← Job (18/42) → |
1. | ሹሐዊውም በልዳዶስ መለሰ እንዲህም አለ። |
2. | እስከ መቼ ቃልን ታጠምዳለህ? አስተውል፥ ከዚያም በኋላ እንናገራለን። |
3. | ስለ ምንስ እንደ እንስሶች ተቈጠርን? ስለ ምንስ በዓይንህ ፊት ረከስን? |
4. | ቍጣ ወርሶሃል፤ አንተስ የሞትህ እንደ ሆነ፥ ምድር ስለ አንተ ባድማ ትሆናለችን? ወይስ ዓለት ከስፍራው ይነቀላልን? |
5. | የኃጢአተኛ መብራት ይጠፋል፥ የእሳቱም ነበልባል ብልጭ አይልም። |
6. | ብርሃን በድንኳኑ ውስጥ ይጨልማል፥ መብራቱም በላዩ ይጠፋል። |
7. | የኃይሉም እርምጃ ትጠብባለች፥ ምክሩም ትጥለዋለች። |
8. | እግሩ በወጥመድ ትያዛለች፥ በመረብም ላይ ይሄዳል። |
9. | አሽክላ ሰኰናውን ይይዛል፥ ወስፈንጠርም ይበረታበታል። |
10. | በምድር ላይ የሸምቀቆ ገመድ፥ በመንገዱም ላይ ወጥመድ ለእርሱ ተሰውራለች። |
11. | ድንጋጤ በዙሪያው ታስፈራዋለች፥ በስተ ኋላውም ሆና ታባርራቸዋለች። |
12. | ኃይሉ በራብ ትደክማለች፥ መቅሠፍትም እስኪሰናከል ተዘጋጅቶለታል። |
13. | የሰውነቱ ብልቶች ይጠፋሉ፤ የሞትም በኵር ልጅ ብልቶቹን ይበላል። |
14. | ከሚታመንበት ድንኳን ይነቀላል፤ ወደ ድንጋጤም ንጉሥ ያስቸኵሉታል። |
15. | በድንኳኑ ውስጥ ለእርሱ የማይሆነው ይኖራል፤ በመኖሪያውም ላይ ዲን ይበተናል። |
16. | ሥሩ ከበታቹ ይደርቃል፥ ጫፉም ከበላይ ይረግፋል። |
17. | መታሰቢያው ከምድር ላይ ይጠፋል፥ በሜዳም ስም አይቀርለትም። |
18. | ከብርሃን ወደ ጨለማ ያፈልሱታል፥ ከዓለምም ያሳድዱታል። |
19. | ዘርም ትውልድም በሕዝቡ መካከል አይሆንለትም፤ በመኖሪያውም ውስጥ የሚቀመጥ ሰው አይቀርለትም። |
20. | የፊተኞች ሰዎች እንደ ደነገጡ፥ እንዲሁ የኋለኞች ሰዎች ስለ ዘመኑ ይደነቃሉ። |
21. | በእውነት የኃጢአተኞች ቤት እንዲሁ ናት፥ እግዚአብሔርንም የማያውቅ ሰው ስፍራ ይህ ነው። |
← Job (18/42) → |