| ← Job (29/42) → |
| 1. | ኢዮብም ምሳሌውን ይመስል ዘንድ ደገመ፥ እንዲህም አለ። |
| 2. | እግዚአብሔር ይጠብቀኝ እንደ ነበረው ጊዜ፥ እንደ ፊተኛው ወራት ምነው በሆንሁ! |
| 3. | በራሴ ላይ መብራቱ በበራ ጊዜ፥ እኔም ጨለማውን አልፌ በብርሃኑ በሄድሁ ጊዜ፥ |
| 4. | በሙሉ ሰውነቴ እንደ ነበርሁ ጊዜ፥ እግዚአብሔር ድንኳኔን በጋረደ ጊዜ፥ |
| 5. | ሁሉን የሚችል አምላክ ከእኔ ጋር ገና ሳለ፥ ልጆቼም በዙሪያዬ ሳሉ፥ |
| 6. | መንገዴ በቅቤ ይታጠብ በነበረ ጊዜ፥ ድንጋዩ የዘይት ፈሳሽ ያፈስስልኝ በነበረ ጊዜ። |
| 7. | ወደ ከተማይቱ በር በወጣሁ ጊዜ፥ በአደባባዩም ወንበሬን ባኖርሁ ጊዜ፥ |
| 8. | ጐበዛዝት እኔን አይተው ተሸሸጉ፥ ሽማግሌዎችም ተነሥተው ቆሙ። |
| 9. | አለቆቹ ከመናገር ዝም አሉ፥ እጃቸውንም በአፋቸው ላይ ጫኑ። |
| 10. | የታላላቆቹም ድምፅ አረመመ፤ ምላሳቸውም በትናጋቸው ተጣጋ። |
| 11. | የሰማችኝ ጆሮ አሞገሰችኝ፥ ያየችኝም ዓይን መሰከረችልኝ፤ |
| 12. | የሚጮኸውን ችግረኛ፥ ድሀ አደጉንና ረጂ የሌለውን አድኜ ነበርሁና። |
| 13. | ለጥፋት የቀረበው በረከት በላዬ መጣ፤ የባልቴቲቱንም ልብ እልል አሰኘሁ። |
| 14. | ጽድቅን ለበስሁ እርስዋም ለበሰችኝ፤ ፍርዴም እንደ መጐናጸፊያና እንደ ኵፋር ነበረ። |
| 15. | ለዕውር ዓይን፥ ለአንካሳ እግር ነበርሁ። |
| 16. | ለድሀው አባት ነበርሁ፤ የማላውቀውንም ሰው ሙግት መረመርሁ። |
| 17. | የኃጢአተኛውን መንጋጋ ሰበርሁ፥ የነጠቀውንም ከጥርሱ ውስጥ አስጣልሁ። |
| 18. | እኔም አልሁ። በልጆቼ መካከል እሞታለሁ፥ ዕድሜዬንም እንደ አሸዋ አበዛለሁ፤ |
| 19. | ሥሬ በውኃ ላይ ተዘርግቶአል፥ ጠልም በቅርንጫፌ ላይ ያድራል፤ |
| 20. | ክብሬ በእኔ ዘንድ ታድሶአል፥ ቀስቴም በእጄ ውስጥ ለምልሞአል። |
| 21. | ሰዎች እኔን ሰምተው በትዕግሥት ተጠባበቁ፥ ምክሬንም ለማዳመጥ ዝም አሉ። |
| 22. | ከቃሌ በኋላ አንዳች አልመለሱም፤ ንግግሬም በእርሱ ላይ ተንጠባጠበ። |
| 23. | ዝናብን እንደሚጠብቁ በትዕግሥት ጠበቁኝ፤ የጥቢን ዝናብ እንደሚሹ አፋቸውን ከፈቱ። |
| 24. | እነርሱ ባልታመኑ ጊዜ ሳቅሁላቸው፤ የፊቴንም ብርሃን አላወረዱም። |
| 25. | መንገዳቸውን መረጥሁ፤ እንደ አለቃ ሆኜ ተቀመጥሁ፤ ንጉሥ በሠራዊቱ መካከል እንደሚኖር፥ ኅዘነተኞችን እንደሚያጽናና ኖርሁ። |
| ← Job (29/42) → |