| ← James (5/5) |
| 1. | አሁንም እናንተ ባለ ጠጎች፥ ስለሚደርስባችሁ ጭንቅ ዋይ ዋይ እያላችሁ አልቅሱ። |
| 2. | ሀብታችሁ ተበላሽቶአል፥ ልብሳችሁም በብል ተበልቶአል። |
| 3. | ወርቃችሁም ብራችሁም ዝጎአል፥ ዝገቱም ምስክር ይሆንባችኋል ሥጋችሁንም እንደ እሳት ይበላል። ለኋለኛው ቀን መዝገብን አከማችታችኋል። |
| 4. | እነሆ፥ እርሻችሁን ያጨዱት የሠራተኞች ደመወዝ በእናንተ ተቀምቶ ይጮኻል፥ የአጫጆችም ድምፅ ወደ ጌታ ፀባዖት ጆሮ ገብቶአል። |
| 5. | በምድር ላይ ተቀማጥላችኋል በሴሰኝነትም ኖራችኋል፤ ለእርድ ቀን እንደሚያወፍር ልባችሁን አወፍራችኋል። |
| 6. | ጻድቁን ኰንናችሁታል ገድላችሁትማል፤ እናንተን አይቃወምም። |
| 7. | እንግዲህ፥ ወንድሞች ሆይ፥ ጌታ እስኪመጣ ድረስ ታገሡ። እነሆ፥ ገበሬው የፊተኛውንና የኋለኛውን ዝናብ እስኪቀበል ድረስ እርሱን እየታገሠ የከበረውን የመሬት ፍሬ ይጠብቃል። |
| 8. | እናንተ ደግሞ ታገሡ፥ ልባችሁንም አጽኑ፤ የጌታ መምጣት ቀርቦአልና። |
| 9. | ወንድሞች ሆይ፥ እንዳይፈረድባችሁ እርስ በርሳችሁ አታጉረምርሙ፤ እነሆ፥ ፈራጅ በደጅ ፊት ቆሞአል። |
| 10. | ወንድሞች ሆይ፥ የመከራና የትዕግሥት ምሳሌ የሆኑትን በጌታ ስም የተናገሩትን ነቢያትን ተመልከቱ። |
| 11. | እነሆ፥ በትዕግሥት የጸኑትን ብፁዓን እንላቸዋለን፤ ኢዮብ እንደ ታገሠ ሰምታችኋል፥ ጌታም እንደ ፈጸመለት አይታችኋል፤ ጌታ እጅግ የሚምር የሚራራም ነውና። |
| 12. | ከሁሉም በፊት፥ ወንድሞቼ ሆይ፥ በሰማይ ቢሆን በምድርም ቢሆን በሌላ መሐላም ቢሆን በምንም አትማሉ፤ ነገር ግን ከፍርድ በታች እንዳትወድቁ ነገራችሁ አዎን ቢሆን አዎን ይሁን፥ አይደለምም ቢሆን አይደለም ይሁን። |
| 13. | ከእናንተ መከራን የሚቀበል ማንም ቢኖር እርሱ ይጸልይ፤ ደስ የሚለውም ማንም ቢኖር እርሱ ይዘምር። |
| 14. | ከእናንተ የታመመ ማንም ቢኖር የቤተ ክርስቲያንን ሽምግሌዎች ወደ እርሱ ይጥራ፤ በጌታም ስም እርሱን ዘይት ቀብተው ይጸልዩለት። |
| 15. | የእምነትም ጸሎት ድውዩን ያድናል ጌታም ያስነሣዋል፤ ኃጢአትንም ሠርቶ እንደ ሆነ ይሰረይለታል። |
| 16. | እርስ በርሳችሁ በኃጢአታችሁ ተናዘዙ። ትፈወሱም ዘንድ እያንዳንዱ ስለ ሌላው ይጸልይ፤ የጻድቅ ሰው ጸሎት በሥራዋ እጅግ ኃይል ታደርጋለች። |
| 17. | ኤልያስ እንደ እኛ የሆነ ሰው ነበረ፥ ዝናብም እንዳይዘንብ አጥብቆ ጸለየ፥ በምድርም ላይ ሦስት ዓመት ከስድስት ወር አልዘነበም፤ ሁለተኛም ጸለየ፥ |
| 18. | ሰማዩም ዝናብን ሰጠ ምድሪቱም ፍሬዋን አበቀለች። |
| 19. | ወንድሞቼ ሆይ፥ ከእናንተ ማንም ከእውነት ቢስት አንዱም ቢመልሰው፥ |
| 20. | ኃጢአተኛን ከተሳሳተበት መንገድ የሚመልሰው ነፍሱን ከሞት እንዲያድን፥ የኃጢአትንም ብዛት እንዲሸፍን ይወቅ። |
| ← James (5/5) |