| ← Job (21/42) → |
| 1. | ኢዮብም መለሰ እንዲህም አለ። |
| 2. | ስሙ፥ ቃሌን ስሙ፤ ይህም መጽናናታችሁ ይሁን። |
| 3. | እናገር ዘንድ ተዉኝ፤ ከተናገርሁም በኋላ ተሳለቁ። |
| 4. | በውኑ የኀዘን እንጉርጕሮዬ ለሰው እናገራለሁን? አለመታገሥ ስለ ምን አይገባኝም? |
| 5. | ወደ እኔ ተመልከቱ፥ ተደነቁም፤ እጃችሁንም በአፋችሁ ላይ አኑሩ። |
| 6. | እኔ ባሰብሁ ቍጥር እጨነቃለሁ፥ ፃዕርም ሥጋዬን ይይዛል። |
| 7. | ስለ ምን ኃጢአተኞች በሕይወት ይኖራሉ? ስለ ምንስ ያረጃሉ? በባለጠግነትስ ስለ ምን ይበረታሉ? |
| 8. | ዘራቸው ከእነርሱ ጋር ጸንቶ ይኖራል፥ ልጆቻቸውም በዓይናቸው ፊት ናቸው። |
| 9. | ቤታቸው ከፍርሃት ወጥቶ የታመነ ነው፥ የእግዚአብሔርም በትር የለባቸውም። |
| 10. | ኮርማቸው ይወልዳል፥ ዘሩንም አይጥለውም፤ ላማቸውም ትወልዳለች፥ አትጨነግፍም። |
| 11. | ሕፃናቶቻቸውን እንደ መንጋ ያወጣሉ፥ ልጆቻቸውም ይዘፍናሉ። |
| 12. | ከበሮና መሰንቆ ወስደው ይዘምራሉ፥ በእምቢልታ ድምፅ ደስ ይላቸዋል። |
| 13. | ዕድሜያቸውንም በተድላ ይፈጽማሉ፤ ድንገትም ወደ ሲኦል ይወርዳሉ። |
| 14. | እግዚአብሔርንም። ከእኛ ዘንድ ራቅ፤ መንገድህን እናውቅ ዘንድ አንወድድም። |
| 15. | እናመልከውስ ዘንድ ሁሉን የሚችል አምላክ ማን ነው? ወይስ ወደ እርሱ ብንጸልይ ምን ይጠቅመናል? ይላሉ። |
| 16. | እነሆ፥ ሀብታቸው በእጃቸው ውስጥ አይደለምን? የኃጥአን ምክር ከእኔ ዘንድ የራቀች ናት። |
| 17. | የኃጥአን መብራት የጠፋው፥ መቅሠፍትም የመጣባቸው፥ እግዚአብሔርም በቍጣው መከራ የከፈላቸው፥ |
| 18. | በነፋስ ፊት እንደ ገለባ፥ ዐውሎ ነፋስም እንደሚወስደው ትቢያ የሆኑ ስንት ጊዜ ነው? |
| 19. | እናንተ። እግዚአብሔር በደላቸውን ለልጆቻቸው ይጠብቃል ብላችኋል። እነርሱ ያውቁ ዘንድ ፍዳን ለራሳቸው ይክፈል። |
| 20. | ዓይኖቻቸው ጥፋታቸውን ይዩ፥ ሁሉን ከሚችል አምላክ ቍጣ ይጠጡ። |
| 21. | የወራታቸውስ ቍጥር ቢቈረጥ፥ ከእነርሱ በኋላ የቤታቸው ደስታ ምን ይሆናቸዋል? |
| 22. | ከፍ ከፍ ባሉትስ ላይ ለሚፈርድ ለእግዚአብሔር በውኑ ሰው እውቀትን ያስተምራልን? |
| 23. | አንድ ሰው በሰላም ተዘልሎ ሲቀመጥ በሙሉ ኃይሉ ሳለ ይሞታል። |
| 24. | በአንጀቱ ውስጥ ስብ ሞልቶአል፥ የአጥንቶቹም ቅልጥም ረጥቦአል። |
| 25. | ሌላውም ሰው መልካምን ነገር ከቶ ሳይቀምስ በተመረረች ነፍስ ይሞታል። |
| 26. | በአፈር ውስጥ በአንድ ላይ ይተኛሉ፥ ትልም ይከድናቸዋል። |
| 27. | እነሆ፥ አሳባችሁን፥ የመከራችሁብኝንም ክፉ ምክር አውቄዋለሁ። |
| 28. | እናንተ። የከበርቴው ቤት የት ነው? ኃጢአተኛውም ያደረበት ድንኳን የት ነው? ብላችኋል። |
| 29. | መንገድ አላፊዎችን አልጠየቃችሁምን? ምልክታቸውን አታውቁምን? |
| 30. | ኃጢአተኛው በመቅሠፍት ቀን እንደ ተጠበቀ፥ በቍጣው ቀን እንደሚድን። |
| 31. | መንገዱን በፊቱ የሚናገር ማን ነው? የሠራውንስ የሚመልስበት ማን ነው? |
| 32. | እርሱን ግን ወደ መቃብር ይሸከሙታል፥ ሰዎቹም በመቃብሩ ላይ ይጠብቃሉ። |
| 33. | የሸለቆው ጓል ይጣፍጥለታል፤ በኋላውም ሰው ሁሉ ይሳባል፥ በፊቱም ቍጥር የሌለው ጉባኤ አለ። |
| 34. | የምትመልሱልኝ ውስልትና ነውና በከንቱ እንዴት ታጽናኑኛላችሁ? |
| ← Job (21/42) → |