Job (27/42)  

1. ኢዮብም ምሳሌውን ይመስል ዘንድ ደገመ፥ እንዲህም አለ።
2. ፍርዴን ያስወገደ ሕያው እግዚአብሔርን! ነፍሴንም መራራ ያደረገ ሁሉን የሚችል ሕያው አምላክን!
3. እስትንፋሴ በእኔ ውስጥ፥ የእግዚአብሔርም መንፈስ በአፍንጫዬ ውስጥ ገና ሳለ፥
4. ከንፈሬ ኃጢአትን አትናገርም፥ አንደበቴም ሽንገላን አያወጣም።
5. እናንተን ማጽደቅ ከእኔ ዘንድ ይራቅ፤ እስክሞት ድረስ ፍጹምነቴን ከእኔ አላርቅም።
6. ጽድቄን እይዛለሁ እርሱንም አልተውም፤ ከቀኖቼም ሁሉ ስለ አንዱ ልቤ አይዘልፈኝም።
7. ጠላቴ እንደ በደለኛ፥ በእኔ ላይም የሚነሣ እንደ ኃጢአተኛ ይሁን።
8. እግዚአብሔር ባጠፋውና ነፍሱን በለየ ጊዜ፥ የዝንጉ ሰው ተስፋው ምንድር ነው?
9. በውኑ መከራ በመጣበት ጊዜ፥ እግዚአብሔር ጩኸቱን ይሰማልን?
10. ሁሉንስ በሚችል አምላክ ደስ ይለዋልን? እግዚአብሔርንስ ሁልጊዜ ይጠራልን?
11. እኔ ስለ እግዚአብሔር እጅ አስተምራችኋለሁ፤ ሁሉን በሚችል አምላክ ዘንድ ያለውን አልሸሽግም።
12. እነሆ፥ ሁላችሁ አይታችኋል፤ ስለ ምን ከንቱ ሆናችሁ?
13. ይህች ከእግዚአብሔር ዘንድ የበደለኛ እድል ፈንታ፥ ግፈኛም ሁሉን ከሚችል አምላክ ዘንድ የሚቀበላት ርስት ናት፤
14. ልጆቹ ቢበዙ ለሰይፍ ይሆናሉ፤ ዘሩም እንጀራን አይጠግብም።
15. ለእርሱም የቀሩት በቸነፈር ይቀበራሉ፤ መበለቶቻቸውም አያለቅሱም።
16. እርሱ ብርን እንደ አፈር ቢከምር፥ ልብስንም እንደ ጭቃ ቢያዘጋጅ፥
17. እርሱ ያዘጋጀው ይሆናል፥ ነገር ግን ጻድቅ ይለብሰዋል፤ ብሩንም ንጹሐን ይከፋፈሉታል።
18. የሚሠራው ቤት እንደ ሸረሪት ድር ይሠራል፥ ጠባቂም እንደሚሠራው ጎጆ ነው።
19. ባለጠጋ ሆኖ ይተኛል፥ ዳግመኛም አይተኛም፤ ዓይኑን ይከፍታል፥ እርሱም የለም።
20. ድንጋጤ እንደ ጐርፍ ታገኘዋለች፤ በሌሊትም ዐውሎ ነፋስ ትነጥቀዋለች።
21. የምሥራቅ ነፋስ ያነሣዋል፥ እርሱም ይሄዳል፤ ከቦታውም ይጠርገዋል።
22. እርሱ ይጥልበታል፥ አይራራለትም፤ ከእጁ ፈጥኖ መሸሽ ይወድዳል።
23. ሰው በእጁ ያጨበጭብበታል፤ ከስፍራውም በፉጨት ያስወጡታል።

  Job (27/42)