| ← Job (30/42) → |
| 1. | አሁን ግን በዕድሜ ከእኔ የሚያንሱ፥ አባቶቻቸውን ከመንጋዬ ውሾች ጋር ለማኖር የናቅኋቸው፥ በእኔ ላይ ተሳለቁብኝ። |
| 2. | ሙሉ ሰው መሆናቸው ጠፍቶባቸው ነበርና የእጃቸው ብርታት ለእኔ ምን ይጠቅማል? |
| 3. | በራብና በቀጠና የመነመኑ ናቸው፤ የመፍረስና የመፈታት ጨለማ ወዳለበት ወደ ምድረ በዳ ይሸሻሉ። |
| 4. | በቍጥቋጦ አጠገብ ያለውን ጨው ጨው የሚለውን አትክልት ይለቅማሉ፤ የክትክታ ሥር ደግሞ መብላቸው ነው። |
| 5. | ከሰዎች ተለይተው ተሰደዱ፤ በሌባ ላይ እንደሚጮኽ ይጮኹባቸዋል። |
| 6. | በሸለቆ ፈረፈርና በምድር ጕድጓድ በድንጋይም ዋሻ ውስጥ ይኖራሉ። |
| 7. | በቍጥቋጦ መካከል ይጮኻሉ፤ ከሳማ በታች ተሰብስበዋል። |
| 8. | የሰነፎችና የነውረኞች ልጆች ናቸው፤ ከምድርም በግርፋት የተባረሩ ናቸው። |
| 9. | አሁንም እኔ መዝፈኛና መተረቻ ሆንኋቸው። |
| 10. | ተጸየፉኝ፥ ከእኔም ራቁ፤ አክታቸውንም በፊቴ መትፋትን አልተዉም። |
| 11. | የቀስቴን አውታር አላልቶብኛል፥ አዋርዶኝማል፤ እነርሱም በፊቴ ልጓማቸውን ፈትተዋል። |
| 12. | በቀኜ በኩል ዱርዬዎች ተነሥተዋል፥ እግሬንም ይገለብጣሉ፤ የጥፋታቸውን መንገድ በእኔ ላይ ይጐድባሉ። |
| 13. | ጐዳናዬን ያበላሻሉ፤ ረዳት የሌላቸው ሰዎች መከራዬን ያበዛሉ። |
| 14. | በሰፊ ፍራሽ እንደሚመጡ ይመጡብኛል፤ በባድማ ውስጥ ይንከባለሉብኛል። |
| 15. | ድንጋጤ በላዬ ተመለሰችብኝ፥ ክብሬንም እንደ ነፋስ ያሳድዱአታል፤ ደኅንነቴም እንደ ደመና አልፋለች። |
| 16. | አሁንም ነፍሴ በውስጤ ፈሰሰች፤ የመከራም ዘመን ያዘችኝ። |
| 17. | በሌሊት አጥንቴ በደዌ ተነደለች፥ ጅማቶቼም አያርፉም። |
| 18. | ከታላቁ ደዌ ኃይል የተነሣ ልብሴ ተበላሸች፤ እንደ ቀሚስ ክሳድ አነቀችኝ። |
| 19. | እርሱ በጭቃ ውስጥ ጣለኝ፥ አፈርና አመድም መሰልሁ። |
| 20. | ወደ አንተ ጮኽሁ፥ አልመለስህልኝም፤ ተነሣሁ፥ አልተመለከትኸኝም። |
| 21. | ተመልሰህ ጨካኝ ሆንህብኝ፤ በእጅህም ብረታት አስጨነቅኸኝ። |
| 22. | በነፋስ አነሣኸኝ፥ በላዩም አስቀመጥኸኝ፤ በዐውሎ ነፋስ አቀለጥኸኝ። |
| 23. | ለሞት ሕያዋንም ሁሉ ለሚሰበሰቡበት ቤት አሳልፈህ እንደምትሰጠኝ አውቄአለሁና። |
| 24. | ነገር ግን ሰው በወደቀ ጊዜ እጁን አይዘረጋምን? በጥፋቱስ ጊዜ አይጮኽምን? |
| 25. | ጭንቅ ቀን ላገኘው ሰው አላለቀስሁምን? ለችግረኛስ ነፍሴ አላዘነችምን? |
| 26. | ነገር ግን በጎነትን በተጠባበቅሁ ጊዜ ክፉ ነገር መጣችብኝ፤ ብርሃንን በትዕግሥት ጠበቅሁ፥ ጨለማም መጣ። |
| 27. | አንጀቴ ፈላች፥ አላረፈችም፤ የመከራም ዘመን መጣችብኝ። |
| 28. | ያለ ፀሐይ በትካዜ ሄድሁ፤ በጉባኤም መካከል ቆሜ ጮኽሁ። |
| 29. | ለቀበሮ ወንድም፥ ለሰጐንም ባልንጀራ ሆንሁ። |
| 30. | ቁርበቴ ጠቈረ፥ ከእኔም ተለይቶ እርግፍግፍ አለ፤ አጥንቴም ከትኵሳት የተነሣ ተቃጠለች። |
| 31. | ስለዚህ መሰንቆዬ ለኀዘን፥ እምቢልታዬም ለሚያለቅሱ ቃል ሆነ። |
| ← Job (30/42) → |