| ← Job (16/42) → |
| 1. | ኢዮብም መለሰ እንዲህም አለ። |
| 2. | እንደዚህ ያለ ዓይነት ነገር እጅግ ሰማሁ፤ እናንተ ሁላችሁ የምታደክሙ አጽናኞች ናችሁ። |
| 3. | በውኑ ከንቱ ቃል ይፈጸማልን? ወይስ ትመልስ ዘንድ ያነሣሣህ ምንድር ነው? |
| 4. | እኔ ደግሞ እንደ እናንተ እናገር ዘንድ ይቻለኝ ነበር፤ ነፍሳችሁ በነፍሴ ፋንታ ቢሆን ኖሮ፥ እኔ በእናንተ ላይ ቃል ማሳካት፥ ራሴንም በእናንተ ላይ መነቅነቅ በተቻለኝ ነበር። |
| 5. | በአፌም ነገር ባበረታኋችሁ ነበር፤ የከንፈሬን ማጽናናት ባልከለከልሁም ነበር። |
| 6. | እኔ ብናገር ሕማሜ አይቀነስም፤ ዝምም ብል ከእኔ አይወገድም። |
| 7. | አሁን ግን አድክሞኛል፤ ወገኔንም ሁሉ አፍርሰሃል። |
| 8. | መጨማተሬ ይመሰክርብኛል፤ ክሳቴም ተነሥቶብኛል፤ በፊቴም ይመሰክርብኛል። |
| 9. | በቍጣው ቀደደኝ፥ እርሱም ጠላኝ፤ ጥርሶቹንም አፋጨብኝ፤ ጠላቴ ዓይኑን አፈጠጠብኝ፤ |
| 10. | እነርሱም አፋቸውን ከፈቱብኝ፤ እያላገጡ ጕንጬን ጠፈጠፉኝ፤ በአንድነትም ተሰበሰቡብኝ። |
| 11. | እግዚአብሔር ለጠማማ ሰው አሳልፎ ሰጠኝ፥ በክፉዎችም እጅ ጣለኝ። |
| 12. | ተዘልዬ ተቀምጬ ነበር፥ እርሱም ሰበረኝ፤ አንገቴንም ይዞ ቀጠቀጠኝ፤ እንደ ዓላማ አድርጎ አቆመኝ። |
| 13. | ቀስተኞቹ ከበቡኝ፤ ኵላሊቴንም ቈራረጠ፥ እርሱም አልራራም፤ ሐሞቴን በምድር ላይ አፈሰሰ። |
| 14. | በቍስል ላይ ቍስል ጨመረብኝ፤ እንደ ኃያል እየሠገገ ይሮጥብኛል። |
| 15. | በቁርበቴ ላይ ማቅ ሰፋሁ፥ ቀንዴንም በመሬት ላይ አኖርሁ። |
| 16. | ፊቴ ከልቅሶ የተነሣ ቀላ፤ የሞት ጥላ በዓይኖቼ ቆብ ላይ አለ፤ |
| 17. | ነገር ግን በእጄ ዓመፅ የለም፤ ጸሎቴም ንጹሕ ነው። |
| 18. | ምድር ሆይ፥ ደሜን አትክደኚ፥ ለጩኸቴም ማረፊያ አይሁን። |
| 19. | አሁንም፥ እነሆ፥ ምስክሬ በሰማይ አለ፥ የሚመሰክርልኝም በአርያም ነው። |
| 20. | ጸሎቴ ወደ እግዚአብሔር ይድረስ፥ ዓይኔም በፊቱ እንባ ታፍስስ። |
| 21. | የሰው ልጅ ከባልንጀራው ጋር እንደሚምዋገት፥ ሰው በእግዚአብሔር ፊት ለመምዋገት ምነው በቻለ! |
| 22. | ጥቂቶች ዓመታት ካለፉ በኋላ እኔ ወደማልመለስበት መንገድ እሄዳለሁ። |
| ← Job (16/42) → |