← Job (12/42) → |
1. | ኢዮብም መለሰ እንዲህም አለ። |
2. | በእርግጥ እናንተ ዓይነተኞች ሰዎች ናቸሁ፤ ጥበብም ከእናንተ ጋር ይሞታል። |
3. | ነገር ግን እኔ ደግሞ እንደ እናንተ ማስተዋል አለኝ፤ ከእናንተም የማንስ አይደለሁም፤ እንደዚህ ያለውን ነገር የማያውቅ ማን ነው? |
4. | እግዚአብሔርን የጠራሁ እርሱም የመለሰልኝ እኔ ለባልንጀራው መሳለቂያ እንደሚሆን ሰው ሆኛለሁ፤ ጻድቅና ፍጹም ሰው መሳለቂያ ሆኖአል። |
5. | ተዘልሎ በሚቀመጥ ሰው አሳብ መከራ ይናቃል፤ ነገር ግን እግሩን ሊያድጠው ተዘጋጅቶአል። |
6. | የቀማኞች ድንኳን በደኅንነት ይኖራል፥ እግዚአብሔርንም የሚያስቈጡ ተዘልለው ተቀምጠዋል፤ እግዚአብሔር ሁሉን በእጃቸው አምጥቶላቸዋል። |
7. | አሁን ግን እንስሶችን ጠይቅ፥ ያስተምሩህማል፤ የሰማይንም ወፎች ጠይቅ፥ ይነግሩህማል። |
8. | ወይም ለምድር ተናገር፥ እርስዋም ታስተምርሃለች፤ የባሕርም ዓሣዎች ይነግሩሃል። |
9. | የእግዚአብሔር እጅ ይህን እንዳደረገ ከእነዚህ ሁሉ የማያውቅ ማን ነው? |
10. | የሕያዋን ሁሉ ነፍስ የሰውም ሁሉ መንፈስ በእጁ ናት። |
11. | ምላስ መብልን እንደሚቀምስ፥ ጆሮ ቃልን የሚለይ አይደለምን? |
12. | በሽምግልና ጊዜ ጥበብ፥ በዘመንስ ርዝመት ማስተዋል ይገኛል። |
13. | በእግዚአብሔር ዘንድ ጥበብና ኃይል አለ፤ ለእርሱ ምክርና ማስተዋል አለው። |
14. | እነሆ፥ ይፈርሳል፥ የፈረሰውም ተመልሶ አይሠራም፤ በሰውም ቢዘጋበት የሚከፍትለት የለም። |
15. | እነሆ፥ ውኆቹን ይከለክላል፥ እነርሱም ይደርቃሉ፤ እንደ ገና ይሰድዳቸዋል፥ ምድሪቱንም ይገለብጣሉ። |
16. | ኃይልና ጥበብ በእርሱ ዘንድ ናቸው፤ የሚስተውና የሚያስተው ለእርሱ ናቸው። |
17. | መካሮችንም እንደ ዘረፋ ይወስዳቸዋል፥ ፈራጆችንም ያሳብዳል። |
18. | የነገሥታትንም እስራት ይፈታል፥ ወገባቸውንም በመታጠቂያ ያስራቸዋል። |
19. | ካህናትን እንደ ዘረፋ ይወስዳቸዋል፥ ኃያላንንም ይገለብጣቸዋል። |
20. | ከታመኑ ሰዎችም ቋንቋን ያርቃል፥ የሽማግሌዎችንም ማስተዋል ይወስድባቸዋል። |
21. | በአለቆች ላይ ንቀትን ያፈስሳል፥ የብርቱዎችንም መታጠቂያ ያላላል። |
22. | ጥልቅ ነገር ከጨለማ ይገልጣል፥ የሞትንም ጥላ ወደ ብርሃን ያወጣል። |
23. | አሕዛብን ከፍ ከፍ ያደርጋል፥ እነርሱንም ያጠፋል፤ አሕዛብንም ያሰፋል፥ እነርሱንም ያፈልሳቸዋል። |
24. | ከምድር አሕዛብ አለቆች ዘንድ ማስተዋልን ይወስዳል፥ መንገድም በሌለበት በረሃ ያቅበዘብዛቸዋል። |
25. | ብርሃንም ሳይኖር በጨለማ ይርመሰመሳሉ፤ እንደ ሰካራም ይቅበዘበዛሉ። |
← Job (12/42) → |