← Job (32/42) → |
1. | ኢዮብም ራሱን ጻድቅ አድርጎ ነበርና እነዚያ ሦስቱ ሰዎች መመለስን ተዉ። |
2. | ከራም ወገን የሆነ የቡዛዊው የባርክኤል ልጅ የኤሊሁ ቍጣ ነደደ፤ ከእግዚአብሔር ይልቅ ራሱን ጻድቅ አድርጎ ነበርና ኢዮብን ተቈጣው። |
3. | ደግሞም በኢዮብ ፈረዱበት እንጂ የሚገባ መልስ ስላላገኙ በሦስቱ ባልንጀሮቹ ላይ ተቈጣ። |
4. | ኤሊሁ ግን ከእርሱ ይልቅ ሽማግሌዎች ነበሩና ከኢዮብ ጋር መናገርን ጠብቆ ነበር። |
5. | ኤሊሁም በነዚህ በሦስቱ ሰዎች አፍ መልስ እንደሌለ ባየ ጊዜ ቍጣው ነደደ። |
6. | የቡዛዊውም የባርክኤል ልጅ ኤሊሁ ተናገረ እንዲህም አለ። እኔ በዕድሜ ታናሽ ነኝ፥ እናንተ ግን ሽማግሌዎች ናችሁ፤ ስለዚህም ሰጋሁ፤ እውቀቴን እገልጥላችሁ ዘንድ ፈራሁ። |
7. | እንደዚህም አልሁ። ዓመታት በተናገሩ ነበር፥ የዓመታትም ብዛት ጥበብን ባስተማረች ነበር። |
8. | ነገር ግን በሰው ውስጥ መንፈስ አለ፥ ሁሉንም የሚችል የአምላክ እስትንፋስ ማስተዋልን ይሰጣል። |
9. | በዕድሜ ያረጁ ጠቢባን አይደሉም፥ ሽማግሌዎችም ፍርድን አያስተውሉም። |
10. | ስለዚህም። ስሙኝ፤ እኔ ደግሞ እውቀቴን እገልጥላችኋለሁ አልሁ። |
11. | እነሆ፥ ቃላችሁን በትዕግሥት ጠበቅሁ፤ የምትናገሩትን ነገር እስክትመረምሩ ድረስ፤ ብልሃታችሁን አዳመጥሁ። |
12. | እንዲሁም ልብ አደረግሁ፤ እነሆም፥ በእናንተ መካከል ኢዮብን ያስረዳ፥ ወይም ለቃሉ የመለሰ የለም። |
13. | እናንተም። ጥበብን አግኝተናል፤ እግዚአብሔር ነው እንጂ ሰው አያሸንፈውም እንዳትሉ ተጠንቀቁ። |
14. | እርሱ ግን ቃሉን በእኔ ላይ አልተናገረም፤ እኔም በንግግራችሁ አልመልስለትም። |
15. | እነርሱ ደነገጡ፥ ዳግመኛም አልመለሱም፤ የሚናገሩትንም አጡ። |
16. | እነርሱ አልተናገሩምና፥ ቆመው ዳግመኛ አልመለሱምና እኔ በትዕግሥት እጠብቃለሁን? |
17. | እኔ ደግሞ ፈንታዬን እመልሳለሁ፥ እውቀቴንም እገልጣለሁ፤ |
18. | እኔ ቃል ተሞልቻለሁና፥ በውስጤም ያለ መንፈስ አስገድዶኛልና። |
19. | በተሐ ጠጅ እንደ ተሞላና ሊቀደድ እንደ ቀረበ አቁማዳ፥ ሊፈነዳ እንደማይችል እንደ ወይን ጠጅ አቁማዳ፥ እነሆ፥ አንጀቴ ሆነ። |
20. | ጥቂት እንድተነፍስ እናገራለሁ፤ ከንፈሬን ገልጬ እመልሳለሁ። |
21. | ለሰው ፊት ግን አላደላም፤ ሰውንም አላቈላምጥም። |
22. | በማቈላመጥ እናገር ዘንድ አላውቅምና፤ ያለዚያስ ፈጣሪዬ ፈጥኖ ከሕይወቴ ይለየኝ ነበር። |
← Job (32/42) → |