| ← Job (22/42) → |
| 1. | ቴማናዊውም ኤልፋዝ መለሰ እንዲህም አለ። |
| 2. | በውኑ ሰው እግዚአብሔርን ይጠቅመዋልን? በእውነት ጥበበኛ ሰው ራሱን ይጠቅማል። |
| 3. | ጻድቅ መሆንህስ ሁሉን የሚችለውን አምላክ ደስ ያሰኘዋልን? መንገድህን ማቅናትህስ ይጠቅመዋልን? |
| 4. | እርሱንስ ስለ ፈራህ ይዘልፍሃልን? ወደ ፍርድስ ከአንተ ጋር ይገባልን? |
| 5. | ክፋትህስ የበዛ አይደለምን? ለኃጢአትህም ፍጻሜ የላትም። |
| 6. | የወንድሞችህን መያዣ በከንቱ ወስደሃል፥ የእርዘኞቹንም ልብስ ዘርፈሃል። |
| 7. | ለደካማ ውኃ አላጠጣህም፥ ለራብተኛም እንጀራን ከልክለሃል። |
| 8. | በክንድ የበረታ ምድርን ገዛ፤ ከበርቴውም ሰው ተቀመጠባት። |
| 9. | መበለቲቱን አንዳች አልባ ሰድደሃታል፤ የድሀ አደጎችም ክንድ ተሰብሮአል። |
| 10. | ስለዚህ አሽክላ ከብቦሃል፥ ድንገተኛ ፍርሃትም አናውጦሃል። |
| 11. | እንዳታይ ብርሃን ጨለማ ሆነችብህ፥ የውኆችም ብዛት አሰጠመህ። |
| 12. | እግዚአብሔር በሰማያት ከፍ ከፍ አይልምን? ከዋክብትም እንዴት ከፍ ከፍ እንዳሉ ተመልከት። |
| 13. | አንተም። እግዚአብሔር ምን ያውቃል? በድቅድቅ ጨለማ ውስጥ ሆኖ ሊፈርድ ይችላልን? |
| 14. | እንዳያይ የጠቈረ ደመና ጋርዶታል፤ በሰማይ ክበብ ላይ ይራመዳል ብለሃል። |
| 15. | በውኑ ኃጢአተኞች ሰዎች የረገጡአትን የዱሮይቱን መንገድ ትጠብቃለህን? |
| 16. | ጊዜያቸው ሳይደርስ ተነጠቁ፤ መሠረታቸውም እንደ ፈሳሽ ውኃ ፈሰሰ። |
| 17. | እግዚአብሔርንም። ከእኛ ዘንድ ራቅ፤ ሁሉንም የሚችል አምላክ ምን ሊያደርግልን ይችላል? አሉት። |
| 18. | ነገር ግን ቤታቸውን በመልካም ነገር ሞላ፤ የኃጥአን ምክር ከእኔ ዘንድ የራቀች ናት። |
| 19. | ጻድቃን ያዩታል፥ ደስም ይላቸዋል፤ ንጹሐንም በንቀት ይስቁባቸዋል። |
| 20. | በእውነት ሀብታቸው ጠፋ፥ የቀረውንም እሳት በላች። |
| 21. | አሁንም ከእርሱ ጋር ተስማማ፥ ሰላምም ይኑርህ፤ በዚያም በጎነት ታገኛለህ። |
| 22. | ከአፉም ሕጉን ተቀበል፥ በልብህም ቃሉን አኑር፤ |
| 23. | ሁሉን ወደሚችል አምላክ ብትመለስ፥ ብትዋረድም፥ ኃጢአትንም ከድንኳንህ ብታርቅ፥ |
| 24. | የወርቅን ዕቃ በአፈር ውስጥ፥ የኦፊርንም ወርቅ በጅረት ድንጋይ መካከል ብትጥል፥ |
| 25. | ሁሉን የሚችል አምላክ ወርቅና የሚብለጨለጭ ብር ይሆንልሃል። |
| 26. | የዚያን ጊዜ ሁሉን በሚችል አምላክ ደስ ይልሃል፥ ፊትህንም ወደ እግዚአብሔር ታነሣለህ። |
| 27. | ወደ እርሱም ትጸልያለህ፥ እርሱም ይሰማሃል፤ ስእለትህንም ትሰጣለህ። |
| 28. | ነገርንም ትመክራለህ፥ እርሱም ይሳካልሃል፤ ብርሃንም በመንገድህ ላይ ይበራል። |
| 29. | ቢያዋርዱህ አንተ ከፍ ከፍ ትላለህ፤ ትሑቱንም ሰው ያድነዋል። |
| 30. | ንጹሑን ሰው ያድነዋል፤ በእጅህም ንጽሕና ትድናለህ። |
| ← Job (22/42) → |