← Isaiah (65/66) → |
1. | ላልጠየቁኝ ተገለጥሁ፥ ላልፈለጉኝም ተገኘሁ፤ በስሜም ያልተጠራውን ሕዝብ። እነሆኝ፥ እነሆኝ አልሁት። |
2. | መልካም ባልሆነው መንገድ፥ አሳባቸውን እየተከተሉ፥ ወደሚሄዱ ወደ ዓመፀኛ ሕዝብ ቀኑን ሁሉ እጆቼን ዘረጋሁ። |
3. | ይህ ሕዝብ ዘወትር የሚያስቈጡኝ ናቸው፤ እነርሱ በአትክልት ውስጥ የሚሠዉ በጡብም ላይ የሚያጥኑ፥ |
4. | በመቃብርም መካከል የሚቀመጡ፥ በስውርም ስፍራ የሚያድሩ፥ የእሪያ ሥጋም የሚበሉ ናቸው። የረከሰው መረቅ በዕቃቸው ውስጥ አለ። |
5. | እነርሱም። ለራስህ ቁም፥ እኔ ከአንተ ይልቅ ቅዱስ ነኝና ወደ እኔ አትቅረብ ይላሉ፤ እነዚህ በአፍንጫዬ ዘንድ ጢስ ቀኑንም ሁሉ የምትነድድ እሳት ናቸው። |
6. | እነሆ፥ በፊቴ ተጽፎአል። ኃጢአታችሁና የአባቶቻችሁን ኃጢአት በአንድ ላይ ወደ ብብታቸው ፍዳ አድርጌ አመልሳለሁ እንጂ ዝም አልልም፥ ይላል እግዚአብሔር፤ |
7. | በተራሮችም ላይ ስላጠኑ፥ በኮረብቶችም ላይ ስለ ሰደቡኝ፥ ስለዚህ አስቀድመው የሠሩትን ሥራቸውን በብብታቸው እሰፍራለሁ። |
8. | እግዚአብሔር እንዲህ ይላል። ወይን በዘለላው በተገኘች ጊዜ። በረከት በእርስዋ ላይ አለና አታጥፉት እንደሚባለው፥ ሁሉን እንዳላጠፉ ስለባሪያዎቼ እንዲሁ አደርጋለሁ። |
9. | ከያዕቆብ ዘርን ከይሁዳም ተራሮቼን የሚወርሰውን አወጣለሁ፤ እኔም የመረጥኋቸው ይወርሱአታል፥ ባሪያዎቼም በዚያ ይኖራሉ። |
10. | ሳሮንም የበጎች ማሰማርያ፥ የአኮርም ሸለቆ የላሞች መመሰግያ ለፈልጉኝ ሕዝቤ ይሆናል። |
11. | እናንተን ግን እግዚአብሔርን የተዋችሁትን፥ ቅዱሱንም ተራራዬን የረሳችሁትን፥ ጉድ ለተባለ ጣዖትም ማዕድ ያዘጋጃችሁትን፥ እድል ለተባለ ጣዖትም የወይን ጠጅ ለመጠጥ ቍርባን የቀዳችሁትን፥ |
12. | እድላችሁን ለሰይፍ አደርገዋለሁ፥ ሁላችሁም ለመታረድ ትጐነበሳላችሁ፤ በፊቴም ክፉ ነገርን አደረጋችሁ፥ ያልወደድሁትንም መረጣችሁ እንጂ በጠራሁ ጊዜ አልመለሳችሁልኝምና፥ በተናገርሁም ጊዜ አልሰማችሁኝምና። |
13. | ስለዚህ ጌታ እግዚአብሔር እንዲህ ይላል። እነሆ፥ ባሪያዎቼ ይበላሉ እናንተ ግን ትራባላችሁ፤ እነሆ፥ ባሪያዎቼ ይጠጣሉ እናንተ ግን ትጠማላችሁ፤ እነሆ፥ ባሪያዎቼ ደስ ይላቸዋል እናንተ ግን ታፍራላችሁ፤ |
14. | እነሆ፥ ባሪያዎቼ ከልባቸው ደስታ የተነሣ ይዘምራሉ፥ እናንተ ግን ከልባችሁ ኀዘን የተነሣ ትጮኻላችሁ፥ መንፈሳችሁም ስለ ተሰበረ ወዮ ትላላችሁ። |
15. | ስማችሁንም ለተመረጡት ሕዝቤ እርግማን አድርጋችሁ ትተዋላችሁ፥ ጌታ እግዚአብሔርም ይገድላችኋል፥ ባሪያዎቹንም በሌላ ስም ይጠራቸዋል። |
16. | እንዲሁም በምድር ላይ የተባረከ በእውነት አምላክ ይባረካል፥ በምድርም ላይ የማለ በእውነት አምላክ ይምላል፤ የቀድሞው ጭንቀት ተረስቶአልና፥ ከዓይኔም ተሰውሮአልና። |
17. | እነሆ፥ አዲስ ሰማይና አዲስ ምድር እፈጥራለሁና፤ የቀደሙትም አይታሰቡም፥ ወደ ልብም አይገቡም። |
18. | ነገር ግን በፈጠርሁት ደስ ይበላችሁ ለዘላለምም ሐሤት አድርጉ፤ እነሆ፥ ኢየሩሳሌምን ለሐሤት፥ ሕዝብዋንም ለደስታ እፈጥራለሁና። |
19. | እኔም በኢየሩሳሌም ሐሤት አደርጋለሁ በሕዝቤም ደስ ይለኛል፤ ከዚያም ወዲያ የልቅሶ ድምፅና የዋይታ ድምፅ አይሰማባትም። |
20. | ከዚያም ወዲያ ጥቂት ዘመን ብቻ የሚኖር ሕፃን፥ ወይም ዕድሜውን ያልፈጸመ ሽማግሌ አይገኝም፤ ጕልማሳው የመቶ ዓመት ሆኖት ይሞታልና፥ ኃጢአተኛውም የመቶ ዓመት ሆኖት የተረገመ ይሆናልና። |
21. | ቤቶችንም ይሠራሉ ይቀመጡባቸውማል፤ ወይኑንም ይተክላሉ ፍሬውንም ይበላሉ። |
22. | ሌላ እንዲቀመጥበት አይሠሩም፥ ሌላም እንዲበላው አይተከሉም፤ የሕዝቤ ዕድሜ እንደ ዛፍ ዕድሜ ይሆናልና፥ እኔም የመረጥኋቸው በእጃቸው ሥራ ረጅም ዘመን ደስ ይላቸዋልና። |
23. | እነርሱ ከነልጆቻቸው የእግዚአብሔር ቡሩካን ዘር ናቸውና በከንቱ አይደክሙም ለጥፋትም አይወልዱም። |
24. | እንዲህም ይሆናል፤ ሳይጠሩ አመልስላቸዋለሁ፥ ገናም ሲናገሩ እሰማለሁ። |
25. | ተኵላና ጠቦት በአንድነት ይሰማራሉ፥ አንበሳም እንደ በሬ ገለባ ይበላል፥ የእባብም መብል ትቢያ ይሆናል። በተቀደሰው ተራራዬ ሁሉ አይጐዱም፥ አያጠፉምም፥ ይላል እግዚአብሔር። |
← Isaiah (65/66) → |