← Isaiah (9/66) → |
1. | ነገር ግን ተጨንቃ ለነበረች ጨለማ አይሆንም። በመጀመሪያው ዘመን የዛብሎንንና የንፍታሌምን ምድር አቃለለ፤ በኋለኛው ዘመን ግን በዮርዳኖስ ማዶ በባሕር መንገድ ያለውን የአሕዛብን ገሊላ ያከብራል። |
2. | በጨለማ የሄደ ሕዝብ ብርሃን አየ፤ በሞት ጥላ አገርም ለኖሩ ብርሃን ወጣላቸው። |
3. | ሕዝብን አብዝተሃል፥ ደስታንም ጨምረህላቸዋል፤ በመከር ደስ እንደሚላቸው፥ ሰዎችም ምርኮን ሲካፈሉ ደስ እንደሚላቸው በፊትህ ደስ ይላቸዋል። |
4. | በምድያም ጊዜ እንደ ሆነ የሸክሙን ቀንበር የጫንቃውንም በትር የአስጨናቂውንም ዘንግ ሰብረሃል። |
5. | የሚረግጡ የሰልፈኞች ጫማ ሁሉ፥ በደምም የተለወሰ ልብስ ለቃጠሎ ይሆናል፥ እንደ እሳት ማቃጠያም ሆኖ ይቃጠላል። |
6. | ሕፃን ተወልዶልናልና፥ ወንድ ልጅም ተሰጥቶናልና፤ አለቅነትም በጫንቃው ላይ ይሆናል፤ ስሙም ድንቅ መካር፥ ኃያል አምላክ፥ የዘላለም አባት፥ የሰላም አለቃ ተብሎ ይጠራል። |
7. | ከዛሬ ጀምሮ እስከ ዘላለም ድረስ በፍርድና በጽድቅ ያጸናውና ይደግፈው ዘንድ በዳዊት ዙፋንና በመንግሥቱ ላይ አለቅነቱ ይበዛል፥ ለሰላሙም ፍፃሜ የለውም። የእግዚአብሔር ቅንዓት ይህን ያደርጋል። |
8. | ጌታ በያዕቆብ ላይ ቃልን ሰደደ፥ በእስራኤልም ላይ ወደቀ። |
10. | በትዕቢትና በልብ ኵራት። ጡቡ ወድቆአል፥ ነገር ግን በተወቀረ ድንጋይ እንሠራለን፤ የሾላ ዛፎች ተቈርጠዋል፥ ነገር ግን ዝግባን እንተካባቸዋለን የሚሉ በኤፍሬምና በሰማርያ የሚኖሩ ሕዝብ ሁሉ ያውቃሉ። |
11. | ስለዚህ እግዚአብሔር በጽዮን ተራራ ላይ ተቋቋሚ ያስነሣበታል፥ |
12. | ጠላቶቹን ሶርያውያንንም ከምሥራቅ፥ ፍልስጥኤማውያንንም ከምዕራብ ያንቀሳቅስበታል፤ እስራኤልንም በተከፈተ አፍ ይበሉታል። በዚህም ሁሉ እንኳ ቍጣው አልተመለሰችም፥ ነገር ግን እጁ ገና ተዘርግታ ትኖራለች። |
13. | ሕዝቡ ግን ወደ ቀሠፋቸው አልተመለሱም፥ የሠራዊትንም ጌታ እግዚአብሔርን አልፈለጉም። |
14. | ስለዚህ እግዚአብሔር ራስና ጅራትን፥ የሰሌኑን ቅርንጫፍና እንግጫውን በአንድ ቀን ከእስራኤል ይቆርጣል። |
15. | ሽማግሌውና ከበርቴው እርሱ ራስ ነው፤ በሐሰትም የሚያስተምር ነቢይ እርሱ ጅራት ነው። |
16. | ይህን ሕዝብ የሚመሩ ያስቱአቸዋል፤ ተመሪዎቹም ይጠፋሉ። |
17. | ሰው ሁሉ ዝንጉና ክፉ ሠሪ ነውና፥ አፍም ሁሉ ስንፍናን ይናገራልና ስለዚህ ጌታ በጕልማሶቻቸው ደስ አይለውም፥ ለድሀ አደጎቻቸውና ለመበለቶቻቸውም አይራራም። በዚህም ሁሉ እንኳ ቍጣው አልተመለሰችም፥ ነገር ግን እጁ ገና ተዘርግታ ትኖራለች። |
18. | ክፋት እንደ እሳት ይቃጠላል፤ ኵርንችቱንና እሾሁን ይበላል፤ ጭፍቅ የሆነውንም ዱር ያቃጥላል፥ ጢሱም ተትጐልጕሎ እንደ ዓምድ ይወጣል። |
19. | በሠራዊት ጌታ በእግዚአብሔር ቍጣ ምድር ተቃጥላለች፤ ሕዝቡም እሳት እንደሚበላው እንጨት ሆኖአል፤ ሰውም ለወንድሙ አይራራም። |
20. | ሰው በቀኙ በኩል ይነቅላል ይራብማል፤ በግራም በኩል ይበላል አይጠግብምም፤ እያንዳንዱም የክንዱን ሥጋ ይበላል፤ |
21. | ምናሴ ኤፍሬምን ኤፍሬምም ምናሴን ይበላል፤ እነርሱ በአንድነት የይሁዳ ጠላቶች ይሆናሉ። በዚህም ሁሉ እንኳ ቍጣው አልተመለሰችም፥ ነገር ግን እጁ ገና ተዘርግታ ትኖራለች። |
← Isaiah (9/66) → |