Isaiah (66/66)    

1. እግዚአብሔር እንዲህ ይላል። ሰማይ ዙፋኔ ነው፥ ምድርም የእግሬ መረገጫ ናት፤ የምትሠሩልኝ ቤት ምን ዓይነት ነው? የማርፍበትስ ስፍራ ምንድር ነው?
2. እነዚህን ሁሉ እጄ ሠርታለችና እነዚህ ሁሉ የእኔ ናቸው ይላል እግዚአብሔር፤ ነገር ግን ወደዚህ ወደ ትሑት፥ መንፈሱም ወደ ተሰበረ፥ በቃሌም ወደሚንቀጠቀጥ ሰው እመለከታለሁ።
3. በሬን የሚያርድልኝ ሰውን እንደሚገድል ነው፤ ጠቦትንም የሚሠዋ የውሻውን አንገት እንደሚሰብር ነው፤ የእህልን ቍርባን የሚያቀርብ የእርያን ደም እንደሚያቀርብ ነው፤ ዕጣንን የሚያጥን ጣዖትን እንደሚባርክ ነው። እነዚህ የገዛ መንገዳቸውን መረጡ፤ ነፍሳቸውም በርኵሰታቸው ደስ ይላታል፤
4. እኔ ደግሞ የተሳለቀባቸውን እመርጣለሁ፥ የፈሩትንም ነገር አመጣባቸዋለሁ፤ በፊቴ ክፉ ነገርን አደረጉ፥ ያልወደድሁትንም መረጡ እንጂ በጠራሁ ጊዜ አልመለሱልኝምና፥ በተናገርሁም ጊዜ አልሰሙኝምና።
5. በቃሉ የምትንቀጠቀጡ ሆይ፥ የእግዚአብሔርን ቃል ስሙ። የጠሉአችሁ ስለ ስሜም ያባረሩአችሁ ወንድሞቻችሁ። ደስታችሁን እናይ ዘንድ እግዚአብሔር ይክበር ብለዋል፤ ነገር ግን ያፍራሉ።
6. የጩኸት ድምፅ ከከተማ፥ ድምፅም ከመቅደስ፥ በጠላቶቹ ላይ ፍዳን የሚያመጣ የእግዚአብሔር ድምፅ ተሰምቶአል።
7. ሳታምጥ ወለደች፤ ምጥም ሳያገኛት ወንድ ልጅን ወለደች።
8. ከቶ እንዲህ ያለ ነገር ማን ሰምቶአል? እንዲህስ ያለ ነገር ማን አይቶአል? በውኑ አገር በአንድ ቀን ታምጣለችን? ወይስ በአንድ ጊዜ ሕዝብ ይወለዳልን? ጽዮን እንዳማጠች ወዲያው ልጆችዋን ወልዳለችና።
9. በውኑ ወደ መውለድ የማደርስ እኔ አላስወልድምን? ይላል እግዚአብሔር፤ የማስወልድስ ማኅፀንን እኔ እዘጋለሁን? ይላል አምላክሽ።
10. እናንተ የምትወድዱአት ሁሉ፥ ከኢየሩሳሌም ጋር ሐሤትን አድርጉ፥ ስለ እርስዋም ደስ ይበላችሁ፤ እናንተም የምታለቅሱላት ሁሉ፥ ከእርስዋ ጋር በደስታ ሐሤትን አድርጉ፥
11. ትጠቡ ዘንድ ከማጽናናትዋም ጡት ትጠግቡ ዘንድ፤ እጅግ ጠጥታችሁ በክብርዋ ሙላት ደስ ይላችሁ ዘንድ።
12. እግዚአብሔር እንዲህ ይላልና። እነሆ፥ ሰላምን እንደ ወንዝ፥ የአሕዛብንም ክብር እንደሚጐርፍ ፈሳሽ እመልስላታለሁ፤ ከዚያም ትጠባላችሁ፥ በጫንቃ ላይ ይሸከሙአችኋል በጕልበትም ላይ እያስቀመጡ ያቀማጥሉአችኋል።
