← Isaiah (7/66) → |
1. | እንዲህም ሆነ፤ በይሁዳ ንጉሥ በዖዝያን ልጅ በኢዮአታም ልጅ በአካዝ ዘመን የሶርያ ንጉሥ ረአሶን የእስራኤልም ንጉሥ የሮሜልዩ ልጅ ፋቁሔ ኢየሩሳሌምን ሊወጉ ወጡ፥ ሊያሸንፉአትም አልቻሉም። |
2. | ለዳዊትም ቤት። ሶርያ ከኤፍሬም ጋር ተባብረዋል የሚል ወሬ ተነገረ፤ የእርሱም ልብ የሕዝቡም ልብ የዱር ዛፍ በነፋስ እንድትናወጥ ተናወጠ። |
3. | እግዚአብሔርም ኢሳይያስን አለው። አንተና ልጅህ ያሱብ አካዝን ትገናኙት ዘንድ በልብስ አጣቢው እርሻ መንገድ ወዳለው ወደ ላይኛው የኵሬ መስኖ ጫፍ ውጡ፤ |
4. | እንዲህም በለው። ተጠበቅ፥ ዝምም በል፤ ስለ እነዚህ ስለሚጤሱ ስለ ሁለት የእንጨት ጠለሸቶች፥ ስለ ሶርያና ስለ ረአሶን ስለ ሮሜልዩም ልጅ ቍጣ አትፍራ፥ ልብህም አይድከም። |
6. | ሶርያና ኤፍሬም የሮሜልዩም ልጅ። ወደ ይሁዳ እንውጣ እናስጨንቀውም፥ እንስበረውም፥ የጣብኤልንም ልጅ እናንግሥበት ብለው ክፋት ስለ መከሩብህ፤ |
7. | ጌታ እግዚአብሔር እንዲህ ይላል። ይህ ምክር አይጸናምና አይሆንም። |
8. | የሶርያ ራስ ደማስቆ ነው፥ የደማስቆም ራስ ረአሶን ነው፤ በስድሳ አምስት ዓመት ውስጥ ኤፍሬም ይሰባበራልና ሕዝብ አይሆንም፤ |
9. | የኤፍሬምም ራስ ሰማርያ ነው፥ የሰማርያም ራስ የሮሜልዩ ልጅ ነው። ባታምኑ አትጸኑም። |
10. | እግዚአብሔርም ደግሞ አካዝን እንዲህ ብሎ ተናገረው። |
11. | ከጥልቁ ወይም ከከፍታው ቢሆን ከአምላክህ ከእግዚአብሔር ምልክትን ለምን። |
12. | አካዝም። አልለምንም፥ እግዚአብሔርንም አልፈታተንም አለ። |
13. | እርሱም አለ። እናንተ የዳዊት ቤት ሆይ፥ ስሙ፤ በውኑ ሰውን ማድከማችሁ ቀላል ነውን? አምላኬን ደግሞ የምታደክሙ፤ |
14. | ስለዚህ ጌታ ራሱ ምልክት ይሰጣችኋል፤ እነሆ፥ ድንግል ትፀንሳለች፥ ወንድ ልጅም ትወልዳለች፥ ስሙንም አማኑኤል ብላ ትጠራዋለች። |
15. | ክፉን ለመጥላት መልካሙንም ለመምረጥ ሲያውቅ ቅቤና ማር ይበላል። |
16. | ሕፃኑ ክፉን ለመጥላት መልካሙን ለመምረጥ ሳያውቅ የፈራሃቸው የሁለቱ ነገሥታት አገር ባድማ ትሆናለች። |
17. | እግዚአብሔርም ኤፍሬም ከይሁዳ ከተለየበት ቀን ጀምሮ ያልመጣውን ዘመን በአንተና በሕዝብህ በአባትህም ቤት ላይ ያመጣል፤ እርሱም የአሦር ንጉሥ መምጣት ነው። |
18. | በዚያም ቀን እንዲህ ይሆናል፤ እግዚአብሔር በግብጽ ወንዝ ዳርቻ ያለውን ዝምብ በአሦርም አገር ያለውን ንብ በፉጨት ይጠራል። |
19. | ይመጡማል፥ እነርሱም ሁሉ በበረሃ ሸለቆ በድንጋይም ዋሻ ውስጥ በእሾህ ቍጥቋጦ ሁሉ ላይ በማሰማርያውም ሁሉ ላይ ይሰፍራሉ። |
20. | በዚያም ቀን እግዚአብሔር ከወንዙ ማዶ በተከራየው ምላጭ በአሦር ንጉሥ የራሱንና የእግሩን ጠጕር ይላጨዋል፤ ምላጩም ጢሙን ደግሞ ይበላል። |
21. | በዚያም ቀን እንዲህ ይሆናል፤ ሰው አንዲት ጊደርን ሁለት በጎችንም ያሳድጋል፤ |
22. | ከሚሰጡት ወተት ብዛት የተነሣ ቅቤ ይበላል፤ በአገሪቱም መካከል የቀረ ሁሉ ቅቤና ማር ይበላል። |
23. | በዚያም ቀን እንዲህ ይሆናል፤ ሺህ ብር የተገመተ ሺህ የወይን ግንድ በነበረበት ስፍራ ሁሉ ለኵርንችትና ለእሾህ ይሆናል። |
24. | ኵርንችትና እሾህ በምድር ሁሉ ላይ ነውና በፍላጻና በቀስት ወደዚያ ይገባሉ። |
25. | በመቈፈርያም ወደ ተቈፈሩ ኮረብቶች ሁሉ ከኵርንችትና እሾህ ፍርሃት የተነሣ ወደዚያ አትሄድም፤ ነገር ግን የበሬ ማሰማርያና የበግ መራገጫ ይሆናል። |
← Isaiah (7/66) → |