በግንድ አጣበቀ፥ መንገዴንም ሁሉ ተመለከተ። | 
| 12. | እነሆ፥ አንተ በዚህ ጻድቅ አይደለህም፤ እግዚአብሔር ከሰው ይበልጣል ብዬ እመልስልሃለሁ። | 
| 13. | አንተ። ለቃሌ ሁሉ አይመልስልኝም ብለህ፥ ስለ ምን ከእርሱ ጋር ትከራከራለህ? | 
| 14. | እግዚአብሔር በአንድ መንገድ በሌላም ይናገራል፤ ሰው ግን አያስተውለውም። | 
| 15. | በሕልም፥ በሌሊት ራእይ፥ አፍላ እንቅልፍ በሰዎች ላይ ሲወድቅ፥ በአልጋ ላይ ተኝተው ሳሉ፥ | 
| 16. | በዚያን ጊዜ የሰዎችን ጆሮ ይከፍታል፥ በተግሣጹም ያስደነግጣቸዋል፥ | 
| 17. | ሰውን ከክፉ ሥራው ይመልሰው ዘንድ ከሰውም ትዕቢትን ይሰውር ዘንድ፤ | 
| 18. | ነፍሱን ከጕድጓድ፥ በሰይፍም እንዳይጠፋ ሕይወቱን ይጠብቃል። | 
| 19. | ደግሞ በአልጋ ላይ በደዌ ይገሥጸዋል፥ አጥንቱንም ሁሉ ያደነዝዛል። | 
| 20. | ሕይወቱም እንጀራን፥ ነፍሱም ጣፋጭ መብልን ትጠላለች። | 
| 21. | ሥጋው እስከማይታይ ድረስ ይሰለስላል፤ ተሸፍኖ የነበረውም አጥንት ይገለጣል። | 
| 22. | ነፍሱ ወደ ጕድጓዱ፥ ሕይወቱም ወደሚገድሉአት ቀርባለች። | 
| 23. | የቀናውን መንገድ ለሰው ያስታውቀው ዘንድ፥ ከሺህ አንድ ሆኖ የሚተረጕም መልአክ ቢገኝለት፥ | 
| 24. | እየራራለት። ቤዛ አግኝቻለሁና ወደ ጕድጓድ እንዳይወርድ አድነው ቢለው፥ | 
| 25. | ሥጋው እንደ ሕፃን ሥጋ ይለመልማል፤ ወደ ጕብዝናውም ዘመን ይመለሳል። | 
| 26. | ወደ እግዚአብሔር ይጸልያል፥ እርሱም ሞገስን ይሰጠዋል ፊቱንም በደስታ ያሳየዋል፤ ለሰውም ጽድቁን ይመልስለታል። | 
| 27. | እርሱም በሰው ፊት እየዘመረ። እኔ በድያለሁ፥ ቅኑንም አጣምሜአለሁ፤ የሚገባኝንም ብድራት አልተቀበልሁም፤ | 
| 28. | ነፍሴ ወደ ጕድጓድ እንዳትወርድ አድኖአታል፥ ሕይወቴም ብርሃንን ታያለች ይላል። | 
| 29. | እግዚአብሔር ይህን ሁሉ ሁለት ጊዜና ሦስት ጊዜ ከሰው ጋር ያደርጋል፤ | 
| 30. | ይህም ነፍሱን ከጕድጓድ ይመልስ ዘንድ፥ በሕያዋንም ብርሃን ያበራ ዘንድ ነው። | 
| 31. | ኢዮብ ሆይ፥ አድምጥ፥ እኔንም ስማ፤ ዝም በል፥ እኔም እናገራለሁ። | 
| 32. | ነገር ቢኖርህ መልስልኝ፤ ትጸድቅ ዘንድ እወድዳለሁና ተናገር። | 
| 33. | ያለዚያም እኔን ስማ፤ ዝም በል፥ እኔም ጥበብን አስተምርሃለሁ። | 
| ← Job (33/42) → |