13. እናት ልጅዋን እንደምታጽናና እንዲሁ አጽናናችኋለሁ፥ በኢየሩሳሌምም ውስጥ ትጽናናላችሁ።
14. ታያላችሁ፥ ልባችሁም ሐሤት ታደርጋለች፥ አጥንታችሁም እንደ ለምለም ሣር ትበቅላለች፤ የእግዚአብሔርም እጅ ለሚፈሩት ትታወቃለች፥ በጠላቶቹም ላይ ይቈጣል።
15. እነሆ፥ እግዚአብሔር መዓቱን በቍጣ፥ ዘለፋውንም በእሳት ነበልባል ይመልስ ዘንድ ከእሳት ጋር ይመጣል፥ ሰረገሎቹም እንደ ዐውሎ ነፋስ ይሆናሉ።
16. እግዚአብሔርም በሥጋ ለባሽ ሁሉ ላይ በእሳትና በሰይፉ ይፈርዳል፤ በእግዚአብሔርም ተወግተው የሞቱት ይበዛሉ።
17. በመካከላቸው ያለውን አንዱን ተከትለው ወደ ገነቱ ይገቡ ዘንድ ሰውነታቸውን የሚቀድሱና የሚያነጹ፥ የእሪያንም ሥጋ አስጸያፊ ነገርንም አይጥንም የሚበሉ በአንድነት ይጠፋሉ፥ ይላል እግዚአብሔር።
18. ሥራቸውንና አሳባቸውን አውቄአለሁና፤ አሕዛብንና ልሳናትን ሁሉ የምሰበስብበት ጊዜ ይደርሳል፥ እነርሱም ይመጣሉ ክብሬንም ያያሉ።
19. በመካከላቸውም ምልክት አደርጋለሁ፥ ከእነርሱም የዳኑትን ዝናዬን ወዳልሰሙ፥ ክብሬንም ወዳላዩ ወደ አሕዛብ ወደ ተርሴስ ወደ ፉጥ ወደ ሉድ ወደ ሞሳሕ ወደ ቶቤል ወደ ያዋን በሩቅ ወዳሉ ደሴቶች እልካቸዋለሁ፥ በአሕዛብም መካከል ክብሬንም ይናገራሉ።
20. የእስራኤል ልጆች ቍርባናቸውን በጥሩ ዕቃ አድርገው ወደ እግዚአብሔር ቤት እንደሚያመጡ፥ እንዲሁ ለእግዚአብሔር ቍርባን ይሆን ዘንድ ወንድሞቻችሁን ሁሉ፥ በፈረሶችና በሰረገሎች፥ በአልጋዎችና በበቅሎች በጠያር ግመሎችም ላይ አድርገው፥ ከአሕዛብ ሁሉ ወደ ተቀደሰው ተራራዬ ወደ ኢየሩሳሌም ያመጡአቸዋል፥ ይላል እግዚአብሔር።
21. ካህናትና ሌዋውያን እንዲሆኑ ከእነርሱ እወስዳለሁ፥ ይላል እግዚአብሔር።
22. እኔ የምሠራቸው አዲስ ሰማይና አዲስ ምድር ከፊቴ ጸንተው እንደሚኖሩ፥ እንዲሁ ዘራችሁና ስማችሁ ጸንተው ይኖራሉ፥ ይላል እግዚአብሔር።
23. እንዲህ ይሆናል፤ በየመባቻውና በየሰንበቱ ሥጋ ለባሽ ሁሉ በፊቴ ይሰግድ ዘንድ ዘወትር ይመጣል፥ ይላል እግዚአብሔር።
24. ወጥተውም በእኔ ያመፁብኝን ሰዎች ሬሳቸውን ያያሉ፤ ትላቸው አይሞትምና፥ እሳታቸውም አይጠፋምና፤ ለሥጋ ለባሽም ሁሉ አስጸያፊ ነገር ይሆናሉ።

  Isaiah (66/66)