← James (2/5) → |
1. | ወንድሞቼ ሆይ፥ በክብር ጌታ በጌታችን በኢየሱስ ክርስቶስ ያለውን እምነት ለሰው ፊት በማድላት አትያዙ። |
2. | የወርቅ ቀለበት ያደረገና የጌጥ ልብስ የለበሰ ሰው ወደ ጉባኤአችሁ ቢገባ፥ እድፍ ልብስም የለበሰ ድሀ ሰው ደግሞ ቢገባ፥ |
3. | የጌጥ ልብስም የለበሰውን ተመልክታችሁ። አንተስ በዚህ በመልካም ስፍራ ተቀመጥ ብትሉት፥ ድሀውንም። አንተስ ወደዚያ ቁም ወይም ከእግሬ መረገጫ በታች ተቀመጥ ብትሉት፥ ራሳችሁን መለያየታችሁ አይደለምን? |
4. | ክፉ አሳብ ያላቸውም ዳኞች መሆናችሁ አይደለምን? |
5. | የተወደዳችሁ ወንድሞቼ ሆይ፥ ስሙ፤ እግዚአብሔር በእምነት ባለ ጠጎች እንዲሆኑ ለሚወዱትም ተስፋ ስለ እርሱ የሰጣቸውን መንግሥት እንዲወርሱ የዚህን ዓለም ድሆች አልመረጠምን? |
6. | እናንተ ግን ድሆችን አዋረዳችሁ። ባለ ጠጎቹ የሚያስጨንቁአችሁ አይደሉምን? ወደ ፍርድ ቤትም የሚጎትቱአችሁ እነርሱ አይደሉምን? |
7. | የተጠራችሁበትን መልካሙን ስም የሚሰድቡ እነርሱ አይደሉምን? |
8. | ነገር ግን መጽሐፍ። ባልንጀራህን እንደ ራስህ ውደድ እንደሚል የንጉሥን ሕግ ብትፈጽሙ መልካም ታደርጋላችሁ፤ |
9. | ለሰው ፊት ግን ብታደሉ ኃጢአትን ትሠራላችሁ፥ ሕግም እንደ ተላላፊዎች ይወቅሳችኋል። |
10. | ሕግን ሁሉ የሚጠብቅ፥ ነገር ግን በአንዱ የሚሰናከል ማንም ቢኖር በሁሉ በደለኛ ይሆናል፤ አታመንዝር ያለው ደግሞ። አትግደል ብሎአልና፤ |
11. | ባታመነዝርም፥ ነገር ግን ብትገድል፥ ሕግን ተላላፊ ሆነሃል። |
12. | በነጻነት ሕግ ፍርድን ይቀበሉ ዘንድ እንዳላቸው ሰዎች እንዲህ ተናገሩ፥ እንዲህም አድርጉ። |
13. | ምሕረትን ለማያደርግ ምሕረት የሌለበት ፍርድ ይሆናልና፤ ምሕረትም በፍርድ ላይ ይመካል። |
14. | ወንድሞቼ ሆይ፥ እምነት አለኝ የሚል፥ ሥራ ግን የሌለው ሰው ቢኖር ምን ይጠቅመዋል? እምነቱስ ሊያድነው ይችላልን? |
15. | ወንድም ወይም እኅት ራቁታቸውን ቢሆኑ የዕለት ምግብንም ቢያጡ፥ |
16. | ከእናንተ አንዱም። በደኅና ሂዱ፥ እሳት ሙቁ፥ ጥገቡም ቢላቸው ለሰውነት ግን የሚያስፈልጉትን ባትሰጡአቸው ምን ይጠቅማቸዋል? |
17. | እንደዚሁም ሥራ የሌለው እምነት ቢኖር በራሱ የሞተ ነው። |
18. | ነገር ግን አንድ ሰው። አንተ እምነት አለህ እኔም ሥራ አለኝ፤ እምነትህን ከሥራህ ለይተህ አሳየኝ፥ እኔም እምነቴን በሥራዬ አሳይሃለሁ ይላል። |
19. | እግዚአብሔር አንድ እንደ ሆነ አንተ ታምናለህ፤ መልካም ታደርጋለህ፤ አጋንንት ደግሞ ያምናሉ ይንቀጠቀጡማል። |
20. | አንተ ከንቱ ሰው፥ እምነት ከሥራ ተለይቶ የሞተ መሆኑን ልታውቅ ትወዳለህን? |
21. | አባታችን አብርሃም ልጁን ይስሐቅን በመሠዊያው ባቀረበ ጊዜ በሥራ የጸደቀ አልነበረምን? |
22. | እምነት ከሥራው ጋር አብሮ ያደርግ እንደ ነበረ፥ በሥራም እምነት እንደ ተፈጸመ ትመለከታለህን? |
23. | መጽሐፍም። አብርሃምም እግዚአብሔርን አመነ ጽድቅም ሆኖ ተቈጠረለት ያለው ተፈጸመ፤ የእግዚአብሔርም ወዳጅ ተባለ። |
24. | ሰው በእምነት ብቻ ሳይሆን በሥራ እንዲጸድቅ ታያላችሁ። |
25. | እንደዚሁም ጋለሞታይቱ ረዓብ ደግሞ መልእክተኞቹን ተቀብላ በሌላ መንገድ በሰደደቻቸው ጊዜ በሥራ አልጸደቀችምን? |
26. | ከነፍስ የተለየ ሥጋ የሞተ እንደ ሆነ እንዲሁ ደግሞ ከሥራ የተለየ እምነት የሞተ ነው። |
← James (2/5) → |