| ← Job (20/42) → |
| 1. | ናዕማታዊውም ሶፋር መለሰ እንዲህም አለ። |
| 2. | ስለዚህ በውስጤ ስላለው ችኰላ አሳቤ ትመልስልኛለች። |
| 3. | የሚያሳፍረኝንም ተግሣጽ ሰምቻለሁ፥ የማስተዋሌም መንፈስ ይመልስልኛል። |
| 4. | ሰው በምድር ላይ ከተቀመጠ፥ ከዱሮ ዘመን ጀምሮ፥ |
| 5. | የኃጢአተኛ ፉከራ አጭር መሆኑን የዝንጉዎችም ደስታ ቅጽበት መሆኑን አታውቁምን? |
| 6. | ከፍታው ወደ ሰማይ ቢወጣ፥ ራሱም እስከ ደመና ቢደርስ፥ |
| 7. | እንደ ፋንድያ ለዘላለም ይጠፋል፤ ያዩትም። ወዴት ነው? ይላሉ። |
| 8. | እንደ ሕልም ይበርራል፥ እርሱም አይገኝም፤ እንደ ሌሊትም ራእይ ይሰደዳል። |
| 9. | ያየችውም ዓይን ዳግመኛ አታየውም፤ ስፍራውም ከእንግዲህ ወዲህ አይመለከተውም። |
| 10. | ልጆቹ ድሆቹን ያቈላምጣሉ፤ እጁ ሀብቱን ይመልሳል። |
| 11. | አጥንቶቹ ብላቴንነቱን ሞልተዋል፤ ነገር ግን ከእርሱ ጋር በመሬት ውስጥ ይተኛል። |
| 12. | ክፋት በአፉ ውስጥ ቢጣፍጥ፥ ከምላሱም በታች ቢሰውረው፥ |
| 13. | ቢጠብቀውም ባይተወውም፥ በጕሮሮውም ቢይዘው፥ |
| 14. | መብሉ በአንጀቱ ውስጥ ይገላበጣል፤ እንደ እፉኝትም ሐሞት በውስጡ ይሆናል። |
| 15. | የዋጠውን ሀብት ይተፋዋል፤ እግዚአብሔርም ከሆዱ ውስጥ ያወጣዋል። |
| 16. | የእፉኝትን መርዝ ይጠባል፤ የእባብም ምላስ ይገድለዋል። |
| 17. | የማሩንና የቅቤውን ፈሳሽ ወንዞቹንም አይመለከትም። |
| 18. | የድካሙን ፍሬ ሳይውጠው ይመልሰዋል፤ እንደ ንግዱም ትርፍ አይደሰትም። |
| 19. | ድሀውን አስጨንቆአል፥ ትቶታልም፤ ያልሠራውንም ቤት በዝብዞአል። |
| 20. | ሆዱ ዕረፍትን አላወቀምና የወደደው ነገር አላዳነውም። |
| 21. | እርሱ ከበላ በኋላ ምንም አልተረፈም፤ ስለዚህ በረከቱ አይከናወንለትም። |
| 22. | በጠገበ ጊዜ ይጨነቃል፤ የችግረኞችም ሁሉ እጅ ታገኘዋለች። |
| 23. | ሆዱን ሳያጠግብ እግዚአብሔር የቍጣውን ትኵሳት ይሰድድበታል፥ ሲበላም ያዘንብበታል። |
| 24. | ከብረት መሣርያም ይሸሻል፥ የናስም ቀስት ይወጋዋል። |
| 25. | እርሱም ይመዝዘዋል፥ ከሥጋውም ይወጣል፤ ከሐሞቱም ብልጭ ብሎ ይሠርጻል፤ ፍርሃትም ይወድቅበታል። |
| 26. | ጨለማ ሁሉ ስለ ከበረው ዕቃ ተዘጋጅቶአል፤ በሰው አፍ እፍ የማትባል እሳት ትበላዋለች፤ በድንኳኑ ውስጥ የቀረው ይጨነቅባታል። |
| 27. | ሰማይ ኃጢአቱን ይገልጥበታል፥ ምድርም ትነሣበታለች። |
| 28. | የቤቱም ባለጠግነት ይሄዳል፤ በቍጣው ቀን እንደ ፈሳሽ ውኃ ያልፋል። |
| 29. | ከእግዚአብሔር ዘንድ የበደለኛ ሰው እድል ፈንታ፥ ከእግዚአብሔርም የተመደበ ርስቱ ይህ ነው። |
| ← Job (20/42) → |