| ← Job (28/42) → |
| 1. | በእውነት ብር የሚወጣበት፥ ወርቅም የሚነጠርበት ስፍራ አለ። |
| 2. | ብረት ከመሬት ውስጥ ይወሰዳል፤ መዳብም ከድንጋይ ይቀለጣል። |
| 3. | ሰው ለጨለማ ፍጻሜን ያደርጋል፤ የጨለማውንና የሞት ጥላን ድንጋይ እስከ ወሰኑ ድረስ ይፈላልጋል። |
| 4. | ሰው ከሚኖርበት ርቀው መውረጃ ይቈፍራሉ፤ ከሰውም እግር ተረሱ፥ ከሰዎችም ርቀው እየተንጠለጠሉ ይወዛወዛሉ። |
| 5. | እንጀራ ከምድር ውስጥ ይወጣል፤ በእሳትም እንደሚሆን ታችኛው ይገለበጣል። |
| 6. | ድንጋይዋ የሰንፔር ስፍራ ነው፥ የወርቅም ድቃቂ አለው። |
| 7. | መንገድዋን ጭልፊት አያውቀውም፥ የአሞራም ዓይን አላየውም። |
| 8. | የትዕቢት ልጆች አልረገጡአትም፥ ደቦል አንበሳ አላለፈባትም። |
| 9. | ሰው ወደ ቡላድ ድንጋይ እጁን ይዘረጋል፥ ተራራውንም ከመሠረቱ ይገለብጣል። |
| 10. | ከድንጋይ ውስጥ መንዶልዶያ ይወቅራል፤ ዓይኑም ዕንቍን ሁሉ ታያለች። |
| 11. | ፈሳሹም እንዳይንጠባጠብ ይገድባል፤ የተሰወረውንም ነገር ወደ ብርሃን ያወጣል። |
| 12. | ነገር ግን ጥበብ የምትገኘው ወዴት ነው? የማስተዋልስ ስፍራ ወዴት ነው? |
| 13. | ሰው መንገድዋን አያውቅም፤ በሕያዋን ምድር አትገኝም። |
| 14. | ቀላይ። በእኔ ውስጥ የለችም ይላል፤ ባሕርም። በእኔ ዘንድ የለችም ይላል። |
| 15. | በምዝምዝ ወርቅ አትገኝም፥ ብርም ስለ ዋጋዋ አይመዘንም። |
| 16. | በኦፊር ወርቅ፥ በከበረም መረግድና በሰንፔር አትገመትም። |
| 17. | ወርቅና ብርጭቆ አይወዳደሩአትም፥ በጥሩ ወርቅም ዕቃ አትለወጥም። |
| 18. | ስለ ዛጐልና ስለ አልማዝ አይነገርም። የጥበብ ዋጋ ከቀይ ዕንቍ ይልቅ ይበልጣል። |
| 19. | የኢትዮጵያ ቶጳዝዮን አይተካከላትም፥ በጥሩም ወርቅ አትገመትም። |
| 20. | እንግዲያሳ ጥበብ ከወዴት ትመጣለች? የማስተዋልስ ስፍራ ወዴት ነው? |
| 21. | ከሕያዋን ሁሉ ዓይን ተሰውራለች፥ ከሰማይ ወፎች ተሸሽጋለች። |
| 22. | ጥፋትና ሞት። ወሬዋን በጆሮቻችን ሰማን ብለዋል። |
| 23. | እግዚአብሔር መንገድዋን ያስተውላል፥ እርሱም ስፍራዋን ያውቃል። |
| 24. | እርሱም የምድርን ዳርቻ ይመለከታል፥ ከሰማይም በታች ያለውን ሁሉ ያያል። |
| 25. | ለነፋስ ሚዛንን ባደረገለት ጊዜ፥ ውኆችንም በስፍር በሰፈረ ጊዜ፥ |
| 26. | ለዝናብም ሥርዓትን፥ ለነጐድጓድ መብረቅም መንገድን ባደረገ ጊዜ፥ |
| 27. | በዚያን ጊዜ አያት፥ ገለጣትም፤ አዘጋጃትም፥ ደግሞም መረመራት። |
| 28. | ሰውንም። እነሆ፥ እግዚአብሔርን መፍራት ጥበብ ነው፤ ከኃጢአትም መራቅ ማስተዋል ነው አለው። |
| ← Job (28/42) → |