| ← James (3/5) → |
| 1. | ወንድሞቼ ሆይ፥ ከእናንተ ብዙዎቹ አስተማሪዎች አይሁኑ፥ የባሰውን ፍርድ እንድንቀበል ታውቃላችሁና። |
| 2. | ሁላችን በብዙ ነገር እንሰናከላለንና፤ በቃል የማይሰናከል ማንም ቢኖር እርሱ ሥጋውን ሁሉ ደግሞ ሊገታ የሚችል ፍጹም ሰው ነው። |
| 3. | እነሆ፥ ፈረሶች ይታዘዙልን ዘንድ ልጓም በአፋቸው ውስጥ እናገባለን፥ ሥጋቸውንም ሁሉ እንመራለን። |
| 4. | እነሆ፥ መርከቦች ደግሞ ይህን ያህል ታላቅ ቢሆኑ በዐውሎ ነፋስም ቢነዱ፥ የመሪ ፈቃድ ወደሚወደው ስፍራ እጅግ ታናሽ በሆነ መቅዘፊያ ይመራሉ። |
| 5. | እንዲሁም አንደበት ደግሞ ትንሽ ብልት ሆኖ በታላላቅ ነገር ይመካል። እነሆ፥ ትንሽ እሳት እንዴት ያለ ትልቅ ጫካ ያቃጥላል። |
| 6. | አንደበትም እሳት ነው። አንደበት በብልቶቻችን መካከል ዓመፀኛ ዓለም ሆኖአል፤ ሥጋን ሁሉ ያሳድፋልና፥ የፍጥረትንም ሩጫ ያቃጥላል፥ በገሃነምም ይቃጠላል። |
| 7. | የአራዊትና የወፎች የተንቀሳቃሾችና በባሕር ያለ የፍጥረት ወገን ሁሉ በሰው ይገራል፥ ደግሞ ተገርቶአል፤ |
| 8. | ነገር ግን አንደበትን ሊገራ ማንም ሰው አይችልም፤ የሚገድል መርዝ የሞላበት ወላዋይ ክፋት ነው። |
| 9. | በእርሱ ጌታንና አብን እንባርካለን፤ በእርሱም እንደ እግዚአብሔር ምሳሌ የተፈጠሩትን ሰዎች እንረግማለን፤ |
| 10. | ከአንድ አፍ በረከትና መርገም ይወጣሉ። ወንድሞቼ ሆይ፥ ይህ እንዲህ ሊሆን አይገባም። |
| 11. | ምንጭስ ከአንድ አፍ የሚጣፍጥንና የሚመርን ውኃ ያመነጫልን? |
| 12. | ወንድሞቼ ሆይ፥ በለስ ወይራን ወይስ ወይን በለስን ልታፈራ ትችላለችን? ከጨው ውኃም ጣፋጭ ውኃ አይወጣም። |
| 13. | ከእናንተ ጥበበኛና አስተዋይ ማን ነው? በመልካም አንዋዋሩ ስራውን በጥበብ የዋህነት ያሳይ። |
| 14. | ነገር ግን መራራ ቅንዓትና አድመኛነት በልባችሁ ቢኖርባችሁ፥ አትመኩ በእውነትም ላይ አትዋሹ። |
| 15. | ይህ ጥበብ ከላይ የሚወርድ አይደለም፤ ነገር ግን የምድር ነው፥ የሥጋም ነው፥ የአጋንንትም ነው፤ |
| 16. | ቅንዓትና አድመኛነት ባሉበት ስፍራ በዚያ ሁከትና ክፉ ስራ ሁሉ አሉና። |
| 17. | ላይኛይቱ ጥበብ ግን በመጀመሪያ ንጽሕት ናት፥ በኋላም ታራቂ፥ ገር፥ እሺ ባይ ምሕረትና በጎ ፍሬ የሞላባት፥ ጥርጥርና ግብዝነት የሌለባት ናት። |
| 18. | የጽድቅም ፍሬ ሰላምን ለሚያደርጉት ሰዎች በሰላም ይዘራል። |
| ← James (3/5) → |