← Job (13/42) → |
1. | እነሆ፥ ይህን ሁሉ ዓይኔ አየች፤ ጆሮዬም ሰምታ አስተዋለችው። |
2. | እናንተ የምታውቁትን እኔ ደግሞ አውቃለሁ፤ ከእናንተ የማንስ አይደለሁም። |
3. | ነገር ግን ሁሉን ለሚችል አምላክ መናገር እፈልጋለሁ፥ ከእግዚአብሔርም ጋር ለመዋቀስ እሻለሁ። |
4. | እናንተ ግን በሐሰት ለባጮች ናችሁ፤ ሁላችሁ የማትጠቅሙ ባለ መድኃኒቶች ናችሁ። |
5. | ምነው ዝም ብላችሁ ብትኖሩ! ይህ ጥበብ በሆነላችሁ ነበር። |
6. | አሁንም ክርክሬን ስሙ፥ የከንፈሬንም ሙግት አድምጡ። |
7. | በውኑ ስለ እግዚአብሔር ሐሰትን ትናገራላችሁን? ስለ እርሱም ሽንገላን ታወራላችሁን? |
8. | ለፊቱስ ታደላላችሁን? ስለ እግዚአብሔርስ ትከራከራላችሁን? |
9. | ቢመረምራችሁስ መልካም ይሆንልችኋልን? ወይስ በሰው እንደምትሳለቁ ትሳለቁበታላችሁን? |
10. | በስውር ለሰው ፊት ብታደሉ ዘለፋ ይዘልፋችኋል። |
11. | ክብሩስ አያስፈራችሁምን? ግርማውስ አይወድቅባችሁምን? |
12. | ምስሌዎቻችሁ የአመድ ምሳሌዎች ናቸው፤ ምሽጎቻችሁ የጭቃ ምሽጎች ናቸው። |
13. | ዝም በሉ፥ እናገርም ዘንድ ተዉኝ፤ የሆነው ነገር ይምጣብኝ። |
14. | ሥጋዬን በጥርሴ እይዛለሁ፥ ሕይወቴንም በእጄ አኖራለሁ። |
15. | እነሆ፥ ቢገድለኝ ስንኳ እርሱን በትዕግሥት እጠባበቃለሁ፤ ነገር ግን መንገዴን በፊቱ አጸናለሁ። |
16. | ዝንጉ ሰው በፊቱ አይገባምና እርሱ መድኃኒት ይሆንልኛል። |
17. | ነገሬን ተግታችሁ ስሙ፥ ምስክርነቴንም በጆሮአችሁ አድምጡ። |
18. | እነሆ፥ ሙግቴን አዘጋጅቻለሁ። እንደምጸድቅም አውቃለሁ። |
19. | ከእኔስ ጋር የሚፋረድ ማን ነው? አሁን እኔ ዝም ብል እሞታለሁ። |
20. | ነገር ግን ሁለት ነገር አታድርግብኝ፤ የዚያን ጊዜ ከፊትህ አልሰወርም፤ |
21. | እጅህን ከእኔ አርቅ፤ ግርማህም አታስደንግጠኝ። |
22. | ከዚያም በኋላ ጥራኝ፥ እኔም እመልስልሃለሁ። ወይም እኔ ልናገር፥ አንተም መልስልኝ። |
23. | ያለብኝስ በደልና ኃጢአት ምን ያህል ነው? መተላለፌንና ኃጢአቴን አስታውቀኝ። |
24. | ፊትህን ከእኔ የሰወርህ፥ እንደ ጠላትህም የቈጠርኸኝ ስለ ምን ነው? |
25. | የረገፈውን ቅጠል ታስጨንቃለህን? ወይስ የደረቀውን ዕብቅ ታሳድዳለህን? |
26. | የመረረ ነገር ጽፈህብኛልና፤ የሕፃንነቴንም ኃጢአት ታወርሰኛለህ። |
27. | እግሬንም በእግር ግንድ አግብተሃል፥ መንገዴንም ሁሉ መርምረሃል፤ የእግሬን ፍለጋ ወስነሃል። |
28. | እኔ እንደሚጠፋ በስባሳ ነገር፥ ብልም እንደሚበላው ልብስ ነኝ። |
← Job (13/42) → |