| ← Job (24/42) → |
| 1. | ሁሉን ከሚችል አምላክ ዘንድ ዘመናት አልተሰወረምና እርሱን የሚያውቁ ለምን ወራቱን አያዩም? |
| 2. | የድንበሩን ምልክት የሚያፈርሱ አሉ፤ መንጋዎቹን በዝብዘው ያሰማራሉ። |
| 3. | የድሀ አድጎቹን አህያ ይነዳሉ፤ የመበለቲቱን በሬ ስለ መያዣ ይወስዳሉ። |
| 4. | ድሆቹን ከመንገዱ ያወጣሉ፤ የምድርም ችግረኞች ሁሉ ይሸሸጋሉ። |
| 5. | እነሆ፥ በምድረ በዳ እንዳሉ እንደ ሜዳ አህዮች፥ መብልን ፈልገው ወደ ሥራቸው ይወጣሉ፤ ምድረ በዳውም ለልጆቻቸው መብልን ይሰጣቸዋል። |
| 6. | እነዚያ በእርሻ ውስጥ እህላቸውን ያጭዳሉ፤ የበደለኛውንም ወይን ይቃርማሉ። |
| 7. | ራቁታቸውን ያለ ልብስ ያድራሉ፥ በብርድ ጊዜ መጐናጸፊያ የላቸውም። |
| 8. | ከተራሮች በሚወርድ ዝናብ ይረጥባሉ፤ መጠጊያም አጥተው ቋጥኙን ያቅፋሉ። |
| 9. | ድሀ አደጉን ልጅ ከጡቱ የሚነጥሉ አሉ ከችግረኛውም መያዣ ይወስዳሉ። |
| 10. | ያለ ልብስ ራቁታቸውን ይሄዳሉ፤ ተርበውም ነዶዎችን ይሸከማሉ፤ |
| 11. | በእነዚህ ሰዎች አጥር ውስጥ ዘይት ያደርጋሉ፤ ወይንም ይጠምቃሉ፥ ነገር ግን ይጠማሉ። |
| 12. | ከከተማውና ከገዛ ቤቶቻቸው ይባረራሉ፤ የልጆችም ነፍስ ለእርዳታ ትጮኻለች፤ እግዚአብሔር ግን ስንፍናቸውን አይመለከትም። |
| 13. | እነዚህ በብርሃን ላይ የሚያምፁ ናቸው፤ መንገዱን አያውቁም፥ በጎዳናውም አይጸኑም። |
| 14. | ነፍሰ ገዳዩም ሳይነጋ ማልዶ ይነሣል፤ ችግረኞችንና ድሆችን ይገድላል፤ በሌሊትም እንደ ሌባ ነው። |
| 15. | የአመንዝራም ዓይን ድግዝግዝታን ይጠብቃል። የማንም ዓይን አያየኝም ይላል፥ ፊቱንም ይሸፍናል። |
| 16. | ቤቶቹን በጨለማ ይነድላሉ፤ በቀን ይሸሸጋሉ፤ ብርሃንም አያውቁም። |
| 17. | የጥዋት ብርሃን ለእነርሱ ሁሉ እንደ ሞት ጥላ ነው፤ የሞትን ጥላ ድንጋጤ ያውቃሉና። |
| 18. | እነርሱ በውኃ ፊት ላይ በርረው ያልፋሉ፤ እድል ፈንታቸውም በምድር ላይ የተረገመች ናት፤ ወደ ወይኑ ቦታ መንገድ አይዞሩም። |
| 19. | ድርቅና ሙቀት የአመዳዩን ውኃ ያጠፋሉ፤ እንዲሁ ሲኦል በደለኞችን ታጠፋለች። |
| 20. | ማኅፀን ትረሳዋለች፤ ትልም በደስታ ይጠባዋል፤ ዳግመኛም አይታሰብም፤ ክፋትም እንደ ዛፍ ይሰበራል። |
| 21. | የማትወልደውን መካኒቱን ይበድላታል፤ ለመበለቲቱም በጎነት አያደርግም። |
| 22. | ነገር ግን በኃይሉ ኃያላንን ይስባል፤ እርሱም በተነሣ ጊዜ ሰው በሕይወቱ አይታመንም። |
| 23. | እግዚአብሔር በደኅና አኑሮአቸዋል፥ በዚያም ይታመናሉ፤ ዓይኖቹ ግን በመንገዳቸው ላይ ናቸው። |
| 24. | ጥቂት ጊዜ ከፍ ከፍ ይላሉ፤ ይሄዳሉ፥ ይጠወልጋሉም፤ እንደ ሌሎች ሁሉ ይከማቻሉ፤ እንደ እሸትም ራስ ይቈረጣሉ። |
| 25. | እንዲህስ ባይሆን ሐሰተኛ የሚያደርገኝ፥ ነገሬንስ እንደ ምናምን የሚያደርገው ማን ነው? |
| ← Job (24/42) → |