| ← Job (10/42) → |
| 1. | ነፍሴ ሕይወቴን ሰለቸቻት፤ የኀዘን እንጕርጕሮዬን እለቀዋለሁ፤ በነፍሴም ምሬት እናገራለሁ። |
| 2. | እግዚአብሔርን እንዲህ እለዋለሁ። አትፍረድብኝ፤ የምትከራከረኝ ለምን እንደ ሆነ ንገረኝ። |
| 3. | ልታስጨንቅና የእጅህን ሥራ ልትንቅ የኃጥአንንስ ምክር ልታበራ በአንተ ዘንድ መልካም ነውን? |
| 4. | በውኑ የሥጋ ዓይን አለህን? ወይስ ሰው እንደሚያይ ታያለህን? |
| 6. | ወይስ ክፋቴን ትፈላለግ ዘንድ፥ ኃጢአቴንም ትመረምር ዘንድ፥ ዘመንህ እንደ ሰው ዘመን ነውን? ወይስ ዓመታትህ እንደ ሰው ዓመታት ናቸውን? |
| 7. | ከዚህም በላይ በደለኛ እንዳልሆንሁ፥ ከእጅህም የሚያድን እንደሌለ አንተ ታውቃለህ። |
| 8. | እጅህ ለወሰችኝ ሠራችኝም፤ ከዚያም በኋላ ዞረህ ታጠፋኝ ዘንድ ፈለግህ። |
| 9. | እንደ ጭቃ አድርገህ እንደ ለወስኸኝ አስብ፤ ወደ ትቢያም ትመልሰኛለህን? |
| 10. | በውኑ እንደ ወተት አላፈሰስኸኝምን? እንደ እርጎስ አላረጋኸኝምን? |
| 11. | ቁርበትና ሥጋ አለበስኸኝ፥ በአጥንትና በጅማትም አጠንከርኸኝ። |
| 12. | ሕይወትና ቸርነት አደረግህልኝ፤ መጐብኘትህም መንፈሴን ጠበቀች። |
| 13. | እነዚህንም ነገሮች በልብህ ውስጥ ሰወርህ። ይህ ሁሉ በአሳብህ እንዳለ አውቃለሁ። |
| 14. | ኃጢአት ብሠራ አንተ ትመለከተኛለህ፤ ከኃጢአቴም ንጹሕ አታደርገኝም። |
| 15. | በደለኛ ብሆን ወዮልኝ፤ ጻድቅም ብሆን ራሴን አላነሣም፤ ጕስቍልናን ተሞልቻለሁ፥ መከራዬንም ተመልክቻለሁ። |
| 16. | ራሴም ከፍ ከፍ ቢል እንደ አንበሳ ታድነኛለህ፤ ተመልሰህም ድንቅ ነገር ታድርግብኛለህ |
| 17. | ምስክሮችህን ታድስብኛለህ፤ ቍጣህንም ታበዛብኛለህ፤ ጭፍራ በጭፍራ ላይ ትጨምርብኛለህ። |
| 18. | ስለ ምን ከማኅፀን አወጣኸኝ? ዓይን ሳያየኝ ምነው በሞትሁ። |
| 19. | እንዳልነበረ በሆንሁ፤ ከማኅፀንም ወደ መቃብር በወሰዱኝ። |
| 20. | የሕይወቴ ዘመን ጥቂት አይደለምን? |
| 21. | ወደማልመለስበት ስፍራ፥ ወደ ጨለማና ወደ ሞት ጥላ ምድር፥ |
| 22. | እንደ ጨለማም ወደ ጨለመች፥ ሥርዓትም ወደሌለባት ወደ ሞት ጥላ፥ ብርሃንዋም እንደ ጨለማ ወደ ሆነ ምድር ሳልሄድ፥ ጥቂት እጽናና ዘንድ ተወኝ፥ ልቀቀኝም። |
| ← Job (10/42) → |